ሽልማታዊ ሳምንት

0
608

ሳምንቱ ኢትዮጵያ በልጆቿ ዓለም ዐቀፋዊ ሽልማቶችን ስትጎናፀፍ ያሳለፈችበት የኩራት ሳምንት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በአንድ በኩል በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ‹በሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ላይ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፣ ሴቶች በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩም ያደረጉት አስተዋጽኦ ልዩ ነው›› በሚል ለሰናይት መብርሀቱ በሲኤንኤን የዓመቱ ምርጥ ጀግና ተብለው ተሸልመዋል።
ሥመ ጥሩ፤ የአገረ አሜሪካ ልሳን የሚባለው እና መቀመጫውን በቅንጡዋ አትላንታ ከተማ ያደረገው ሲኤንኤን፣ ሰናይትን 2019 ጀግና አድርጎ መሸለሙ ታዲያ በአገር ቤት ልዩ ስሜትን የፈጠረ ነበር። ብሔር፣ ጎሣ፣ ጎጥ ተከፋፍሎ ለሚጠዛጠዘው ኹሉ፣ ሽልማቱ እጅግ ቀልብን የሚገዛና ወደ አንድ ያቀራረበም ነው። ኢትዮጵያም ‹‹አበጀሽ! ከወለዱ አይቀር እንደአንቺ ነው እንጂ›› ተብላ ደስታን አጣጥማለች።
ሌላም አለ፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2019 የዓለም የሰላም የኖቤል አሸናፊ መሆናቸው ከተነገረ ዋል አደር ማለቱ የሚታወስ ነው። ነገር ግን የሽልማት ሥነ ስርዓቱ በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነበር በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ የተከናወነው። በዚህ የሽልማት መርሃ ግብር ላይ ዓለም በአንድ አቅጣጫ ሥሟን እንኳን ሰምቶት ወደ ማያውቀው ቢሰማም በደኅና ነገር ስሟ ወደ ማይነሳው አገር ኢትዮጵያ ዐይኖቹን አንስቶ በአድናቆት አጨብጭቧል። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ ከሆነ፣ ከ1 ቢሊዮን ሕዝብ በላይ ደግሞ በዓለም ላይ ሒደቱን ተከታትሏል፣ አይቷል፣ ሰምቷል።
ከሽልማቱ ጋር ተያይዞ፣ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ከፍ ብላለች። በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ባለቤታቸው አርፈውበታል በተባለው የኦስሎው ግራንድ ሆቴል ደጅ ላይ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በአንድነት ሕብረ ቀለማትን ፈጥረው ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚያወድሱ መፈክሮችን እና የድጋፍ ድምጾችን ሲያሰሙ ተስተውለዋል። ምሥራቅ አፍሪካ ያውም ኢትዮጵያ ያሉ እንጂ ብዙ ሺሕ ማይሎችን ርቀው በሰው አገር ያሉ እስከማይመስሉ፣ በቋንቋቸው ሲዘፍኑ እና ሲጨፍሩ ለተመለከተ ኢትዮጵያ ከውስጣቸው አልወጣችም፤ ‹እግር እንጂ ልብ ከአገር አይርቅም› አስብሏል።
የሽልማት ሥነ ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የጠላትም ሆነ የወዳጅን ቀልብ የሚገዛ ንግግር አድርገው ዓለምን አስደምመዋል። በተለይ ደግሞ በኢትዮ-ኤርትራ በኩል የተፈጠረውን የሰላም ግንኙነት በተመለከተ እጅግ ይበል የሚያሰኝ ንግግር ማድረጋቸው አድናቆትን ፈጥሮላቸዋል። ሳምንቱ በዚህ መልኩ በኹለቱ ሽልማቶች ደምቆ ተጠናቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here