ኢትዮ ቴሌኮም በግማሽ ዓመት ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

0
749
ስድስት አዳዲስ እና 16 የተሻሻሉ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን ለገበያ በማቅረብ በስድስት ወራት ውስጥ 22 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ኢትዮ ቴሌኮም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ። ተቋሙ የእቅዱን 104 በመቶ ያሳካ ሲሆን፣ ገቢው ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ32 በመቶ እድገት አሳይቷል። የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 73 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ ይህም የእቅዱን 111 በመቶ  ያስመዘገበ እና ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ116 በመቶ  እድገት እንዳስመዘገበ ተነግሯል። የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምጽ ገቢ ድርሻ 50 ነጥብ 4 በመቶ፣ የዳታና ኢንተርኔት ገቢ ድርሻ 27 በመቶ፣ የዓለም አቀፍ ንግድ ገቢ ድርሻ 9 በመቶ፣ እሴት ከሚጨምሩ አገልግሎቶች (VAS) 8 ነጥብ 5 በመቶ  እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶች የተገኘው ገቢ ድርሻ 3 በመቶ  ይይዛል። በስድስት ወራት ውስጥ አጠቃላይ 3 ነጥብ 89 ቢሊዮን ብር ታክስና 2 ቢሊዮን ብር ዲቪደንድ ለመንግሥት የተከፈለ ሲሆን፣ በቬንደር ፋይናንሲንግ ሞዳሊቲ ወይም 148 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ተፈጽሟል። ለተከናወኑ ፕሮጀክቶች ብድር 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወይም 148 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ እንደተፈጸመ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ይፋ አድርጓል። የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ብዛት 45 ነጥብ 6 ሚሊዮን ደርሷል። የእቅዱ 99 በመቶ አፈጻጸም ላይ ያለ ሲሆን፣ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር የ10 ነጥብ 9 እድገት አሳይቷል። የደንበኞችን ሁለንተናዊ ተሞክሮ ለማሻሻል የዳታ አገልግሎት ተጠቃሚነት ፍላጎት ማስተናገድ የሚያስችል የኔትወርክ አቅም የማሳደግ ሥራዎች በአዲስ አበባና በክልሎች እያከናወነ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል። በስድስት ወራት ከተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች 759 ሺሕ 741 ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል የ3ጂ እና 170 ሺሕ 737 የ2ጂ ሞባይል ኔትወርክ አቅም መፍጠር መቻሉ ተገልጿል። ቅጽ 2 ቁጥር 63 ጥር 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here