ለሰዎች እና ለእንስሳት ምግብ የሚሆኑ 23 የቀርከሃ ዝርያዎችን ማባዛት ተጀመረ

0
1042

የኢትዮጵያ የአካባቢ እና ደን ልማት ኢንስቲትዩት 21 አዳዲስ የቀርከሃ ዝርያዎችን ከኤስያ እና ከደቡብ አሜሪካ በማስገባት ለሰዎች ምግብ እንዲሁም ለእንስሳትን መኖ እስከ 65 በመቶ ለመሸፈን ሥራ ጀመረ።
ከ 800 እስከ 1 ሺሕ 800 ሜትር ከፍታ መሀል ባለው ክፍተት መብቀል የሚችሉት ዝርያዎቹ፣ ከአጠቃላይ ክብደታቸው 20 በመቶ የሚሆነው ለእንስሳት መኖ መዋል የሚችል ቅጠል መሆኑ እና በውስጡም ፕሮድ (prode) የተሰኘ ፕሮቲን እንዳላቸው ተገልጿል።
ለእንስሳት ከሚቀርበው መኖ ውስጥም 65 በመቶ የሚሆነውን በእነዚህ የቀርከሃ ቅጠሎች በመተካት 33 በመቶ የሚሆነውን ከፋጉሎ እና ፈሩሽካ ጋር በመቀላቀል በአርሲ አርቲ በተሰኙ በጎች ላይ ሙከራና ጥናት ተደርጓል። በዚህ ጥናት መሠረት በእያንዳንዱ በግ እስከ አምስት ኪሎ ግራም የሚደርስ ተጨባጭ ለውጥ ማግኘት መቻሉን የአካባቢ እና ደን ልማት ኢንስቲትዩት የቀርክሃ አያያዝ ከፍተኛ ተመራማሪ ይጋረዱ ሙላቱ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
ከእንስሳት በተጨማሪ ቀርከሃ ለሰዎችም ለምግብነት መዋል ይችላል ያሉት ይጋረዱ፣ በዓለም ላይ ካለው የቀርከሃ የገበያ ስርዓት ውስጥ 13 በመቶ የሚሆነውን ከቀርክሃ የሚዘጋጁ የምግብ ውጤቶች እንደሚይዙ ገልጸዋል። ለምግብነት የሚውል ቀርከሃን ማምረትም የራሱ የሆነ ቅድመ ዝግጅት የሚጠይቅ እና ኅብረተሰቡን ማሳመን የሚያስፈልገው መሆኑንም ተናግረዋል።
አዳዲሶቹንም ዝርያዎች በ አዊ ዞን እና በጅማ አንዳንድ አካባቢዎች ለአርሶ አደሮች በማከፋፈል በማሳያ ደረጃ እንዲበቅሉ እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።
ቀርከሃ ከሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ጊዜያት ከመሬት በታች ሌሎች ግንዶችን የሚያበቅሉ እንቡጦች (shoots) ያበቅላል። አንድ መቶ ግራም የሚመዝን እንቡጥም በውስጡ 16 ሚሊ ግራም ፖታሺየም፣ 887 ፖታሺየም እና እስከ 31 በመቶ የሚደርስ የፕሮቲን ይዘት አለው። ቀርከሃን በስፋት ማምረት ቢቻል በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ሊያግዝ ይችላል ተብሏል።
ከነሐሴ እስከ መስከረም ባሉት ወራት፣ ቀርከሃ ሌሎች ግንዶችን ለማብቀል የሚጠቅም እንቡጦችን ያበቅላል ያሉት ተመራማሪዋ፣ እነዚህ እንቡጦች ከ 25 ሳንቲ ሜትር በላይ በሚያድጉበት ጊዜ ለምግብነት መዋል ይችላሉ ሲሉ አብራርተዋል። በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች ቀርከሃ ለምግብነት እንደሚውል ገልፀው፣ በቤኔሻንጉል እና በርታ ማኅበረሰብ ዘንድ የቀርከሃ እነዚህን እንቡጦች በውሃ በመዘፍዘፍ እና በማብሰል ለምግብነት የማዋል ልምድ አለ ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኹለት ዓይነት የቀርከሃ ዝርያዎች የሚበቅሉ ሲሆን፣ ከ 800 እስከ 1800 ሜትር ከባህር ክፍታ በላይ የሚበቅለው የዎላ ቀርክሃ እንዲሁም ከ 2400 እስከ 3500 ሜትር ላይ የሚበቅለው የደጋ ቀርከሃ ናቸው።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ በቀርከሃ የተሸፈነ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ደን ሲኖር፣ የቀርከሃ ግንድ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን ለማምረት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። ሆኖም አብዛኛው ምርት በቤት ውስጥ የሚመረት በመሆኑ የጥራት እና የተደራሽነት ችግር ማነቆ አንደሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ። የቤት ውስጥ መገልገያዎችን የሚያመርቱ ዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች የምርት ግብዓት የሆነውን የቀርከሃ ግንድ እንደልብ ማግኘት ሲሳናቸው፣ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ቀርከሃ አዋጭ አይደለም በሚል በሌሎች ዛፎች እየተኩት እንደሚገኝም ጥናቶች ያመላክታሉ።
ቀርከሃ በስፋት በሚበቅልባቸው አካባቢዎች ያሉ የሌሎች እፅዋት ደኖች እስከ አሁን ተጠብቀው የቆዩት ቀርከሃ ከማገዶነት አንስቶ ቤት ውስጥ መገልገያ መሣሪያዎችን ለማምረት፣ እንዲሁም ለግንባታ በመዋሉ መሆኑን እና የደን ሽፋንን እንደተጠበቀ ለማቆየት ያስችላል ተብሏል።
የቀርከሃ አንዱ አጠና በእድገቱ ቁመቱንና ውፍረቱን ለመጨረስ የሚወስድበት ጊዜ ሦስት ወራት ብቻ ነው። ከ3 እስከ 4 ዓመታት ድረስ ጥንካሬውን እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን፣ ይህ ሂደት በየዓመቱ በዝናብ ወቅት አዳዲስ እንቡጥ በማውጣት የሚቀጥል የሥነ-ሕይወት ዑደት ነው። በየዓመቱ ቢያንስ በሄክታር እስከ 4000 አዳዲስ እንቡጦች ይወለዳሉ። ቀርከሃ ወረቀት፣ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ እንዲሁም ሌሎች ምርቶች ማስገኘት የሚችል ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሌሎችም ደጋማ አካባቢዎች በስፋት ይበቅላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here