ሔኒከን ቢራ ፋብሪካ የሰራተኛ ቅነሳ ሊያደርግ ነው መባሉን አስተባበለ

0
695

ሔኒከን ቢራ ፋብሪካ በቅርቡ ሰራተኛ ቅነሳ ሊያደርግ ነው ተብሎ የሚናፈሰው መረጃ ሐሰት እና ከእውት የራቀ እንደሆነ አስታወቀ። የሔኒከን ቢራ ፋብሪካ ሕዝብ ግንኙነትና ማርኬቲንግ ኃላፊ ፍቃዱ በሻህ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በፋብሪካው ዘንድ ምንም አይነት ሰራተኛ የመቀነስም ሆነ የማባረር ፍላጎትም ሆነ አዝማሚያ የለም ሲሉ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ሰራተኞች መቀነሳቸው እና ከዚህም ጋር ተያይዞ በፋብሪካው ውስጥ ነበረው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሰለመፍረሱ የተጠየቁት ፍቃዱ ‹‹ሲጀመር ሕዝብ ግንኙነት የሚባል ክፍል አልነበረም ››ሲሉ ጀምረው ‹‹እኔ ብቻ ነኝ የፋብካው የውጭ ግንኙነት ባለሙያ›› ሲሉም የተባለው ጉዳይ መሰረተ ቢስ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኃላፊው ይህን ይበሉ እንጂ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት የሚገኘውን አዲሱን የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ ተከትሎ ከፍተኛ የኤክሳይስ ታክስ በቢራ ምርት ላይ በመጣሉ ፋብሪካው ላይ ከፍተኛ ገቢ መቀነስ ያጋጥማል ተብሎ በመታሰቡ እና እንዲሁም ብልሹ አሰራሮች የተገኘባቸውን የሽያጭ ሰራተኞች በድምሩ 200 የሚደርሱ ሰራተኞች በቅርቡ ፋብሪካው እንደሚቀንስ ታውቋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደምም ሰራተኞች የተቀነሱ ሲሆን በዚህም ሕዝብ ግንኙነት የሚባለው ክፍል ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ እንደተደረገ የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል።

ፋብሪካው ከኤክሳይስ ታክሱ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ አቅራቢያ በ250 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ሊያስገነባው የነበረው ማስፋፊያ ማቆሙን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁ ሲሆን አዲሱ የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያው በደምብ ያልታሰበበት እና የቢራ ፋብሪካዎችን በተለየ ደግሞ የሚጎዳ ነው ሲል ገልጾ፤ ማስፋፊያዎችን ከማቆም ባሻገር ሰራተኞችንም ለመቀነስ እንደሚገደድም ምንጮች ጨምረው ገልፀዋል።

ታህሳስ 22/2012 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዲሱን የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያን በተመለከተ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት በአምራቾች በኩል ቅሬታቸውን በስፋት አስተጋብተዋል። በተለይም ደግሞ የቢራ አምራቾች ማኅበር ከዚህ ቀደም በአንድ ሊትር እስከ ሦስት ብር ይጣል የነበረው ኤክሳይስ ታክስ በአዲሱ ማሻሻያ ከዘጠኝ እስከ አስራ አንድ ብር በሊትር እንዲጣል መወሰኑ አግባብ አይደለም ዘርፉን የሚያቀጭጭ እንደሆነም በመጥቀስ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። በዚሁ መድረክ ላይ የውሃ አምራቾች ማህበርም ከዚህ ቀደም የነበረው የ20 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ ወደ 15 በመቶ ዝቅ ይበል እንጂ አዲሱ ስሌት በሽጭ ላይ የዋጋ ጭማሪ ስለሚያመጣ ቢቻል እንዲያውም ኤክሳይስ ታክሱ በውሃ ላይ ሙሉ በሙሉ ቢቀር የሚል ሃሳብም ሰንዝረዋል።

አዲሱን የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ በተመለከተ የገቢዎች ሚንስትር አዳነች አቤቤ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት አዲሱ ማሻሻያ ወደ ታች ሲወርድ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ አያመጣም ሲሉ ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው በአምራች ዘርፉ ላይ በግብዓቶች ላይ ይጣል የነበረው ኤክሳይስ ታክስም ወደ ምርቶቹ በመዞሩ አምራቾች በግብዓት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ያጭበረብሩ እንደነበርና የአሁኑ አካሔድ ይህንንም እንደሚቀርፍ ያስረዳሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ እና የንግድ ተደራዳሪው ማሞ ምህረቱ በአዲሱ ኤክሳይስ ታክስ ዙሪያ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አማካሪው የታክስ አሰባሰብን ማዘመን አንዱ አካል እንደሆነ ስለ አዲሱ ኤክሳይስ ታክስ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ማሻሻያው በኅብረተሰቡ ዘንድ ብዥታ እንደፈጠረ የሚታወቅ ቢሆንም የገንዘብ ሚኒስቴር ይህን ለመፍታት የተለያዩ መወያያ መድረኮችን በማዘጋጀት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታክስ ምሁር ታደሰ ሌንጮ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት አዲሱ ኤክሳይስ ታክስ በደምብ የታሰበበት አይደለም ሲሉ ጀምረው ‹‹ የፖሊሲ ጥራት ችግር አለ ›› ብለዋል። ታደሰ አያይዘውም ኤክሳይስ ታክስ የምጣኔ አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ የምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት እንደሚያመጣም ጨምረው ገልጸዋል። እንደ ታደሰ ገለጻ ኤክሳይስ ታክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሦስት ምክንያቶች ሊጣል እንደሚችል ይናገራሉ። በዚህም መሰረት የጤና ዕክል በሚያደርሱ ምርቶች ላይ፣ የቅንጦት ዕቃዎች ላይ እንዲሁም ኤክሳይስ ታክሱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የሚውል ከሆነ እና የተሰበሰበው ታክስ የሚገባበት ቋት ካለው ሊጣል እንደሚችል አብራርተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here