የፖርቲዎች ጥምረት ወደ ጥቂት ትልልቅ አማራጮች ሊደርስ ይገባል!

0
947

በሕወሐት ይመራ የነበረው ኢሕአዴግ ከውስጥና ከውጭ በገጠመው ጫና ራሱን ከቀየረና የለውጥ ኃይል በመባል የሚታወቀው ቡድን ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዳንዴ ተስፋ ሰጪ አንዳንዴ ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ ሲሆን ቆይቷል። ከውጭ የገቡትም ሆኑ በአገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ያለፉትን ኻያ ወራት እርስ በእርስ የመወነጃጀያ እና ሴራ የመጎንጎኛ ጊዜ ሲያደርጉት ቆይተዋል። የለውጡ ጊዜ እገሌ ፓርቲ በዚህ አካባቢ ከተካሔደው ደም መፋሰስ እና ከዜጎች ግጭት ጀርባ አለ የሚሉ የእርስ በእርስ ክሶች በርትተው የታዩበት ጊዜም ነው።

ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ግን የምርጫው ጊዜ እየቀረበ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ወይም የእርስ በእርስ መናቆሩን በመሰልቸትም ሊሆን ይችላል፤ ፓርቲዎች እየተቀራረቡ የመነጋገር አዝማሚያቸው እየጨመረ ሄዷል። የኃይል አሰላለፎች ባልተጠበቀ መልኩ እየተቀያየሩ መምጣታቸው ምርጫው ሲቀርብ ፓርቲዎች የመጨረሻው ዙር ላይ እንዳሉ በመረዳት ፉክክሩን እንዳጠነከሩት የሚያሳይ ነው። ከዚህ በፊት አዲስ ማለዳ በሰፊው እንደዳሰሰችው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኃይል አሰላለፎች እየተቀየሩ ይገኛሉ።

የብሔር ፖለቲካን የአገሪቱ ዋነኛ መስመር አድርጎ ወደ ፊት የጎተተው ኢሕአዴግ፣ ራሱን አክስሞ አንድ ወጥ የሆነ ብልጽግና ፓርቲ ከተባለ ከረመ። በአክቲቪስትነትና በመገናኛ ብዙኀን ባለቤትነት በኹለት ጽንፍ ቆመው የቆዩት ጃዋር መሐመድ እና እስክንድር ነጋም ወደ ፖለቲካው እንደሚቀላቀሉ በቅርቡ ገልጸው ነበር። ጃዋር መሐመድ የብልጽግና ፓርቲ መፈጠር ወደ አሃዳዊነት መንደርደር መሆኑን ገልጾ ከአዲሱ ፓርቲ ጋር ሆድና ጀርባ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

በቅርቡ እንደታዘብነው ደግሞ የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ የሆኑት፣ በእስክንድር ነጋ የሚመራው ባልደራስ እና ኢዜማ እንደማይጣጣሙ ነው። የለማ መገርሳ ጊዜያዊ ተቃውሞም በፍጥነት በሚቀያየረው የኃይል አሰላለፍ ውስጥ የታየ ለውጥ ነው። በዚህ ሳምንት እንደተሰማው ደግሞ ጃዋር የእነ መረራ ጉዲናን (ፕሮፌሰር) የኦሮሞ ፌዴራሊስት ፓርቲ ተቀላቅሏል። መረራ እና ጃዋር በአንድ ላይ ሊሠሩ ይችላሉ ብሎ የጠረጠረ በማይገኝበት አገር፣ አሰላለፉ ከዚህ የባሰ ነገር ይዞ መጥቷል።

