የደኅንነቱ መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች እርምጃ ይውሰዱ፣ ይቅርታም ይጠይቁ!

0
972

በየሳምንቱ ሰኞ ምሽት በትግራይ ቲቪ የሚተላለፈው ‹‹ኢትዮ ፎረም›› የተሰኘው ፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢ የሆኑት ያዬሰው ሽመልስ አርብ ታኅሳስ 24/2012 ከቦሌ ዓለማቀፍ አየር ማረፊያ ወደ መቀሌ ለመጓዝ በመሰናዳት ላይ ሳሉ በፀጥታ ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበረ በማኅበራዊ ገፃቸው መግለፃቸው ይታወሳል።
ይህ ከመሆኑ በፊትም የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ በስልክ ደውለው ወደ ቢሮአቸው እንደጠሯቸው ጠቅሰው በተመሳሳይ በማኅበራዊ ገፃቸው ላይ አስፍረውም ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት፣ ወደ ፊት ከመጣ በኋላ እንብዛም ታይቶ የማይታወቅ እንግዳ የሆነ ድርጊት መሆኑን ተከትሎ እና የተፈጠሩት ድርጊቶች ተያያዥነት እንዲሁም ከግለሰቡ ሞያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማወቅም አዲስ ማለዳ የተወሰኑ ጥረቶችን አድርጋለች።
አዲስ ማለዳ በስልክ ያነጋገረቻቸው ያየሰው እንደሚሉት፣ ወደ መቀሌ ለመሄድ ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ ካቀኑ በኋላ ወደ አውሮፕላን ለመግባት የሚደረገው መጨረሻ የፍተሻ ነጥብ ጋር ሲደርሱ ነበር ተለይተው እንዲቀመጡ ጥያቄ የቀረበላቸው። በአካባቢው የሚገኝ ወንበር ላይ የተወሰነ ከተቀመጡ በኋላ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት መሥሪያ ቤት ባልደረቦች ‹‹ከዚህ ውጣ›› በሚል ከአየር መንገዱ ተርሚናል አጅበው እንዳስወጧቸውም ይናገራሉ።
ወደ መቀሌ እንዲሄዱ እንዳልተፈለገ ተገልፆ ከተረሚናል ያስወጧቸው የደኅንነት ባልደረባ ሲመለሱም፣ ኹለት የደኅንነት ሰዎች እንዲሁም አንድ የደንብ ልብስ የለበሱ የፌዴራል ፖሊስ ሆነው እንደተቀበሏቸው እና አንድ ወንበር ያለበት ክፍል ውስጥ እንዳስገቧቸውም ያዬሰው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹በአጠቃላይ ከ11 ሰዓት ተኩል እስከ ኹለት ሰዓት ተኩል በአየር ማረፊያው ውስጥ ቆይቻለሁ›› ያሉት ያዬሰው፣ ከዚህ ውስጥ የተወሰነውን በዚህ ጠባብ ክፍል ቀጥሎም የሰሌዳ ቁጥር የሌለው ቶዮታ ራቫ ፎር መኪና ውስጥ ማሳለፋቸውን ጠቅሰዋል።
‹‹የቺቺኒያ ስድቦችን ለረጅም ሰዓታት ስሰደብ ነበር›› ያሉት ያዬሰው፣ ከዚህ ውጪ ግን ምንም አይነት ምርመራም ሆነ ሕጋዊ ጥያቄዎች እንዳልቀረቡባቸው ተናግረዋል። አንድ መጽሐፍ እና መድኀኒት ተወስዶባቸው እስከ አሁንም እንዳልተመለሰላቸው እና ስልካቸውም ከኹለት ቀን ቆይታ በኋላ መመለሱን ተናግረዋል።
በመሻሻል ሂደት ላይ የሚገኘው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ተቋሙን በድጋሚ የሚያቋቁመው አዋጅ፣ በጋዜጠኞች እና በፖለቲካ ፓርቲዎች ስለላን እስከማስቀረት የሚደርስ እና መሥሪያ ቤቱ ለዘመናት ሲተችበት የነበረውን አፈና ያሻሽላል የሚል ተስፋ የተጣለበት ነበር።
