የጃዋር መሐመድ የፓርቲ አባልነት ሳምንት

0
551

አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደራት የሚገኘው ለጋው የለውጥ አመራር በትረ ሥልጣኑን ከመጨበጡ አስቀድሞ በርካቶች ነፍጥ አንስተው ጫካ ገብተዋል፣ እምቢ ባይነታቸውን በሰላ ትችትና በርቱዕ አንደበት በአደባባይ ሞግተው እና ገልፀው ወደ እስር ቤት ተግዘዋል። ከፊሎቹ ደግሞ በምዕራባውያን አገራት ዘንድ ሆነው በጊዜው ሥልጣን ላይ የነበረውን አመራር ታግለዋል።

የሆነው ሆኖ አሁን ወደ ኹለተኛ ዓመት የልደት በዓሉ እየተንደረደረ ያለውን የለውጥ አመራር ወደ አራት ኪሎ መግባቱን ተከትሎ፣ ከተበተኑበት የዓለም ክፍል ወደ ኢትዮጵያ ተምመሙ፤ የፖለቲካ ምህዳሩም ሰፍቷል ተብሎ ‹‹ጉሮ ዎሸባዬ›› ተደለቀ።

ለዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሳይኖሩ፣ በስደት በሰው አገር ሆነው ገዢውን መንግሥት ሲሞግቱ ከነበሩት እና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በርካታ ተከታይ አላቸው ከሚባሉ ግለሰቦች አንዱ ደግሞ አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ነው። በማኅበራዊ ሚዲያ በሚጽፋቸው እና በብዙ ሺሕ ማይሎች ርቀት ላይ ሆኖ በሚናገረው ንግግር፣ ብዙዎችን ያውም ወጣቶች በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት ላይ እንዲነሱ ሲያደርግ የነበረው እና የየትኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል ያልነበረው ጃዋር፣ ባሳለፍነው ሳምንት ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስን መቀላቀሉን በይፋ አውጇል።

ይህ ዜና ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ታዲያ በርካቶች የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ወሬ ማድመቂያ እና የመወያያ ርዕስ አድርገውት ሰንብተዋል። አንዱ ወገን ከዚህ ቀደም ያልነበረ እና ራሱ ጃዋርም በግልጽ በተደጋጋሚ የማንኛወም የፖለቲካ ድርጅት አባል እንዳልሆነ እንዲሁም መሆን እንደማይፈልግ ሲገልጽ ኖሮ ‹‹አሁን ምን ተገኘ?›› ሲሉ ጠይቀዋል። ምን አይቶ ነው የገባው? እንዲሁም በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚታገሉ ሌሎች ድርጅቶች እያሉ እንዴት ኦፌኮን መረጠ? የሚሉ ጥያቄዎችም ተስተውለዋል።

በሌላ በኩል ያሉት ደግሞ ጃዋር በአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ መታቀፉ ከዚህ በኋላ ለሚኖረው የትኛውም አይነት እንቅስቃሴ እንደዚህ ቀደም ሁሉ እንደፈለገ አንዳይንቀሳቀስ የሚያደርግ በመሆኑ ለብዙኃኑ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነም አመክንዮ በማንሳት ይናገራሉ።

ከኹለቱ ሐሳቦች በተለየ ደግሞ፣ የኦፌኮ ሊቀ መንበር ፐሮፌሰር መረራ ጉዲና ‹‹ፓርቲያቸው ይህን አይነት ውሳኔ ሲወስን እንዴት ዝም ይላሉ ወይስ ከመጀመሪያው ጀምሮ የጃዋርን ሐሳብ ሲደግፉ ነበር?›› የሚሉ ጥያቄዎች ከዚህም ከዚያም ተደምጠዋል። በእርግጥ ሊቀ መንበሩ ጃዋር መሐመድ በይፋ ድርጅታቸውን መቀላቀሉን ከቢሯቸው እንደሰሙ ለቢቢሲ አማርኛው ክፍል ተናግረዋል።

የሆነው ሆኖ ያሳለፍነው ሳምንት ጃዋር መሐመድ ኦፌኮን መቀላቀሉ ከዚህ ቀደም በድብቅ ኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር አባል ነው ብለው ለሚጠረጥሩ ሰዎች ምላሽ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here