የንግድ ተቋማት እስከ ዓመቱ መጨረሻ ዓለማቀፉን የሂሳብ አቀራረብ ዘዴ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጠ

0
562

የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ እስከ 2012 መጨረሻ ዓመታዊ ገቢያቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የመንግሥት፣ የግል እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በዓለም ዐቀፉ የሂሳብ አቀራረብ ዘዴ (IFRS) ተመዝግበው ዓመታዊ የገንዘብ ሪፖርታቸውን በዚህ አሠራር መሰረት እንዲያቀርቡ አሳሰበ።
ዓመታዊ ገቢያቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የንግድ ድርጅቶች፣ እስከ 2012 መጨረሻ በ (IFRS) ተመዝግበው የሂሳብ ዘገባዎችን ለቦርዱ የማያሳውቁ ከሆነ ቦርዱ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።
ከ2010 ጀምሮ መካከለኛ እና ጥቃቅን የንግድ ተቋማት የኹለት ዓመት የሂሳብ ዘገባቸውን በዚሁ ዘዴ መሰረት እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብ ቢቆይም፣ በንግድ ሚኒስቴር ተመዝግበው ከሚገኙ ከ 200 ሺሕ የንግድ ተቋማት ውስጥ እስከ አሁን ተመዝግበው የሂሳብ አያያዝ እና ዘገባ ዘዴያቸውን የቀየሩት ከ 35 ሺሕ እንደማይበልጡ ቦርዱ ገልጿል።
ቦርዱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ የሕዝብ ጥቅም ያለባቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች፣ የበጎ አድራጎት ማኅበራት እና የንግድ ተቋማት በኢትዮጵያ አሠራሩን እንዲተገበሩ ከ 2008 ጀምሮ ሲሠራ መቆየቱን ገልጿል። በዚህ መሰረትም የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ተቋማቱን ባላቸው የሀብት እና የሕዝብ ጥቅም ደረጃ ሲከፋፍል መቆየቱ ተገልጿል።
እነዚህንም ተቋማት በሦስት ዐበይት ክፍሎች በመክፈል ከፍተኛ ሕዝብ ጥቅም ያለባቸው ተቋማት፣ ሌሎች የሕዝብ ጥቅም ያለባቸው እና ከ 50 ሚሊዮን ብር በላይ በዓመት የሚያንቀሳቅሱ በምርት ገበያ የተመዘገቡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሲሆኑ፣ መካከለኛ እና ጥቃቅን የንግድ ተቋማት በሚል የተከፋፈሉት ደግሞ በዓመት ከ 1 ሚሊዮን እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚያንቀሳቅሱ ናቸው።
ከ 2008 ጀምሮ በቅድም ተከተላቸው መሰረት ከ 18 እስከ 24 በሚደርሱ ወራት በዓለም ዓቀፉ የሂሳብ አቀራረብ ዘዴ (IFRS) እንዲተገብሩ ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውቋል።
አሠራሩ ተግባራዊ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ፣ በርካታ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች ሂሳብ አያያዝ እና አዘጋገብ ዘዴያቸውን በዚሁ መንገድ እንዲያደርጉ ቦርዱ ሲሠራ መቆየቱን የገለፁት የቦርዱ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ ሺፈራው፣ በርካታ መንግሥታዊ ልማት ድርጅቶች ካለው ፖለቲካዊ ሁኔታ እና ለሺሽጓቸው የሚፈልጓቸው ክፍተቶች በመኖራችው እስከ አሁን በዚህ መንገድ አለማቅረባቸውን ገልፀዋል።
እስከ አሁንም ለበርካታ ዓመታት ኦዲት ተደርገው የማያውቁ የመንግሥተ የልማት ድርጅቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ኀላፊው፣ ‹‹ኦዲት ማድረግ የቦርዱ ኀላፊነት አይደለም፤ የቦርዱ ኀላፊነት የተቋማቱን ተጠሪ አካላት አሠራሩን እንዲያስተገብሩ ማድረግ ነው›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሳይቀር አሠራሩን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኝነት አይታይም ያሉት ኀላፊው፣ ቦርዱ ባለው አቅም አሠራሩ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ በመሥራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘርፉ ከፍተኛ የዕውቀት ክፍትት መኖሩ በተደጋጋሚ እንደሚነሳ ያወሱት ኀላፊው፤ እውቅና ያላቸው የሂሳብ ተቋማት እና ኦዲተሮች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ ለሥራው ከፍተኛ ዋጋ እንዲጠይቁ በር ከፍቷል። የእውቀት ክፍተቱንም ለማጥበብ ‹‹34 ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ መምህራን ሥልጠናዎችን ሰጥተናል፤ በየጊዜውም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀት ስንሰጥ ቆይተናል›› ብለዋል።
ይህ አሰራር የተቋማትን እያንዳንዱን ንብረት በመመዝገብ እና በገበያ ላይ ያለውን ዋጋ መሰረት ባደረገ መልኩ የተቋማትን እና የድርጅቶችን ሀብት ለማወቅ የሚረዳ መሆኑ ታምኖበት በመተግበር ላይ ይገኛል ያሉት አበበ፣ በተቋማት በኩል ግን በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ ወደ አሠራሩ ለመግባት እንደሚያመነቱ ጠቅሰዋል። ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቀሰው ኦዲተሮች እና ሂሳብ አዋቂዎች ተቋማቱን የሚጠይቁት ከፍተኛ ገንዘብ ነው ያሉ ሲሆን፣ የተቋማቱ ኀላፊዎች የተጠየቁትን ከመክፈላቸው በፊት አማራጮችን ማየት እና ቦርዱን ማማከር ይኖርባቸዋል ብለዋል።
አያይዘውም ‹‹በቀረው ጊዜ እነዚህ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ አሠራሩ ይገባሉ የሚል ሐሳብ የለኝም። ካላቸው የቁጥር ብዛት አንፃርም ቅጣት ለማስተላለፍ አስቸጋሪ ይሆናል። በመሆኑም የአዋጅ ማሻሻያዎች እና አሠራር ለውጦች ሊደረጉ ይችላሉ›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ከ 15 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱት አብዱልመናን መሐመድ በበኩላቸው፣ ዓለም ዐቀፉ የሂሳብ አቀራረብ ዘዴ (IFRS) ተግባራዊ የተደረገው በምዕራቡ ዓለም ያለውን የተወሳሰበ የሂሳብ ዘገባ ፍላጎት እንዲሁም የመረጃ ፍላጎት ሟሟላት በማስፈለጉ ነው ብለዋል።
አሠራሩ ቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ መገልበጡ አሰፈላጊ አይደለም፤ በተለይም እነዚህ አነስተኛ እና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ብር በላይ ገቢ ያላቸው ድርጅቶች ላይ መደረጉ ድርጅቶቹን ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ እና አላስፈላጊ ጫና ውስጥ እንዲገቡ የሚያደረግ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ዓለም ዐቀፉ የሂሳብ አቀራረብ ዘዴን በአግባቡ የሚረዳ የሂሳብ ባለሙያ እንኳ የለም ያሉት አበዱልመናን፣ እነዚህ አነስተኛ ተቋማት አሠራሩን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ወጪ ማውጣታቸው አላስፈላጊ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
‹‹በኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት የተወሳሰቡ የሂሳብ ዘገባዎች የሚያስፈልጉት በትልልቅ እና ከፍተኛ ሕዝብ ጥቅም ባላቸው ድርጅቶች ላይ እንጂ በአነስተኛዎቹ ላይ አይደለም፤ አሠራሮች ከውጪ አገራት በቀጥታ ሲገለበጡ የሚከሰት ክፍተት ነው። አላስፈላጊ እና ማሻሻያ ሊደረግበት የሚገባው ነው›› ሲሉም አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ያለው የሂሳብ አያያዝ እና አዘጋገብ ዘዴ በመንግሥታዊም ሆነ በሌሎች ተቋማት ላይ በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑን በ2006 ዓለም ባንክ እና ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ያደረጉትን ጥናት መሰረት በማድረግ፣ ከ 2008 ጀምሮ ዓለም ዐቀፉ የሂሳብ አቀራረብ ዘዴ (IFRS) እንዲተገበር መወሰኑን ከቦርዱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here