የባህላዊ ምግብ ቤቶች አዲሱ ገጽታ

0
1603

በኢኮኖሚ እድገት ካሳዩ ዘርፎች መካከል የአገሪቱን ዓመታዊ የጠቅላላ ምርት እድገት አርባ ከመቶ የሚሸፍነው የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። የዚሁ የኢኮኖሚ ዘርፍ ዓመታዊ የእድገት ፍጥነቱ ዐስር በመቶ ሲሆን፣ ለዚህ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ደግሞ የሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መሄድ ነው። ከእነዚህ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች መካከል አብዛኞቹ የሚገኙት አዲሰ አበባ ሲሆን፣ የከተማውን ነዋሪ የአመጋገብ ስልት ተከትለው የገበያ ትኩረታቸውን ያደረጉ ናቸው።

በአዲስ አበባ የሚገኙ እነዚህ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ኢትዮጵያ ያላትን ልዩ ልዩና በርካታ የባህል ስብጥር አያንጸባርቁም። ነገር ግን ይህ ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለወጠ የመጣ ይመስላል። የዚህም ማሳያው ከተለመደው ውጪ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን የአመጋገብ ዘይቤና ልማድ የሚያንጸባርቁ ባህላዊ ሬስቶራንቶች ብቅ ማለታቸው ነው። ከእነዚህ ሬስቶራንቶች መካከል የሲዳማ፣ የወላይታና የወለጋ ባህላዊ ምግብ ቤቶችን መጥቀስ ይቻላል።

በታዋቂዋ ዘፋኝ ትዕግስት ወይሶ የተከፈተውና ሃያ ሁለት አካባቢ የሚገኘው ‹ታይሶ የወላይታ ባህላዊ ምግብ ቤት› በቅርቡ የንግዱን ዘርፍ ከተቀላቀሉት ምግብ ቤቶች አንዱ ነው። ትዕግስት የወላይታ ባህላዊ ምግብ ቤት የመክፈት ሐሳብ የመጣላት ከአስራ ኹለት ዓመት በፊት በአርባ ምንጭ ጣፋጩን የወላይታ ባህላዊ ምግብ በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ ካጣጣመች በኋላ ነው። ምንም እንኳን የተወለደችው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኘው ወላይታ ውስጥ ቢሆንም፣ ከዚህ ክስተት ቀደም ብሎ ምግብ ቤት የመክፈት እቅድ አልነበራትም።
በተጨማሪም በወቅቱ ሙሉ ጊዜዋን ለሙዚቃ ሰጥታ ስለነበር የወላይታ ባህላዊ ምግብ ቤት የመክፈት ሐሳቧን እውን ለማድረግ ዐስር ዓመት ፈጅቶባታል። ነገር ግን በግል ምክንያት የሙዚቃውን ዓለም ለቅቃ ከወጣች በኋላ ፊትዋን ወደ ምግብ ቤት ሥራ በማዞር፣ ከዓመት በፊት ታይሶ የወላይታ ባህላዊ ምግብ ቤትን ከፍታለች። ትዕግስት ብዙ ጭብጨባ፣ አድናቂና ተመልካች ካለበት የሙዚቃ መድረክ ጭብጨባም ሆነ አድናቂ ወደሌለበት ምግብ ማብሰያ ክፍል ለመግባት አላመነታችም። በመሆኑም በግማሽ ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ታይሶ የወላይታ ባህላዊ ምግብ ቤትን ከፈተች።

‹‹የተወለድኩት ወላይታ ቢሆንም ገና ልጅ እያለሁ ነበር ወደ ከተማ የመጣሁት። በመሆኑም የወላይታ ምግብ እንዴት እንደሚሠራ አላውቅም ነበር። እናም ልክ ምግብ ቤት ለመክፈት ሳስብ የምግብ አሰራሩን ያስተማርችኝ የካሙዙ እናት ነበረች›› በማለት ትዕግስት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ትገልጻለች። ሙያውን ከካሙዙ እናት ለመማር ታድያ ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም። እንደውም ከራሷ አልፋ ወደ ዐስራ ሦስት የሚጠጉ ለሠራተኞቿ ከካሙዙ እናት ያገኘችውን ሙያ አሠልጥናለች።

