የኦብነግ አመራሮች ዛሬ ወደ አገር ቤት ይገባሉ

0
743

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) አመራሮች ዛሬ ኅዳር 22/2011 ወደ አገር ቤት እንደሚገቡ ይጠበቃል።
ባለፈው ወር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የሚመራ ልዑክ ወደ ኤርትራ በማምራት ከግንባሩ ጋር ባደረገው ድርድር ግንባሩ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ሠላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሰቸው ይታወሳል። ይሁንና ስምምነቱ ‹በሱማሌ ክልል የኢትዮጵያ አካል ሆኖ መቀጠል አለመቀጠል ጉዳይ ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲከሄድ የሚል መግባባትንም› አካቷል መባሉን ተከትሎ በወቅቱ ውዝግብ ማስነሳቱ ይታወሳል። ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ሕዝበ ውሳኔ የሚለው ጉዳይ ስህተት መሆኑን ማስተባበያም ተሰጥቷል።
ዛሬ የግንባሩ ሊቀመንበር መሐመድ ኦማርን ጨምሮ ከ20 በላይ ከፍተኛ አመራሮች አገር ቤት እንደሚገቡ ግንባሩ አስታውቋል። ባለፈው ሳምንትም የኦብነግ ሠራዊት አባላት ትጥቃቸውን በመፍታት ከአስመራ ወደ ጅግጅጋ መግባታቸው ታውቋል።
ኦብነግ በአውሮፓዊያኑ 1984 የተመሠረተ የፖለቲካ ድርጅት ሲሆን ከወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስኪሰረዝ ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት በሽብርተኝነት ተፈርጆ ቆይቷል። ከሽብርተኝነት መዝገብ ከተሰረዘ በኋላም ኦብነግ ተኩስ አቁም አውጇል።
የግንባሩ ቃል አቀባይ ከወራት በፊት እንዳሳወቁት ኦብነግ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ እንደሚጠይቅ ለብሉምበርግ የዜና አውታር መግለፃቸው ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here