ኢትዮ ቴሌኮም ዋትስአፕ፣ ቫይበር፣ ቴሌግራምና ሌሎችንም አላግድም አለ

0
982

ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ‹ዋትሳፕ›፣ ‹ሜሴንጀር›፣ ‹ቫይበር›፣ ‹ኢሞ›፣ ‹ዊቻት› እና ‹ቴሌግራም› ያሉ የማኅበራዊ የመገናኛ መተግበሪያዎችን የመዝጋት ፍላጎት እንደሌለው ገለጸ።
ኢትዮ ቴሌኮም የማኅበራዊ መገናኛ መተግበሪያዎች ላይ የክፍያ ታሪፍ ለማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ለመዝጋት የሚያስችለውን የቴክኖሎጂ ግዢ ፈጽሟል የሚባለው መረጃ ውሸት እንደሆነ አስታውቋል። ይሁንና ደንበኞቼ የማኅበራዊ መገናኛ መተግበሪያዎችን በተሻለ ሁኔታ መጠቀም የሚያስላቸውን ቴክኖሎጂ ለመግዛት ውል አስሬ ነበር ያለው ኢትዮ ቴሌኮም ከቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያው ጋር ባለመግባባቴ ለጊዜው ውሉን አቋርጫለሁ ብሏል።
በማኅበራዊ ሚዲያና አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የተሰራጨው መረጃ ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ‹ዋትሳፕ›፣ ‹ሜሴንጀር›፣ ‹ቫይበር›፣ ‹ኢሞ›፣ ‹ዊቻት› እና ‹ቴሌግራም› ዓይነት የበይነ መረብ መገናኛ ዘዴዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ‹ቴክኖሎጂ ባይት› ከተባለ ኩባንያ ከ10 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ በሆነ ዋጋ መግዛቱን የሚገልጽ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሞባይልና በይነመረብ አገልግሎትን የሚጠቀሙ ሰዎች ዓለም ዐቀፍ የስልክ ጥሪ ከማድረግ ይልቅ ዋትሳፕና ቫይበርን ጨምሮ የተለያዩ የሞባይል መተግበሪያዎችን እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ይህም ኢትዮ ቴሌኮም ከዓለም ዐቀፍ ጥሪ የሚያገኘውን ገቢ ይቀንሳል የሚሉ አሉ። ተገዛ የተባለውና ፒሲአርኤፍ/ቲዲፍ የተሰኘው መተግበሪያም ኢትዮ ቴሌኮም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ምክንያት እየቀነሰ የመጣውን ገቢ ለማሻሻል ይረዳዋል ተብሏል።
ስለ ጉዳዩ አዲስ ማለዳ የጠየቀቻቸው በኢትዮ ቴሌኮም የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ጨረር አክሊሉ “ኢትዮ ቴሌኮም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን የሚያግድ ወይንም በአገልግሎቱ ላይ የታሪፍ ጭማሪ ማድረግ የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ ገዝቷል የሚባለው የሐሰት ወሬ ነው” ብለዋል።
በእርግጥ ተቋሙ “ደንበኞቻችን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተሻለ ሁኔታ መጠቀም የሚያስላቸውን የቴክኖሎጂ መሣሪያ ግዢ ለመፈፀም ሥሙን አሁን መጥቀስ ከማልፈልገው ተቋም ጋር ውል ተዋውሎ ነበር። ነገር ግን ቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያው ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ የግዢ አፈፃፀምን ለመከተል በመፈለጉ ኢትዮ ቴሌኮም ውሉን ለጊዜው አቋርጧል” ብለዋል።
ጨረር የኩባንያውን ሥም መግለጽ ያልፈለጉበትን ምክንያት ሲያስረዱም ጉዳዩ እንዳልተቋጨና የሥራ አስፈፃሚው አካል እየተነጋገረበት ያለ መሆኑን ገልጸው ሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ ሲያሳልፍ ሙሉ መረጃሙን እንደሚሰጡ ተናግረዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ማድረግ የሚያስችሉ የሞባይል መተግበሪያዎች መስፋፋት የድርጅቱን ገቢ ይቀንሳል ስለተባለው ጉዳይ ሲያብራሩም እንደ ‹ቫይበር›ና ‹ቴሌግራም› ያሉ መተግበሪያዎችን ለመጠቀም የበይነመረብ አገልግሎት እንደሚያስፈልግ ገልጸው ኢትዮ ቴሌኮም ከዓለም ዐቀፍ ጥሪ ማግኘት ያልቻለውን ከበይነመረብ አገልግሎት እንደሚያገኘው ጠቁመዋል።
በ2010 ይፋ የሆነ መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ቁጥር 53 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን፥ የበይነመረብ ተጠቃሚዎቹ ቁጥር ደግሞ ከ10 ሚሊዮን አልፏል። ይህም ከ2009 ጋር ሲነፃፀር የ11 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
ተቋሙ ትርፋማ ከሚባሉት መካል ሲመደብ የ2010 ዓመታዊ ገቢውም 33 ቢሊየን ብር ደርሷል። ከ2005 ጋር ሲነፃፀርም የ21 ቢሊየን ብር ጭማሪ አሳይቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here