የትግራይ ክልል የምግብ ዋጋ ግሽበት 23 በመቶ ደረሰ

0
409

ግሽበቱ ካለፈው ዓመት የአስር በመቶ ጭማሪ አሳይቷል

የትግራይ ክልል የምግብ ዋጋ ግሽበት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር እስከ አስር በመቶ የሚደረስ ጭማሪ ማስመዝገቡን የብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ዘገባ አመላከተ።
ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ግብዓቶች ላይ በክልሉ የተስተዋለው የግሽበት መጠን በ2011 ከነበረበት የ 13 በመቶ የአስር በመቶ ጭማሪ በማድረግ አሁን 23 ከመቶ ላይ እንደሚገኝ የባንኩ ዓመታዊ ዘገባ ያስረዳል። አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ በትግራይ ክልል ባለፈው ዓመት 13.9 በመቶ ላይ የነበረ ሲሆን፣ አሁን 19.8 በመቶ ላይ ደርሶ ይገኛል።
ምግብን ጨምሮ አልኮል አልባ መጠጦች ላይ የዋጋ ግሽበት በድሬዳዋ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ ክልሎች ከፍ ብሎ የተስተዋለ ሲሆን፣ የክልሎች አማካኝ የግሽበት መጠን 11.2 በመቶ ላይ እንደደረሰ ታውቋል። በመዲናዋ አዲስ አባባ የምግብ ዋጋ ግሽበት መጠን እስከ ተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ድረስ 15 በመቶ ላይ ይገኛል።
ከሁሉም ክልሎች ከፍተኛው ነው የተባለለት የትግራይ ክልል 23 በመቶ የግሽበት መጠን፣ ከባለፈው ዓመት 13 በመቶ ምጣኔ ላይ የአስር በመቶ ጭማሪ ተስተውሏል ያለው ሪፖርቱ፣ በደቡብ ክልል የተመዘገበው 9 በመቶ የግሽበት መጠን ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ እንደሆነ አመላክቷል።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል የድኀረ ምረቃ መረሃ ግብር አስተባባሪ ምዑዝ ሀዲሽ (ዶ/ር)፣ የዋጋ ግሽበት ማለት የሸቀጦች እና የአገልግሎት ዋጋ በማያቋርጥ መልኩ መጨመርን የሚያመለክት ነው ብለዋል። ለዚህ ዋና ዋና ምክንያቶቹም የፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠን እንዲሁም ምርቶችን ለማምረት የሚያገለግሉ ጥሬ እቃዎች መወደድ እና የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም መሆናቸውን ገልፀዋል።
የዋጋ ግሽበቱ እንደ አገር የተከሰተ ነው ያሉ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል ከመሠረታዊ ሸቀጦች ጀምሮ እስከ ግንባታ ጥሬ ዕቃዎች ከሌሎች ክልሎች የሚያስገባ እንደሆነ ገልፀዋል። እንደ ዘይት እና ስኳር ያሉ መንግሥት በድጎማ የሚያቀርባቸው መሠረታዊ ሸቀጦች፣ በመንገድ ላይ በሚፈጠሩ ችግሮች ወደ ክልሉ በሚፈለገው ደረጃ መድረስ አለመቻላቸው የዋጋ ግሽበቱ ከፍ እንዲል አድርጎታል ብለዋል።
ነጋዴዎች አግባብ ያልሆነ ጭማሪ ያደርጋሉ፣ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በሸቀጦች ላይ ጭማሪ ለማድረግ የሚያበቃ ምክንያት ሳይኖር የንግድ ሴራ በማድረግ ሸቀጦች ላይ ያለ አግባብ የሆነ ጭማሪ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው ኤክሳይስ ታክስ እንዲሁም ከዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጀት ለሚገኘው ብድር እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠው ተለዋዋጭ የውጪ ምንዛሬ ተመን አሰራር፣ የብርን ዋጋ እና የመግዛት አቅም በመቀነስ ግሽበት እንዲባባስ ያደርጋል። ምዑዝ በዚህ ላይ ሲያክሉ፣ አሁን በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ያለው አጀንዳ ፖለቲካ እንጂ ኢኮኖሚን እና የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ፍላጎት የሌለው ነው ሲሉ ገልፀዋል።
የዋጋ ግሽበት በሚከሰትበት ወቅት ኅብረተሰቡ ሙሉ ገቢውን ለመሠረታዊ ሸቀጦች ያውላል። ይህም ኅብረተሰቡ እንዳይቆጥብ ያደርጋል። በተዘዋዋሪም የባንኮችን ተንቀሳቃሽ እና ተቀማጭ ካፒታል በመጉዳት ኢንቨስትመንት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የራሱ የሆነ ጫና እንደሚያሳድር አብራርተዋል።
የዋጋ ግሽበት የእያንዳንዱን ዜጋ በር የሚያንኳኳ ነው። ኅብረተሰቡ ፍላጎቱን ማሟላት ሲሳነው በክልሉም ሆነ በፌደራል መንግሥት ላይ ያለው እምነት ይሸረሸራል። ይህም ለአመፅ ሊያነሳሳ እንደሚችል አንስተዋል።
እንደ መፍትሔም መንግሥት ወጪውን መቀነስ ይገባዋል ያሉት ምዑዝ፣ ወጪ ቅነሳው ግን አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዳይሠሩ የሚያደርግ መሆን የለበትም ብለዋል። የመንግሥት ፕሮጀክቶች ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ በመሆናቸው የወጪ ቅነሳው በትኩረት ሊታይ እንደሚገባውም አሳስበዋል።
መንግሥት በሰዎች እጅ ላይ ያለውን ገንዘብ ለመሰብሰብ የቦንድ ሽያጭ ማከናወን አለበት። እንዲሁም የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን እና ምርታማነቱን መጨመር የሚሉት ጉዳዮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በትኩረት ሊታዩ ይጋባቸዋል ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የትግራይ ክልል የሥራ ኃላፊዎችን በስልክ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here