ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን 95 ሚሊዮን ብር ካሳ ተከፈለው

0
1013

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ወደ ሥራ ከገባ ኹለተኛ ዓመቱን ለያዘውና ከአገሪቱ ግዙፍ የባቡር ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው ኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ለደረሰበት አደጋ ከ 95 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መክፈሉ ተገለፀ።
የካሳ ክፍያው የተፈፀመው ከስምንት ወራት በፊት ከሞጆ ወደ ጂቡቲ ይጓዝ በነበረ በኮርፖሬሽኑ ባቡር ላይ ለደረሰው አደጋ ሲሆን፣ የምድር ባቡሩ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት በገዛው የመድን ሽፋን መሠረት ለአደጋው ተመጣጣኝ የሆነ የካሳ ክፍያ መከፈሉ ተገልጿል።

በወቅቱ ለደረሰው አደጋም ምክንያት የሆነው በመንገዱ ላይ የነበረው ጎርፍ ባቡሩን ከሐዲዱ በማንሳት በመገልበጡ እንደሆነም የአደጋው ዘገባ ማብራሪያ ያመለክታል። አደጋው በደረሰበት ጊዜ በውስጡ አራት ፌዴራል ፖሊሶችና ዘጠኝ የባቡር ሠራተኞች እንደነበሩ የገለጸው ኮርፖሬሽኑ፣ ሦስት ቻይናውያን ሦስት ጂቡቲያውያንና ሦስት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን መግለጹ ይታወሳል። በሰው ላይ ምንም አይነት ጉዳት ባይደርስም፣ በኹለት ሎኮሞቲቮችና ኮንቴይነር የጫኑ 19 ተጎታቾች ላይ ጉዳት ተመዝግቦ ነበር።

የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር አጠቃላይ የመድን ሽፋን ለመስጠት የሚያስችለውን አሠራር ለመዘርጋት ብዙ መልፋቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የመድን ሽፋኑን በመግዛቱ ግን የደረሰበትን አደጋ ለመተካት የሚያስችለውን ሽፋን ማግኘቱ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ 44 ዓመታት በገበያ ውስጥ የቆየው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለደንበኞቹ ከከፈለው የካሳ ክፍያ በከፍተኛነቱ ሊጠቀስ የሚችለውን የ95 ነጥብ 14 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ ለኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ከፍሏል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በአሁኑ ወቅት ከሚንቀሳቀሱት 17 የመድን ድርጅቶች ውስጥ ብቸኛው የመንግሥት የኢንሹራንስ ኩባንያ ሲሆን፣ በኢንዱስትሪውም ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ ይዞ ይገኛል። ባለፉት 44 ዓመታት ለደንበኞቹ የከፈለው የጉዳት ካሳ 12.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የኩባንያው የመድን ሽፋንም በየዓመቱ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ የሰጠው የመድን ሽፋን ወይም ድርጅቱ የተሸከመው የሥጋት መጠን ከ14.4 ትሪሊዮን ብር በላይ ደርሶ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here