በአዲስ አበባ የሚኖሩ በርካታ ሰዎችና የተለያየ አገር ጎብኚዎች በታይሶ ምግብ ቤት ተገኝተው የወላይታን ባህላዊ ምግብ ለማጣጣም ጊዜ አልፈጀባቸውም። ‹‹ታይሶ የምመጣው ዝም ብሎ ተመግቦ ለመሔድ ብቻ ሳይሆን በብዙ ኪሎ ሜትሮች ከአዲስ አበባ ርቆ የሚገኘውን የወላይታ ሕዝብ ባህላዊ ምግብ ለማጣጣምም ጭምር ነው። ከራሴ አልፌም ብዙ ጓደኞቼን ወደዚህ አምጥቻቸዋለሁ። ሁሉም ወደውታል›› በማለት የታይሶ ደንበኛ የሆነው ብሩክ ግርማ ይገልጻል።

‹ታይሶ›ን ዓይነት ባህላዊ ምግብ ቤቶች በከተማችን እየተበራከቱ መምጣት ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ መሆኗን ከማሳየት ባለፈ አዲስ ነገርን ለሚፈልጉ ደንበኞችም ጥሩ አማራጭ ሆኗል። እንዲሁም ከተወለዱበት ቀዬ በትምህርት ወይንም በሥራ ምክንያት ርቀው ላሉ ሰዎችም፣ የናፈቃቸውንና ተወልደው ያደጉበትን ባህላዊ ምግባቸውን በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ መልካም አጋጣሚን ፈጥሮላቸዋል።

የሠላሳ ስድስት ዓመቷ ፋሲካ ዓለሙ ከዚህ መልካም አጋጣሚ ተጠቃሚዎች መካከል አንዷ ናት። በአሁኑ ወቅት የሕግ ባለሞያ የሆነችው ፋሲካ፣ ገና በ12 ዓመቷ ነበር የተሻለ ትምህርት ፍለጋ ከወላይታ ወደ አዲሰ አበባ የመጣችው። ፋሲካ ምንም እንኳን የትውልድ መንደሯን ብትናፍቅም፣ የሕይወትና የሥራ ዓለም ሩጫ እንደልቧ ወደ ወላይታ ቶሎ ቶሎ እንድትሔድ አላስቻላትም። አሁን ግን ምንም እንኳን በአካል ወደ ወላይታ ባትሔድም፣ ልጅነቷንና የእናትዋን ጓዳ እንድታስታውስ የሚያስችላት ታይሶ የወላይታ ባህላዊ ምግብ ቤት በመከፈቱ ደስተኛ ነች። በመሆኑም ቢያንስ በሳምንት አንዴ በዚህ ምግብ ቤት ትገኛለች።

‹‹በጣም ቆንጆ ምግብ ቤት ነው። ዋጋውም ቢሆን ከምግቡና አገልግሎቱ ጥራት ጋር ሲነጻጸር ፍትኀዊ ነው። ቤቱ ትንሽ ሰፋ ብሎ የሚይዘው የሰው ብዛት ቢጨምር ደስ ይለኛል። ነገር ግን አሁን ባለበት ሁኔታም ቢሆን ከቤተሰብ፣ ከጓደኛና ወዳጅ ዘመድ ጋር ሰብሰብ ብሎ ለመዝናናት ምቹ ነው። በእርግጥ እዚህ የምመጣው ለምግቡ ብቻ ብዬ ሳይሆን የቤቱ የውስጥ ዲዛይንና አገልግሎት አሰጣጡ ልጅነቴን ስለሚያስታውሰኝም ጭምር ነው›› በማለት ፋሲካ ስለታይሶ ምስክርነቷን ሰጥታለች።

