የዩኒቨርሲቲዎች የእርምጃ ሳምንት

0
439

በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን በሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሰላማዊ መማር ማስተማር ሒደት የቅርብ ጊዜ ትውስታቸው ረዘም ሲልም እንደ ‹‹ደጉ›› ጊዜ የሚተርኩት ሆኖባቸው ከርመዋል። ከተወሰኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውጭ ኹሉም ጊቢዎች ሰላማቸው ከመደፍረሱ የተነሳ ተማሪዎች አገር አማን ብለው ለትምህርት ከወላጅ ጉያ ወጥተው በሔዱበት ተጎድተዋል፣ አካላቸው ጎሏል፣ ባስ ሲልም ውድ ሕይወታቸውን አጥተው ለወላጅ ሰቀቀን፣ ለሰሚው ድንጋጤን ፈጥሮ አልፏል፤ ያላለፈባቸውም እንዳሉ ሁሉ።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚቃጣውን ትንኮሳ እና ሰላም የማደፍረስ ተግባር የዩኒቨርሲቲዎቹ የሥራ ኃላፊዎች ችላ ማለት ከአንዱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ወደ ሌላው እንደ ሰደድ እሳት ለተዛመተው ችግር ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ሐሳባቸውን ሲሰነዝሩ ሰንብተዋል። ይሁን እንጂ በተለይ ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎች ለፖለቲካ መጠቀሚያ መሆናቸው ሳያንስ፣ ምንም የማያውቁ ተማሪዎች ባላወቁት ሁኔታ ሕይወታቸው ሲቀጠፍ መንግሥት ድርሻው ምንድነው? እስከመቼ ድረስስ ነው ትዕግስቱን የሚያሳየው? ሲሉ የተደመጡ እና የመንግሥት ሆደ ሰፊነት አምርረው የተቃወሙ ከፍ ሲልም መንግሥት አልባ እየሆንን ይሆን እንዴ? እስከማለት የደረሱበት ጊዜ ነበር።

ከእነዚህ ውጣ ውረዶች፣ በተለይም ደግሞ አልፎ አልፎ ኮሽ እያሉ የተማሪዎችን ሕይወት ቀጥፈው ከሚከስሙ ግጭቶት በኋላ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተለይም ደግሞ ግጭቶች በስፋት የተስተዋለባቸው ጊቢዎች ከግጭቱ ጋር ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ግንኙነት አላቸው ያሏቸውን የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰቦች፣ ተማሪዎችን ጨምረው ከሥራ እና ከትምህርት አግደዋል። በዚህም መሰረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ 176 ተማሪዎች ከ1 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ከትምህርት ገበታ መታገዳቸውን የኹሉንም ዩኒቨርስቲዎች ቁጥር ጠቅሶ ይፋ አድርጓል።

በዚህ ብቻ ሳይወሰን የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችም በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻቸው በግጭቶች ላይ ተሳትፎ አሏቸው ያሏቸውን ግለሰቦች አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ መውሰዳቸውን ያስታወቁበት ሳምንት ነበር። ይሁን እንጂ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች በቂ አይደለም በሚል አመክንዮ የሰው ነብስ ጠፍቶ እንዴት በአስተዳደራዊ እርምጃ ብቻ ይታለፋል? በሚል፣ ተስፋ መቁረጣቸውን አስተጋብተዋል።
በሌላ ጽንፍ ያሉት ደግሞ፣ ‹የለም መንግሥት ራሱ መጠየቅ ይኖርበታል፤ ምክንያቱ ደግሞ በእንጭጩ መግታት እየቻለ እንዴት ይህን ያህል ስር ሲሰድ ዝም ብሎ ይታዘባል›› የሚሉ እና የተወሰደው እርምጃ መወሰድ ካለበት ዩኒቨርስቲዎችን በሚያስተዳድረው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ነው ሲሉም ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። ሳምንቱ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዕርምጃ የጦፈ ክርክር የተደመጠበት እንዲሁም በርከት ያሉ ጎራዎችም የተከፈሩበት እና ሐሳብ የተሰናዘሩበት ሳምንት ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here