ባለፉት ሁለት ወራት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጫት የተገኘው የውጪ ንግድ ገቢ ከቡና ከተገኘው በሁለት እጥፍ የሚበልጥ መሆኑ ታወቀ።
ኢትዮጵያ በጥቅምትና ኅዳር ወራት በአገሪቷ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወደ ሦስት ቢሊየን ብር የሚያወጣ ጫት የላከች ሲሆን ከቡና የተገኘው ደግሞ ወደ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር አካባቢ ሆኗል።
ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው የውጪ ንግድ ገቢው የተገኘው ከሶማሊያ ሲሆን የቀረው ወደ ጅቡቲ እና ሌሎች የአፍሪካ፣ አውሮፓ እና እስያ አገራት ተልኳል።
ከጫት የተገኘው ገቢ ለመጨመር እንደ ምክንያት የተገለጸው፤ በአገሪቷ ምሥራቅ ክፍል የነበረው አንፃራዊ ሠላም ሲሆን በተለይም በሃረርጌ ዞኖች የተገኘው ከፍተኛ ምርት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
በንግድ ሚንስቴር የጫትና የጫካ ምርቶች ግብይት የቡድን መሪ የሆኑት ዮሴፍ ማስረሻ እንደገለጹት ለባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ጫት አብቃይ አካባቢዎች ሠላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ የወጪ ንግድ ገቢው የቀነሰ ቢሆንም መንግሥት በወሰዳቸው አፋጣኝ እርምጃዎች ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታ ሊመለሱ ችለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 300 ሚሊየን ዶላር (8.2 ቢሊየን ብር) ለማስገባት እንደሚጠበቅ የገለጹት የቡድን መሪው የምርቱ መዋዠቅና ለመገመት የማይቻል መሆኑ ዕቅዱን ማሳካት ከባድ ሊያረገው ይችላል ብለዋል።
የጫት ምርት በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋቱ በዓለም ደረጃ ኢትዮጵያን ከፍተኛ አምራች ከሆኑት አገራት ተርታ አሰልፏታል።
በአሁኑ ወቅት በሠፊ የመሬት ይዞታ ላይ በብዛት ከሚተከሉ ተክሎች መካከል አንዱ የሆነው ጫት አገሪቱ ለውጪ ገበያ ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ሁለተኛውን ደረጃ ሲይዝ፣ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች እጅግ ጠቃሚ የገቢ ምንጭ ነው።
ጫት በአብዛኛው የሚመረተው ትንንሽ እርሻዎች ባሏቸው እና ምርታቸውን ለቀጣይ ስርጭት ወይም ለውጪ ገበያ በንግድ ማዕከላት በሚሸጡ ገበሬዎች ነው። በአሁኑ ወቅት ከሦስት ሚሊዮን የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች ጫት የሚያመርቱ ሲሆን፣ ከእርሻ ከሚገኝ ገቢ መካከል ከፍተኛውን ይይዛል።
የአገር ውስጥ ፍላጎት መኖሩ ከፍተኛ መጠን ያለውን የጫት ምርት በአገሪቱ ውስጥ በጥቅም ላይ እንዲውል ያደረገው ሲሆን ተክሉ ከብዙ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ልምምዶች ጋር በጥልቅ የተሳሰረ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።
በተጨማሪም ጥናቶች እንደሚያሳዮት ባለፉት 15 ዓመታት ለጫት ምርት በጥቅም ላይ የዋለው መሬት ስፋት በ160 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ ቀድሞ ጫት ይበቅልባቸው ባልነበሩ የአገሪቱ ክልሎችም መብቀል ጀምሯል። ጭማሪው ጫት ከቡና፣ ጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ባነሰ ሁኔታ ቢሆንም ሥራ ሥር ያላቸው ተክሎች እና አትክልቶች የያዙት የመሬት መጠን ተደምሮ በመብለጥ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በአጠቃላይ የመሬት ሽፋን ከፍተኛውን መጠን በመያዝ፣ በስፋት የሚመረት ተክል ሆኗል።
ይሁን እንጂ ጫት ውስጥ በተፈጥሮ የሚገኘው አነቃቂ ንጥረ ነገር ካቶኒን፣ የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ሥነ አዕምሮ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ንጥረ ነገሮች ኮንቬንሽን ተርታ ተፈርጇል። በሌላ በኩል በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ዕፆች ዝርዝር ውስጥ የማይገኝ ስለ ሆነ የጫት ሕጋዊነት በራሱ አከራካሪ ሲሆን ከአገር አገር በጫት ላይ የተወሰነው ውሳኔም የተለያየ ነው።
ነገር ግን፤ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቁጥራቸው እየጨመረ በመሔድ ላይ የሚገኑ አገራት ጫትን ቁጥጥር የሚደረገብት ተክል አድርገው ፈርጀውታል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ እነዚህን አገራት ቻይና፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ኔዘርላንድስ ተቀላቅለዋቸዋል። ነገር ግን ጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና የመንን ጨምሮ በአንዳንድ አገራት ውስጥ ጫት መገበያየት ሕጋዊ ነው።
ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011