ትናንት በተጨማሪ እንደተሰማው ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) ጥምረት ፈጥረዋል። በእነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉት ግለሰቦች ደግሞ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአንድነት ለመሥራት ያስባሉ ተብለው የማይጠበቁ ናቸው። ጃዋር መሐመድ ከኦነግ ጋር ቅራኔ ኖሮት የኖረ ሰው መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ለኦዴፓ ያደላ ይመስል የነበረ ቢሆንም፣ የብልጽግና መፈጠር ከኦነግ ጋር አብሮ መሥራትን እንዲያስብ ሳያደርገው አልቀረም። ኦነግ የበፊት አባሉ እና የአሁኑ የኦብፓ መሪ ከሆኑት ከማል ገልቹ ጋር ከፍተኛ ጠብ ኖሮት የቆየ ድርጅት ነው። እንዲያውም በነፍስ የሚፈላለጉ የሚመስሉ ነበሩ። መረራም ከሌሎቹ ብሔረተኞች ጋር አብሮ የሚሔድ አቋም ያላቸው አይመስሉም ነበር። ነገር ግን እነዚህን ልዩነት ይዘው የቆዩ ኃይሎች እና ግለሰቦች በጥምረት ለመሥራት መስማማታቸው የኃይል አሰላለፉ የቅርቡ ክስተት ነው።

የኦሮሞ ፓርቲዎቹ ጥምረት በአገር ደረጃ እየታየ ባለው የብሔርተኛ እና የዜግነት ፖለቲካ ተከታዮች ፉክክር ላይም የራሱ ተጽእኖ እንደሚኖረው ይጠበቃል። አስገራሚ የሚሆነው ነገር ብሔርተኞቹ ‹አንድነት› የሚለውን ቃል የአንድ ወገን ጉዳይ አድርገው በጥርጣሬ የሚመለከቱ ቢሆኑም፣ የተሻለ ጥንካሬ ኖሯቸው የዜግነት ካምፑን ለመብለጥ ግን በአንድነት መሥራታቸው ነው። የተለያዩ ክልሎችን በሚወክሉ ኃይሎች መካከል ሌሎች የብሔርተኞች ጥምረቶች በቅርቡ ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ጠቋሚ ምልክቶችም እየታዩ መሆኑ ደግሞ፣ የብሔርተኞቹ ካምፕ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያሳያል።

በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ሳምንት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ (ኢሀን) እና የአምስት ፓርቲዎች ውህድ የሆነው ሕብር ኢትዮጵያ ጥምረት መፍጠራቸውን ሰምተናል። ይህም አካሔድ ከላይ እንደተጠቀሰው እየተቀየረ የመጣው የኃይል አሰላለፍ ክፍል ሲሆን፣ ምናልባትም ትልልቅ ጥምረቶች መፈጠራቸው ሌሎችም ራሳቸውን ማሰባሰብ እንዳለባቸው እንዲያስቡ እያደረገ ይመስላል።

ምንም እንኳን ቀደም ብለው በውህደት እና በጥምረት ራሳቸውን ሲያጠነክሩ የቆዩት በዜግነት ፖለቲካ መስመር የተሰለፉት ቢሆኑም፣ የብሔርተኞቹ ጥምረት ጥረታቸው አሁንም በቂ እንዳልሆነ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። ይህ ዓይነቱ ሒደት ደግሞ በዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞቹ ዘንድ የተካሔዱት እንደ ኢዜማ ዓይነት ውህደቶች እና ጥምረቶች በቂ ላይሆኑ እንደሚችሉ ጥርጣሬዎችን ሊፈጥር ይችላል።

በመሆኑም ተጨማሪ ውህደቶች በዚህኛው ካምፕም ሊፈጠሩ ይችላሉ። በኔዘርላዷ ሔግ ከተማ መቀመጫውን ያደረገው የዓለም ዐቀፉ የሕገ መንግሥት የምርምር ኢንስቲትዩት አርታኢ እና በምርጫ ጉዳዮች የምሥራቅ አፍሪካ ተንታኝ የሆኑት አደም ካሴ (ዶ/ር) ኢዜማ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር መደበኛ ወይም ኢ-መደበኛ ጥምረት ሊያደርጉ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለው ያምናሉ።

የሚቻለውን ያህል ትልቅ ጥምረት መፍጠር በኹለቱም ወገኞች በኩል እየተካሔደ መሆኑን እያየን ሲሆን፣ የዚህ ሒደት መጠናከር በለውጡ የመጀመሪያ ወራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአገሪቱ ያሉት ፓርቲዎች ቁጥር መብዛትን ተንተርሶ ወደ ትላልቅ ጥቂት ጥምረቶች እንዲቀየሩ ያነሱት ሐሳብ እየተተገበረ እንደሚሔድ ይጠቁማል።

