በወላይታ ዞን እስር ላይ የነበሩ ግለሰቦች መፈታታቸው ተገለፀ

0
572

የወላይታ ዞን ክልልነት ጥያቄን ተከትሎ ከታኅሳስ 9/2012 ጀምሮ የታሰሩ ግለሰቦች ከወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አንዱዓለም ታደሰ ውጪ ከእስር መፈታታቸው ተገለፀ።
በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ወላይታ ሶዶ ከተማ ከትናንት ታኅሳስ 9/2012 ምሽት ጀምሮ እስከ አርብ ጠዋት ድረስ ስድስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው የቆዩ ሲሆን ከግለሰቦቹ መካከል ከወብን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ውጪ ሁሉም መለቀቃቸውን የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ አስታውቋል።
በቁጥጥር ስር ውለው የቆዩት ግለሰቦች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የክልልነት ጥያቄውን አስመልክቶ ሰፊ ንቅናቄ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ በቁጥጥር ስር የዋሉትም ታኅሳስ 10/2012 ከሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ምክንያት እንደነበር ተገልጿል።
ታኅሳስ 10 ረፋዱ ላይም ወርቅነህ ገበየሁ እና አሸናፊ ከበደ የተባሉ ግለሰቦች የተለቀቁ ሲሆንኅ ከሰዓት በኋላ ደግም የቀሩት ተለቀዋል።
የወብን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አንዱዓለም ታደሰ ትላንት አመሻሹ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለፁት ተከተል ላቤና፤ አሸናፊ ከበደ፣ ወርቅነህ ገበየሁ እና ቡዟየሁ ቡቼ የተባሉት ከእስር የተፈቱ ግለሰቦች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚሟገቱ እንደሆኑ ገልፀዋል።
ብርቱካን የተባሉ አንዲት ሴት ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውለው መቆየታቸውን የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተከተል ላቤና ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ኃላፊው በቁጥጥር ስር እንዲቆይ መደረጉ አግባብነት የሌለው ነው ያሉ ሲሆን፣ ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ስንሔድ ለማየት ተከልክለናል ብለዋል። ‹‹በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ችለናል፤ ሆኖም ሊያሳስረው የሚችል ምንም ዓይነት ምክንያት ባለመኖሩ በአፋጣኝ ሊፈታ ይገባል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የክልልነት ጥያቄው በተባለው ጊዜ ምላሽ አለማግኘቱንም ተከትሎ፣ በወላይታ ዞን ካሉት 22 ወረዳዎች ሶዶ እና አረካ ሳይጨምር በ20 ወረዳዎች ላይ ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉንም ጨምረው ገልፀዋል። ሰልፉ ፍፁም ሰላማዊ እንደነበር እና በሰዎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰም ተገልጿል።
ሕዝቡ በሰላማዊ ሰልፉ ወቅት ፍፁም ሰላማዊ ነበር። ይሄንንም ተከትሎ ምንም ዓይነት ጉዳት በሰዎች ላይ እንዳልደረሰ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በዞኑ እና በሶዶ ከተማ በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተከተል ተናግረዋል።
በወረዳዎቹ ከተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በኋላም በወላይታ ሶዶ ከተማ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጌታሁን ጋረደው እና የዞኑ አስተዳዳሪ እንዲሁም አገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች የተሳተፉበት ውይይት ተደርጓል። የክልሉ ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን በተከተለ መንገድ የዞኑን ጥያቄ ማስተናገድ እንዳለበትም በውይይቱ እንደተጠቆመ ታውቋል።
‹‹በከተማዋ ተዘግተው የነበሩ የንግድ ማእከላት ወደ ቀድሞ ሥራቸው በመመለስ ላይ ይገኛሉ›› ያሉት ተከተል፣ የክልልነት ጥያቄው ተገቢውን ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የክልልነት ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የወላይታ ዞን አስተዳዳሪን በጉዳዩ ላይ በስልክ እና በጽሑፍ መልዕክት ለማነጋገር አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም ሳይሳካላት ቀርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here