አማራ ባንክ ኹለት ቢሊዮን ብር በላይ አክሲዮን መሸጡን ገለፀ

0
1039

አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የአክሲዮን ሽያጭ ጊዜውን ማራዘሙን በሶሰት ወራት ውስጥ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ቃል የተገባ አክሲዮን መሰብሰቡን እና ከዚህ ውስጥም የተከፈለው አክሲዮን ከ1.9 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን አስታወቀ።

ባንኩ የአክሲዮን ሽያጩን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ 34 በላይ የሚሆኑ ባለ አክሲዮኖች ከ1.9 ቢሊዮን ብር በላይ አክሲዮን ድርሻ መግዛታቸው የተገለፀ ሲሆን፣ ከ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ቃል መገባቱን የባንኩ ፕሮጀክት አስተባባሪ መሰንበት ሸንቁጥ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲሱ የባንክ ሥራ አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ የሚታወጅበትን ጊዜ ለመጠበቅ እንዲሁም አርሶ አደሮች ሰብል የሚሰበስቡበት ወቅት መሆኑን ተከትሎ ምርታችውን ሰብስበው ጨርሰው በአክስዮን ግዢው ላይ እንዲሳተፉ ለማስቻል በማሰብም፣ ባንኩ የአክሲዮን ሽያጭ ጊዜውን እስከ ታኅሳስ 30/2012 ማራዘሙን መሰንበት ገልፀዋል።
የአክሲዮን ሽያጭ ሒደቱ የሚያበረታታ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ የባንኩን የኢንቨስትመንት አቅም እና ተአማኒነት ለማጠናከር አክሲዮን መግዛት የሚፈልጉ ግለሰቦች 50 በመቶ ክፍያ በመፈፀም ሌላውን በረዥም ጊዜ ክፍያ የሚያከናውኑበት እድል መመቻቸቱም ተጠቅሷል። መጪው ጥር ወርም የባንኩን የዳይሬክተሮች ቦርድ ለመምረጥ ጠቅላላ ጉባዔ ይጠራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ ቦርዱን የሚገመግምበትን የአንድ ወር ጊዜ ጨምሮ አማራ ባንክ በመጋቢት ወር መደበኛ የባንክ አገልግሎት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

የባንኩን አክሲዮኖች ለመሸጥ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ካገኘ ጀምሮ አስፈላጊውን ካፒታል ለማሰባሰብ ውክልና በወሰዱ ግለሰቦች አስተባባሪነት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አክሲዮኖች እየሸጠ እንደሚገኝም ተገልጿል።
ባንኩን ለማቋቋም ምሁራን፣ የአማራ ክልልን ጨምሮ በርካታ የአገር ተቆርቋሪ አካላትን በማሰባሰብ እየተደራጀ የሚገኝ ሲሆን፣ ባንኩ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅትና ከፖለቲካ አመለካከት ጋር ያልወገነ ስለመሆኑ እንዲሁም ለበርካታ በፋይናንስ የትምህርት ዘርፍ ለሠለጠኑ እና የሥራ እድል ላላገኙ ወጣቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥር በተደጋጋሚ ገልጿል።

አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ነሐሴ 11/2011 በይፋ የአክሲዮን ሽያጩን የጀመረ ሲሆን፣ ባንኩ በ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና በኹለት ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል እንደሚቋቋም ይጠበቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here