ኮኬይን በሆዱ ይዞ የተገኘው ናይጄሪያዊ በእሥራት ተቀጣ

0
679

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሆዱ ኮኬይን የተሰኘ አደገኛ ዕፅ ይዞ በተገኘው ናይጄሪያዊ ግለሰብ ላይ የጽኑ እሥራትና ገንዘብ መቀጮ ፍርድ በየነ።
ግለሰቡ የወንጅል ሕግ አንቀጽ 525 (1ለ) ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ ልዩ ፍቃድ ሳይኖረው እንዳይዘዋወርና በጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከለ ዕፅ ይዞ በመገኙቱ በጽኑ እሥራትና ገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
ሚስተር ኢማኑኤል መስከረም 6/2011 ከብራዚል ሳኦፖሎ ወደ ናይጀሪያ ሌጎስ ለመሄድ በመጓዝ ላይ እያለ በቦሌ ዓለም ዐቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመሸጋገሪያ (‹ትራንዚት›) ባረፈበት ወቅት ነበር የተያዘው። የአደገኛ ዕፅ ክትትልና ቁጥጥር ሠራተኞች ፍተሻ በሚያካሂዱበት ጊዜም በሆዱ ውስጥ ሰላሳ አምስት ጥቅል የኮኬይን ዕፅ ተገኝቶበታል። በፌዴራል ፖሊስ በምርመራ ላይ በነበረበት ወቅትም ተጨማሪ ሰላሳ ሦስት ፍሬ ከሆዱ የወጣ በመሆኑ ተከሳሽ በአጠቃላይ 68 ጥቅል ፍሬ ወይም አንድ ነጥብ ሶስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮኬይን የተባለ አደገኛ ዕፅ በሆዱ ይዞ መገኘቱ ተረጋግጧል።
በመሆኑም መርዛማ ዕፆችን ይዞ በመገኘትና በማዘዋወር ወንጅል ተከሶ ፍርድ ቤት መቅረቡን የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘገባ ያስረዳል።
ተከሳሹ ጥፋተኛነቱን አምኖ አባቱ መሞታቸውን በመጥቀስ ቤተሰቦቹን በገንዘብ ለመርዳት ሲል ድርጊቱን መፈፀሙን ተናግሯል። የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ ወንጀል ችሎት በኅዳር 13/2011 በዋለው ችሎት በሰባት ዓመት ጽኑ እሥራትና በሰባት ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ አንዲቀጣ ወስኖበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here