አዲሱ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የመረጃ መሥሪያ ቤቱ አንድም ሰው በቁጥጥር ስር አውሎ አያውቅም በሚል በተደጋጋሚ በተለያዩ ባለሥልጣናት ሲነገር ቆይቷል። ከዛም አልፎ በሕዝቡም ዘንድ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱን እንደ ከፍተኛ የሽብር እና የጭንቀት ምንጭ አድርጎ ማየት የተሻሻለበት ነበር ቢባልም ማጋነን አይሆንም።
መሥሪያ ቤቱ ዋና ሚናው ለአገር ደኅንነት የሚያሰጉ መረጃዎችን ለፖሊስ እና ለሌሎች ለሚለከታቸው የመንግሥት አካላት አሳልፎ በመስጠት እርምጃ እንዲወስድ ማድረግ መሆን አለበት። ከዛ ባሻገር ግን ያለሥልጣኑ የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት መገደብ መጀመሩ ብዙ ከተባለለት የሰብአዊ መብት አያያዝ አንፃር አስደንጋጭ እና አሳሳቢ ያደርገዋል። ይህ ድርጊት ደግሞ በጋዜጠኝነት ሞያ ላይ ባሉ ዜጎች ላይ ሲሆን ደግሞ ጉዳቱ ከግለሰብ አልፎ እንደ አገር የቀደመውን የፍርሃት እና የጭቆና ስርአትን በድጋሚ የሚመልስ ይሆናል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በተለያዩ ዘርፎች ካካሄዳቸው ማሻሻያዎች በግንባር ቀደምነት በሚዲያው ዘርፍ የተደረገው ማሻሻያ እውነተኛ የሚባሉ የተለያዩ መሻሻሎችን ያየነበት ነው። እንዲሁም በአኅጉረ አፍሪካ ጋዜጠኞቿን በማሰር በግንባር ቀደምነተነት ከሚነሱ አገራት ተርታ የነበረቸውን ኢትዮጵያን ለሞያው የተሻለች ሜዳ ያደረገም ነው።
በመካከለኛው እና በስረኛው የሥልጣን እርከን ላይ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣኖች፣ ጋዜጠኞችን ያለአግባብ የማሰር ድርጊት ሲፈፅሙም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች በአስተዳደራቸው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ችግሩ በአፋጣኝ እንዲቀረፍ እና በኋላም ይቅርታቸውንም በማቅረብ ያሳዩት አለኝታነት ተስፋ ሰጪ ነበር።
እነዚህ መልካም አጋጣሚዎች የተለያዩ ዓይነት ጭቆናዎች ሲደርስበት፣ ከዓለም ጭራ ከጎረቤት አገሮች ኋለኛ ለሆነው ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ መሻሻል ተስፋ የሚሰጥ ነበር። ነጋዴው ገንዘቡን ለማፍሰስ እንደጦር ከሩቁ የሚሸሸው፣ ዛሬ መሥራቱን እንጂ ነገ መቀጠሉን እርግጠኛ በማይኮንበት፣ ብሎም ማስታወቂያ ለመስጠት እንኳን የጋዜጣው ፖለቲካዊ አቋም እስከ መንግሥት ሊያመጣ የሚችለው ዱላን ተሸሽቶ ተገልሎ ለቆየው ኢንዱስትሪ፣ የታየው የነፃነት ጭላንጭል አስደሳችም ነው። በመሻሻል ላይ የሚገኘው የመገናኛ ብዙኀን አዋጅም፣ አዋጁን በበጎ ፈቃደኝነት ካረቀቁት የሕግ እና የሚዲያው ባለሞያዎች ጀምሮ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን እና ሌሎች አጋሮቹን የሚያስመሰግን ነው።
አገር በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ከየፅንፉ እየተጎተተች በጭንቅ ላይ በላችበት ጊዜም፣ ሚድያው ከተለመደው የይዘት ጥንቃቄ ላቅ ባለ መልኩ በኃላፊነት መሥራት እንዳለበት የምታምነው አዲስ ማለዳ፣ ይህንን የማያደርግ የሚድያ ተቋም ሲኖር ይህንን የሚከታተለው የብሮድካስት ባለሥልጣን ነገሮች ሳይደባባሱ ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል።
