መገናኛ ብዙኀን የቅድመ ምርጫ ትንበያ እንዲያዘጋጁ የሚፈቅድ መመሪያ ተዘጋጀ

0
554

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተረቀቀው የመገናኛ ብዙኀን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የሥነ ምግባር እና አሠራር መመሪያ፣ መገናኛ ብዙኀን የቅድመ ምርጫ ትንበያ በማዘጋጀት ለመራጩ ሕዝብ ማቅረብ እንዲችሉ ደነገገ። መገናኛ ብዘኀኑ የሕዝብ አስተያየት አሰባስበው ትንበያውን በራሳቸውም ይሁን በሌሎች ድርጅቶች ካከናወኑ፣ የድርጅቶቹን ሥም በመግለፅ መቼ እና የት እንዳከናወኑ፣ ምን ያህል ሕዝብ እንደተጠየቀ፣ እንደዚሁም የት፣ መቼ እና እንዴት እንደተከናወነ በማሳወቅ፤ ለመራጩ ሕዝብ ጠቀሜታ ያለውን የምርጫ ቅድመ ትንበያ መረጃ ሊያሳትሙ እንዲሁም ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ደንግጓል፤ረቂቁ። መረጃውንም ለማሰባሰብ የተጠቀሙበት ስልት ምን አይነት እንደሆነ እና መጠይቁ ሲደረግ የቀረቡትን ጥያቄዎች፣ ከመስክ ሥራ የተገኘ መረጃንም ከምርጫ ትንበያው ገባው ጋር ማያያዝ እንደሚገባቸው ቦርዱ ባዘጋጀው የመገናኛ ብዙኀን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የሥነ ምግባር መመሪያ ረቂቅ ላይ አካትቷል። ነገር ግን ምርጫው በሚከናወንበት ዕለት ማንኛውም ሚዲያ ወይንም (ግለሰብ) የምርጫ ውጤት ትንበያ በማዘጋጀት ማሰራጨት እንደማይችል ተገልጿል።

የምርጫ ቅስቀሳን በተመለከተም መገናኛ ብዙኀንም ሆነ ጋዜጠኛ ምርጫው ሊከናወን ኹለት ቀናት ሲቀሩት ጀምሮ ድምፅ የመስጠት ሂደት እስከሚጠናቀቅበት ሰዓት ድረስ የእጩ ተወዳዳሪዎችን የምርጫ ቅስቀሳ ማተምም ሆነ ማሰራጨት አይችሉም። በምርጫው ዕለት የሚዘገቡ ዜናዎችና ፕሮግራሞች ላይ ድምፅ ሰጪዎች ያስተላለፉትን ምርጫ ውሳኔ የሚገልፅ በሌሎች ድምፅ ሰጪዎች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ይዘት ያለው ህትመት ማተም እና ማሰራጨት የተከለከለ ስለመሆኑ መመሪያው ያትታል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በምርጫ 1997 ወቅት መሰል በርካታ ግምቶች ሲዘጋጁ እንደነበር፣ በወቅቱም ቅንጅት ምርጫውን ያሽንፋል የሚሉ ግምቶች በስፋት ሲሰራጩ መቆየታቸውን የገለፁት የሚዲያ ሕግመምህር እና በሚዲያ ሕግ ማሻሻያ አስተባባሪ የሆነት ሰሎሞን ጎሹ ናቸው። በወቅቱ ከምርጫው በኋላ ለተነሱ ምርጫው ተጭበርብሯል ለሚሉ ጥያቄዎች እንዲሁም ተነስቶ ለነበረው የፖለቲካ ትኩሳት መንስኤ በመሆናቸው፣ የምርጫ ቅድመ ትንበያዎች እንዳይደረጉ ታግደው ቆይተዋል ብለዋል።

እስከ አሁን ባለው ሁኔታ መገናኛ ብዙኀን እና መሰል የሲቪክ ማኅበራት በታፈነ ሁኔታ ውስጥ በመቆየታቸው ተዳክመው ቆይተዋል፤ አሁን ሲፈቀድ የመንግሥት ተቋማት መረጃ በመውሰድ የዜጎችንም አስተያየት በመጠየቅ የምርጫ ዘገባ ማቅረብ ችግር አይኖረውም ሲሉ ገልጸዋል። ሆኖም ጉዳዩ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው ያሉት ሰሎሞን፣ መፈቀዱ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ከዚህ ቀደም እንደሚስተዋለው መገናኛ ብዙሃኀን አካባቢዎችን በመለየት በአካባቢው ከሚገኘው ተወዳዳሪ ፓርቲ ሌላ አይመረጥም የሚሉ መሰል ትንበያዎችን ከማዘጋጀት ሊቆጠቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም መሰል በርካታ መመሪያዎች ወጥተዋል ጉዳዩ መመሪያዎቹ መውጣታቸው ሳይሆን የወጡበት ዓለማ፣ ይዘታቸው እና አተገባበራቸው ላይ ነው። እነዚያ መመሪያዎች ሐሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን ከማስፋፋት ይልቅ የሚገድቡ ናቸው። እንዲሁም ሲዘጋጁ ግልጽነት የጎደላቸው እና የሚመለከታቸውን አካላት ባላገናዘበ መልኩ ነበር ሲሉ ገልጸዋል።

አሁን የመመሪያ ዝግጅቱ በመጠናቅቅ ላይ የሚገኘውን የመገናኛ ብዙኀን የመረጃ ነፃነት አዋጅ መሰረታዊ መርሆች ሊጣስ አይችልም። እንዲሁም መንግሥት እንደዚህ አይነት ጉዳዮችን ከመመሪያው በተጨማሪ መገናኛ ብዙኀን በራሳቸው የኤዲቶሪያል

መመሪያ መሰረት የሚመለከቱበትን እና በኃላፊነት የሚዘግቡበትን መንገድ ሊፈጥር እንደሚገባው ተናግረዋል።

በሴቶች ላይ የሚፈፀም አድሎአዊ የሆነ ወይም የጥላቻ እና የእምነት ማጣት አመለካከት የሚፈጥሩ መረጃዎችን መሰራጨት የተከለከለ መሆኑን የሚገልፀው መመሪያው፣ መገናኛ ብዙኀን ሴት ተወዳዳሪዎችን ማስተዋውቅ እና ማበረታታት እንደሚገባቸው አስቀምጧል።

ቦርዱ ማንኛውንም የምርጫ መረጃ፣ ትምህርት ወይም ማስታወቂያ እና ፕሮግራም ያለ ክፍያም ሆነ በክፍያ በመገናኛ ብዘኀን ማስተላለፍ ይችላል።

እንዲሁም መገናኛ ብዙኀን ማንኛውንም የፖለቲካ ማስታወቂያ ያለ ክፍያ ማስተናገድ የማይችሉ ሲሆን፣ ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እና ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለተመሳሳይ ጊዜ የሚጠይቁት ክፍያ ተመሳሳይ መሆን እንደሚገባው በመመሪያው ተደንግጓል።

ይህንን መመሪያ ተላልፈው በሚገኙ የመገናኛ ብዙኀን ላይም ቦርዱ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ የመገናኛ ብዙኀኑ ይቅርታ እንዲጠይቅ ማድረግን ጨማሮ፣ በጋዜጠኛው የተፈፀመው ጥፋት በዲስፕሊን የሚያስቀጣ ሆኖ ሲገኝም የሚሠራበት ተቋም አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ለምርጫ ቦርዱ እንዲያሳውቅ የሚያስገድድ አንቀፅ በመመሪያው ላይ ተቀምጧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 63 ጥር 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here