ሜቴክ 6 ቢሊየን ብር ቀረጥና ታክስ እንዲከፍል ተጠየቀ

0
642

በተለምዶ ሜቴክ ተብሎ የሚጠራው የብረታ ብረት ኢንጅነሪነግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ) ስድስት ቢሊየን ብር ወዝፍ ቀረጥና ታክስ እንዲከፍል በገቢዎች ሚኒስቴር መጠየቁን አዲስ ማለዳ ከተለያዩ ምንጮች አረጋገጠች።
ኮርፖሬሽኑ ለባለፉት ዓመታት በአራት የጉምሩክ ጽሕፈት ቤቶች በተለያዩ ጊዜያት ላስገባቸው ቁሳቁሶች የሚጠበቅበትን ቀረጥና ታክስ በሚገባ አለመክፈሉ ታውቋል።
በቀድሞው ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ሚንስቴር ባገኘው ፍቃድ መሠረት ኮርፖሬሽኑ ለሦስት ዓመታት ያህል ከቀረጥ ነፃ ካስገባ በኋላ የተሰጠውን መብት ቢነጠቅም ኮርፖሬሽኑ የተጠየቀውን ቀረጥና ታክስ ለሚያስገባቸው ዕቃዎች መክፈል አልቻለም ሲሉ የጉምሩክ ኮሚሽን ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አብዱልከሪም አደም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዕቅድ ያለመሳካት ያልተሰበሰቡ ወዝፍ ቀረጥና ታክስ ገቢዎች እንደምክንያት በተለያየ ጊዜ መጠቀሱ አይዘነጋም።
ባለፈው ዓመት የታተመ የኦዲተር ጄኔራል ሪፖርት እንደሚያሳየው በ2009 ብቻ በቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤትና በሥሩ ባሉት ዐሥራ ሰባት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች 1.5 ቢሊየን ብር በገቢ ግብር፣ ቀረጥና ታክስ በሕጉ መሠረት ሳይሰበሰብ ተገኝቷል።
ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቷ ሕግና ደንብ መሠረት ገቢ በወቅቱ መሰብሰቡን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፤ በባለሥልጣኑ ዘጠኝ ቅርንጫፎች ከውዝፍ ግብር፤ ወለድ እና ቀረጥ መሰብሰበ የሚገባው 6.2 ቢሊየን ብር እንዳልተሰበሰበ መገለጹ አይዘነጋም።
ለባለሥልጣኑ የገቢ ጉድለት ከፍተኛው ድርሻ አሁንም ድረስ የያዘው ኮርፖሬሽኑ ሲሆን በቅርብ የተሾሙት ለአዳማ ከተማ ገቢ መጨመር ከፍተኛ ሚና በመጫወት የሚታወቁት አዳነች አበቤ ከኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራር ጋር ያልተሰበሰው ገቢ እንዴት ወደ መንግሥት ካዝና ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል የሚለው ዙሪያ ባለፈው ሐሙስ ውይይት አድርገው እንደነበር ማወቅ ተችሏል።
ለኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ቅርበት ያላቸው ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ እንዳረጋገጡት፥ ያልተከፈለው ቀረጥ ላይ በድጋሚ ለማረጋገጥ ሚንስቴሩ ድርጅቱን ኦዲት ለማድረግ መስማማቱን ገልጸዋል።
ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ የዛሬ ዓመት አካባቢ ወደ 4.2 ቢሊየን ብር አካባቢ እንዲከፍል ቢጠየቅም የሚጠበቅበት 415 ሚሊየን ብር ብቻ ነው በማለት 107 ሚሊየን ብር የከፈለ ቢሆንም፥ በድጋሚ ማስተካካያ በማድረግ ያለበት ገንዘብ 184 ሚሊየን ብር ብቻ ነው በማለት ለጉምሩክ ባለሥልጣኑ ገልጾ ነበር።
ይሁን እንጂ ባለሥልጣኑ በሰጠው ግብረ መልስ፤ ኮርፖሬሽኑ ያመነው ያለተከፈለው ቀረጥና ታክስ ስህተት መሆኑን በመግለጽ ኮርፖሬሽኑ ያልከፈለው የመንግሥት ቀረጥና ታክስ 4.2 ቢሊየን ብር አሳውቀው የነበረ ቢሆንም የተወሰደ ማስተካከያ እርምጃ አልነበረም።
በቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሳደግ በ10 ቢሊየን ብር የተቋቋመው ኮርፖሬሽኑ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ረድፍ እንድትሰለፍ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተበሎ ተገምቶ ነበር። ነገር ግን የተሰጠውን ሚና ችላ በማለት ኮርፖሬሽኑ (ሜቴክ) ባለፉት ስድስት ዓመታት 37 ቢሊየን ብር የውጪ አገር ግዢ መፈፀሙን እና ሁሉም ግዢዎቹ ያለ ምንም ጨረታ እንደተከናወኑ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መገለጹ አይዘነጋም።
የውጪ አገር ግዢ ሲደረግ፤ ከኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ጋር የሥጋ ዝምድና ወይም የጥቅም ትስስር ያላቸው ሰዎች በግዢዎቹ ላይ እስከ 400 ‹ፐርሰንት› ድረስ የተጋነነ ወጪ ያደርጉ ነበር በማለት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለአብነትም በአንድ ድርጅት የ205 ሚሊዮን ብር ግዢ ያለ ጨረታ መፈፀሙን ተናግሮ እንደነበር አይዘነጋም።
ይህንንም ተከትሎ የብረታ ብረት ኢንጅነሪነግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ክንፈ ዳኘው መታሰራቸውና ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወቃል። በባለፈው ሳምንት በነበረ የፍርድ ቤት ወሎ ዳይሬክተሩ የተጠረጠሩባቸው ግዥዎች ተለይተው ለፍርድ ቤት ቀርቧል።
ከጌትፋም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተገዛው ባለሦስት ፎቅ ሕንፃ፣ የ9.5 ሚሊዮን ዩሮ ውል የፈፀሙበት ዐሥር ያገለገሉ አውሮፕላኖች ግዥ፣ የስምንት ሚሊዮን ዩሮ የናፍጣ ነዳጅ ማምረቻ ፋብሪካ ግዥ፣ በ195 ሚሊዮን ብር ከዓለም ፍፁም የገዙት ሪቬራ ሆቴልና ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ በ72 ሚሊዮን ብር የተገዛው ኢምፔሪያል ሆቴል (አሞራ ሕንፃ) 347.9 ሚሊዮን ዶላር ውል የፈፀሙበት፣ ከቆሻሻ የጄት ነዳጅ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ፣ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቀብለውበታል የተባለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የጫካ ምንጣሮ ሥራ ጉዳይ በፍርድ ቤት ከቀረቡት የተጠረጠሩባቸው ግዥዎች መካከል ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here