ከድሬዳዋ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ወደ ጅቡቲ የሚያቀና መንገደኛ የ19 የተለያዩ አገራት መገበያያገንዘቦችን ይዞ ሊወጣ ሲል በድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጣቢያ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ውሏል። አሕመድ ኡስማን የተባሉ ግለሰብ በድሬዳዋ አየር ማረፊያ በተደረገባቸው ፍተሻ የተለያዩ አገራትን ገንዘቦች ለማስወጣት እየሞከሩ እንደነበር ተደርሶባቸዋል። ግለሰቡም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሔደባቸው እንደሚገኝ የገቢዎች ሚንስቴር አስታውቋል።
ሚንስቴሩ እንዳስታወቀው በፍተሻ ጣቢያዎች በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ፣ ሕገ ወጥ ገንዘቦች፣ ጎጂ መድኃኒቶችና ሐሺሾች እንደሚያዙ ገልጾ፤ በአንድ ግለሰብ ይህን ያህል የበርካታ አገራት ገንዘቦች በአንድ ጊዜ ሲያዝ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጿል።
በቁጥጥር ስር ከዋለው ግለሰብ ውስጥ ከ8095 ዩሮ እስከ 25 የደቡብ ሱዳን ፓውንድ አብሮ መያዙን ከገቢዎች ሚንስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል። በከፍተኛ መጠን ከተያዙትም ውስጥ ዩሮ፣ ዶላር የተባበሩት ዐረብ ኢመሬቶች ድርሐም ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይይዛሉ።