የታይሶ የውስጠኛው ክፍል የወላይታ ሕዝብና ባህል መገለጫ በሆነው በጥቁር፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሸበረቀ ሲሆን ጠረጴዛ፣ ወንበርና የምግብ ዝርዝር ያለበት ሜኑም በተመሳሳይ ቀለማት ተውቧል። አብዛኞቹ በከተማችን የሚገኙ ሆቴሎችና ምግብ ቤቶች ልክ እንደታይሶ ለየት ባለ መልኩ በራሳቸውን መገለጫና በደንበኞቻቸው በቀላሉ ሊታወስ በሚችል መልኩ የውስጠኛውን ክፍላቸውን ማሳመር እየተለመደ የመጣ ነገር ሆኗል።

ታይሶ ለደንበኞቹ ለየት ያሉ ምግቦችን በምግብ ዝርዝር ውስጥ አካትቶ ይዟል። ለምሳሌ ታይሶ ስፔሻል ሰባት ዓይነት ማለትም ሳንታ ቆጭቆጭዋ፣ ሎጉሙዋ፣ ፒላ ሳንታ፣ ቢላንዱዋ፣ ሽክርክሪት፣ ክትፎና ቆጮ የተባሉ የምግብ አይነቶችን ይይዛል። ምግቦቹ በሰባት ትናንሽ ጣባዎች የሚቅረቡ ሲሆን የሙሉ ታይሶ ስፔሻል ዋጋው 500 ብር ነው፤ ግማሹ ደግሞ 250 ብር። እንደ ሙትጭዋ፣ ካሙዙ ስታይል፣ ቦያና ቡላ ያሉ ምግቦች ደግሞ ከ50 እስከ 250 ብር ባለው ዋጋ መካከል ይሸጣሉ።

ከታይሶ ወደ አምስት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ደግሞ ‹ፋንቱ› የተባለ የሲዳማ የባህል ምግብ ቤት ይገኛል። ቦሌ ድልድይ በዩጎ ቸርች መታጠፊያ በኩል የሚገኘው ፋንቱ የሲዳማ ባህል ምግብ ቤት፣ በአጠገቡ በሚያልፉ መንገደኞች ጭምር በቀላሉ የሚለይ ነው። በግቢው ውስጥ የሚገኘውና ከቀርከሀ እንጨት የሚሠራው የሲዳማ ባህላዊ ቤት ፋንቱ ምግብ ቤት በቀላሉ ዐይን ውሰጥ እንዲገባ ከማስቻሉ በተጨማሪ ለግቢው ትልቅ ግርማ ሞገስ ሰጥቶታል።
ከቀርከሀ እንጨት የተሠራውና እስከ አርባ ዓመት የሚያገለግለው የሲዳማ ባህላዊ ቤት፣ በፋንቱ ምግብ ቤት ጊቢ ውስጥ ቆሞ ሲታይ ባህሉን ከማንጸባረቅ አልፎ የሲዳማን ሕዝብ ጥበብ ይመሰክራል። ‹‹በዚህ የሲዳማ ባህላዊ ቤት ውስጥ ሆኖ የሲዳማን ምግብ መመገብ ልዩ ስሜት ይፈጥራል›› በማለት የፋንቱ የሲዳማ ባህላዊ ምግብ ቤት ደንበኛ የሆነው ሰመረ ኪዳኔ ይገልጻል።

በፋንቱ እንደ ጩካቤ እና ቡራሳማ ያሉ የምግብ ዓይነቶችን በኹለትና ሦስት መቶ ብር ማግኘት ይቻላል። እንዲሁም ጋፎማ በ80 ብር፣ ጫንጫናሜ ደግሞ በ60 ብር ይሸጣሉ። ፋንቱ በአዲስ አበባ ያለውን ቅርንጫፉን ከ10 ወር በፊት በአንድ ሚሊዮን ብር ካፒታል የከፈተ ሲሆን፣ የመጀመሪያውን ቅርንጫፉን ደግሞ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሐዋሳ በመክፈት ነበር ወደ ንግዱ ዓለም የተቀላቀለው። የፋንቱ ምግብ ቤት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የሆነው አያላ አልዩ፣ አዲስ አበባ የተለያየ ባህል ያላቸው ሕዝቦች መገኛ በመሆኗ ደንበኛ ለማግኘትም ሆነ ሥራውን ለመጀመር እምብዛም እንዳልተቸገሩ ይናገራል። ፋንቱ ለደንበኞቹ የሲዳማ ባህላዊ ምግቦችን ከማቅረብ ባሻገር ለ100 ሰዎች የሥራ እድል ፈጥሯል።