ነገር ግን እነዚህ ጥረቶች ሁሉ ወደኋላ በመጎተት ሚዲያው ያሉበትን ጉድለቶች ለማሟላት እየጣረ እና አራተኛ መንግሥት ሆኖ ለመቀጠል እየተፍጨረጨረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ያለፈውን ስርዓት አካሄዶች በመጎተት በድጋሚ ለመጫን የሚሞክር ማንኛውም የመንግሥት አካል ችላ ሊባል አይገባውም።
በያዬሰው ላይ የደረሰው ትንኮሳም ይህንኑ የሚያሳይ እና ካደረ የማይቆረጠም ባቄላ ነው። ጋዜጠኛው በጋዜጠኝነት ሥራቸው የሥነምግባር ጉድለት ቢገኝባቸው እንኳ፣ በብሮድካስት ባለሥልጣን እርሳቸውም ሆኑ የአየር ሰዓት ሰጥቶ የሚያሠራቸውን ተቋም መጠየቅ የሚያስችል የሕግ አግባብ አለ። ለአገር ደኅንነት አስጊ የሆነ ድርጊት ላይም ተሳትፈዋል ብሎ ያመነ አካል፣ ማስረጃውን አሰባስቦ ለፖሊስ ሲልም ለዐቃቤ ሕግ በመስጠት ግለሰቡ በሕግ አግባብ ተጠይቀው በሕግ አግባብ የሚመልሱበት ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ የተገለገልንበት የወንጀል ሕግ ስርአት አለ።
ይህንን ሁሉ ወደ ጎን በመተው፣ የግለሰቦችን የመንቀሳቀስ መብት በመገደብ፣ አላስፈላጊ ስደብ እና ማዋረድ ማድረስ እንዲሁም የግል ንብረቶችን ከሕግ ውጪ በሆነ አግባብ መውሰድ እና መበርበርን አዲስ ማለዳ በፅኑ ታወግዘዋለች።
በግንባታ ላይ ያለውን አዲስ የዴሞክራሲ ምህዳር የሚያጠብ እና የኃይል አማራጭ በእጃቸው ላይ ያሉ የመንግሥት አካላት የሚጨቁኑት የመገናኛ ብዙኀንን መፍጠር በትውልድ ንቃተ ህሊና፣ በኢኮኖሚ እድገት፣ በፍትህ አሰጣጥ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገታችን ላይ ያመጣው መዛባት እና ኋላ ቀርነት ሊደገም የሚገባ አይደለም።
የሚዲያ ተቋማትም እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ሲፈፀሙ ዝምታን መምረጣቸው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች በማናለብኝነት ፈላጭ ቆራጭ እንዲሆኑ እድል የሚሰጥ ከመሆኑ በላይ፣ የራሱን መብት ማስከበር ያልቻለ ዘርፍ ለሌላው እንደ አራተኛ መንግሥት ሆኖ ያገለግላል ማለት ዘበት ነው።
ከዚህ ቀደም የነበረው እና የመንግሥት ደጋፊ እና ተቃዋሚ በሚል በሚዲያ ተቋማት መካከል ተገንብቶ የቆየውን ክፍፍል አሽቀንጥሮ በመጣል፣ በእንዲህ ዓይነት ወቅቶች በጋራ በመቆም በኢንዱስትሪአችን ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን መመከት አለብን። የጋዜጠኞች የሙያ ማኅበራት እና የሚድያ ባለቤቶች መማክርትም በዋናነት የሚድያዎቹ እስትንፋስ የሆኑት ጋዜጠኞቻቸውን የመጠበቅ እና መብታቸው ተጥሶም ሲገኝ በይፋ በማውገዝ በጋራ የመቆም ባህልን ማዳበር ይገባናል።
አዲስ ማለዳም ይህንን ድርጊት የፈፀሙ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ባልደረቦች ለፈጸሙት ድርጊት ሊጠየቁ እና የአገርን ደኅንነት እንዲጠብቅ አመኔታ የተጣለበት መሥሪያ ቤቱም እርምጃ ሊወስድባቸው ይገባል ብላ ታምናለች።
ከዚህ ባሻገርም የመሥሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች በይፋ ለተፈጠረው ድርጊት ይቅርታ ጠይቀው ከዚህ በኋላም ከሕግ አግባብ ውጪ ዜጎችን የሚያጉላላ፣ ዴሞክራሲን በአምባገነንነት የሚለውጥ፣ ፍትህን የሚያጓድል እንጂ በሕግ የማይገዛ ከሆነ አገር ከመጠበቅ ይልቅ፣ የማጎሳቆል ሚናው ተመልሶ መምጣቱ አይቀሬ ስለሚሆን ሳይቃጠል በቅጠል ሊባል ይገባል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here