ይህም ሕዝብ ያሉትን አንኳር አንኳር የፖሊሲ አማራጮች በግልጽ እንዲያይ እድል በመስጠት ለምርጫ የተሻለ ንቃት ይፈጥራል። በመሆኑም የጥምረት እና የውህደት እርምጃው የአገሪቱን ፖለቲካ ሊያሻሽለው እንደሚችል አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ያላቸውን ልዩነቶች ወደ ጎን አድርገው በጥምረት ለመሥራት መነሳታቸው ከአገራችን የፖለቲካ ባህል አንጻር የተሻለ እርምጃ ነው። የፓርቲዎቹ በጥምረት መሥራት ደጋፊዎቻቸው በጠላትነት እንዳይተያዩ ከማድረግ አልፎ የአንድነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ ሰላማዊ የምርጫ ድባብ እንዲፈጠር ይረዳል።

መጠላለፍ ብዙ ችግር ያየንበት ፖለቲካ አሁን ፓርቲዎች አብረው በመሆን የሚጣመሩበት ምዕራፍ ላይ መግባቱ የሚያበረታታ ነው። እንደዚህ ዓይነት እርምጃዎች ቀና በመሆናቸው ዜጎች ለወደፊት ጥሩ ነገር ሊመጣ እንደሚችል ተስፋ እንዲያደርጉ ያግዛሉ። በመሆኑም በጋራ በሚሠሩበት ጊዜ ወደ ኋላ በመመልከት የወደፊቱን የሕዝብ ተስፋ እንዳያጨልሙ በሒደቱ ውስጥ የተሳተፉት ኃይሎች ሊያስቡበት ይገባል። የግለሰብ ፍላጎቶች ከሕዝብ ፍላጎት እየጎሉ የኹለት ፖለቲከኞች ጠብ የሕዝብ ክፍፍል ሆኖ እንዳይዳብር ታትሮ መሥራት ያስፈልጋል።

ሌላ ሊስተዋል የሚገባው ጉዳይ ደግሞ በአንድ ጥምረት ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች የፖሊሲ ልዩነታቸውን እንደጠበቁ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ ጥምረቶቹ ሲፈጠሩ ልዩነቶቹ አነስተኛ በሆኑት መካከል ቢሆን የተሻለ መሆኑ ነው። የተራራቁ የፖሊሲ መስመሮችን የሚከተሉ ፓርቲዎች፣ ጥምረታቸውን ለማስቀጠል ማለፍ ያለባቸው ተግዳሮቶች ከፍተኛ ይሆናሉ። በአንጻሩ ደግሞ አነስተኛ የፖሊሲ ልዩነት ያላቸው ፓርቲዎች ከጥምረት ወደ ውህደት ከፍ የማለት እድላቸው የሰፋ ይሆናል። በመሆኑም ምርጫው ደረሰ በሚል ችኮላ ተሯሩጦ መሰባሰቡ ከምርጫው ማግስት ውጤቱ ምንም ይሁን ምን፣ አብሮ ረጅም መንገድ መሔድ የማያስችል ስለሚሆን እርምጃውን ሰከን ብሎ ማሰብ ያዋጣል።

ለሴቶች እኩልነት የምትታገለውና በሴት አንቀጽ የምትጠራው አዲስ ማለዳ፣ ከዚህ አጠቃላይ ሒደት ሌላ የታዘበችው ነገር ቢኖር አሁንም የአገሪቷ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ቦታ የሚሰጡት እንዳልሆነ ነው። የኦነግ፣ ኦፌኮ እና ኦብፓ ጥምረትንም ሆነ የአዴፓ፣ ኢሀን እና ሕብር ኢትዮጵያን ጥምረት ያበሰሩት የፓርቲ መሪዎች፣ ሙሉ በሙሉ ወንዶች ሲሆኑ አንድም ሴት ያለመታየቱ ግማሽ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደተዘነጋ የሚጠቁም ነው። ይህም ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ አዝማሚያ ከመሆኑም በተጨማሪ ነባር ችግሮች እንደሚቀጥሉ ጠቋሚ ነው ስትል አዲስ ማለዳ በማሳሰብ ስጋቷን ትገልጻለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here