ሌላው በአዲስ አበባ ከተለመዱት በተጨማሪ አዲስ የባህል ምግቦችን በማዘጋጀት ለገበያ የሚያቀርበው ልደታ አካባቢ የሚገኘው ‹የወለጋ የባህል ምግብ ቤት› ነው። በዚህ ምግብ ቤት ውስጥ የወለጋ ባህላዊ ምግቦች የሚገኙ ሲሆን፣ እንደሌሎቹ ባህላዊ ምግብ ቤቶች ሁሉ ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በውጪ አገር ዜጎች በተደጋጋሚ ይጎበኛል።
ከላይ የተጠቅሱት ባህላዊ ምግብ ቤቶች ሥራውን ለመቀጠል የሚያበረታቷቸው ነገሮች እንዳሉ ሁሉ ሥራቸውን አስቸጋሪ ካደረጉባቸው ተግዳሮቶች ጋር መግጠም የሥራቸው አንዱ አካል ነው። ከተግዳሮቶቹ መካከልም በዘርፉ በቂ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖርና ከእለት ወደ እለት እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረት ዋነኞቹ ናቸው። ‹‹ለቤት ኪራይ በየወሩ 70 ሺሕ ብር መክፈል አለብን። በዚህ ላይ በየጊዜው የሚጨምረው ምግቦችን ለማዘጋጀት የሚረዱ ቅመማ ቅመሞችና ሌሎች ግብአቶች ሥራችንን ፈታኝ አድርገውታል›› በማለት አያላ ተግዳሮታቸውን ያስረዳል። በወር ለቤት ኪራይ 30 ሺሕ ብር የምትከፍለው ትዕግስትም፣ የአያላን ሐሳብ ትጋራለች። “የውሀና የመብራት መቆራረጥም ሌላው ፈተና ነው” በማለትም ተጨማሪ ተግዳሮቶቻቸውን አክላለች።

ምንም እንኳን የተለያዩ ብሔረሰቦችን ባህላዊ ምግቦች የሚያዘጋጁ ምግብ ቤቶች በአዲስ አበባ እየተበራከቱ የመጡ ቢሆንም፣ የተጠና የገበያ ስትራቴጂ እና ራሳቸውን የማስተዋወቅ በቂ ሥራ ባለመሥራታቸው ትችት ያስተናግዳሉ። ራሳቸውን በሚገባ ቢያስተዋውቁ ገቢያቸውን ከመጨመር ባለፈ እንደ አንድ ቱሪስቶችን የመሳቢያ መንገድ ሆነው ማገልገል እንደሚችሉ የቱሪዝም ባለሞያዎች ይገልጻሉ።

‹‹ለምሳሌ አውስትራሊያ የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑት አገሮች መካከል የምትጠቀስ ናት። ለየት ያሉ ምግቦችን በማዘጋጀት ለገበያ የሚያቀርቡ ባለሞያዎች ለቱሪዝም እድገቱ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም። ኢትዮጵያም ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ አገር በመሆኗ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን በማዘጋጀትና ለገበያ በማቅረብ የቱሪስት መስህቧን መጨመር ትችላለች። ነገር ግን ይህንን ለማድረግ መንግሥት በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት ማበረታቻ በማዘጋጀት የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት›› በማለት የሆቴልና ቱሪዝም ባለሞያ የሆነው አሰፋ አስራት ሐሳቡን አካፍሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here