የስርዓተ መንግሥቱ መዋቅር እንደገና ይጠና

0
590

የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት አወቃቀር በሕግ ፌደራላዊ ሆኖ ከተቀረፀ ሁለት ዐሥርታት በላይ ተቆጥረዋል። በመሠረቱ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሰፊ የቆዳ ሥፋት፣ ብዙ ሕዝብ እና የተለያዩ ባሕላዊ እሴቶች እና ልማዶች እንዲሁም የአኗኗር ዘዬዎች ላሏቸው አገራት በልዩነት እያጌጡ፣ በጋራ ለመኖር ፌደራላዊ የመንግሥት አወቃቀር የተሻለው አማራጭ እንደሆነ ብዙም አጠያያቂ አይደለም። በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ልኂቃን ዘንድም የፌዴራላዊ አገረ መንግሥት አወቃቀር ተገቢነት ላይ ሥምምነት ያለ ይመስላል፤ ልዩነቱ የሚመጣው የፌደራል አወቃቀሩ መሠረት ያደረገባቸው ቅንጣቶች ላይ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትየጵያ የ‹ማንነቴ ይታወቅልኝ› ጥያቄዎች፣ በወረዳ፣ በልዩ ዞን እና በክልልነት ደረጃ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች የፌደራል ስርዓቱ በተግባር ላይ ከዋለ በኋላ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ጥያቄዎቹ በተደጋጋሚ ይሰማሉ፤ ይህ የሆነው መንግሥት ለሕዝባዊ ጥያቄዎች በጎ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ተስፋ መጣል ስለተጀመረ ይሆናል። ይሁንና የጥያቄዎቹ ማቆሚያ የለሽነት ብሎም ለግጭት እና አለመተማመን መንስዔ እስከመሆን መድረሱ፣ ከዚህ በፊት፣ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የፖቲካ ልኂቃን እየተተቸ የነበረው የፌዴራል ስርዓቱ አወቃቀር ድጋሚ መመርመር እንዳለበት አመላካች ሆኗል።
በመሆኑም በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የፌደራሉን አወቃቀርና የክልሎችን የወሰን መካለል ጉዳዮች በተመለከተ ሊያጠና የተቋቋመው ኮሚሽን ተገቢና ወቅታዊ ነው ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ኮሚሽኑ በገለልተኛ ሙያተኞች ሥራውን ማከናወን የሚገባው ከመሆኑም ባሻገር በሥራ ሒደቱ ውስጥ የሕዝቦች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆናቸው መዘንጋት የለበትም። ኮሚሽኑ እነዚህን ሙያተኝነትን እና አሳታፊነትን መሠረት ካደረገ በኋላ በጥልቀት ሊያጠናቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በዚሁ አጋጣሚ መጠቆም እንወዳለን።
በሥራ ላይ የሚገኘው ፌደራላዊ አወቃቀር መሠረት በአመዛኙ ቋንቋን እና በቋንቋ ብያኔ ላይ የተመሠረተ ዘውግን መነሻ ያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ኮሚሽኑ ሊያጠናቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ሌሎች መሥፈርቶችንም (ለምሳሌ የአስተዳደር አመቺነት፣ የተፈጥሮ ሀብት መገኛነት፣ የምጣኔ ሀብት ደረጃ፣ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ እና ወዘተ.) በጥናቱ ውስጥ እንዲያካትት እንጠይቃለን።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እዚህም እዚያም የሚነሱትን ማንነትን መሠረት ያደረጉ አቤቱታዎች፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች እና “የመጤና መሥራች” ትርክቶች፣ እንዲሁም በተፈጠሩት ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት መካከል ያለው መስተጋብር ጤናማ አለመሆን የብዙ ሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ አካል ጉዳት በማድረስ፣ ንብረት በማውደምና በማፈናቀል ረገድ ያደረሰው እና በማድረስ ላይ ያለው ጉዳት አንዱ ምክንያት ይሔው ፌደራላዊ ስርዓተ መንግሥት ነው በሚል ቅሬታ እየቀረበ እንደመሆኑ፥ ኮሚሽኑ በጥናቱ ውስጥ እነዚህን ጉዳዮች ከግምት ውስጥ እንዲያስገባ እና የግጭቶቹ እውነተኛ መንስዔን ምንነት እና ዜጎች ችግራቸው በምን ዓይነት መንገድ እንዲፈታላቸው እንደሚፈልጉ በጥናቱ እንዲመለከተው እናሳስባለን።
ከዚህ በተጨማሪም፣ በጥልቅ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ የአገረ መንግሥቱ አወቃቀር ብቻውን ለሕዝቦች የነጻነት እና በጋራ የመበልፀግ ጥያቄ መልስ አይሰጥም፤ ዴሞክራሲያዊነት ያስፈልጋል። ዴሞክራሲ በሌለበት ስርዓት ውስጥ ፌደራላዊ አወቃቀሩ የሚጠበቅበትን ያልተማከለ፣ የተናጠል እና የጣምራ አመራር (self and shared rules) ያመጣል ማለት ‹ላም ባልዋለበት፣ ኩበት ለቀማ› እንደማድረግ ይቆጠራል። ለዚህ እንደዋቢ የምንጠቅሰው የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት በሕግ ደረጃ ፌዴራላዊ መዋቅር ቢኖረውም፥ በተግባር ግን የተማከለ እና የራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች (የተናጠል አመራር) የሚያሳንስ፣ ለቁጥጥር እና ሚዛን የማይመች መሆኑ ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንዲሉ ችግሩን አባብሶታል። በመሆኑም ዴሞክራሲው ተጠያቂነት እንዲጎለብት፣ የሕግ የበላይነት እንዲያብብ፣ የግልና የቡድን መብቶች እንዲከበሩ፣ በሕዝቦች መካከል መተማመን እንዲፈጠር ብሎም አገር ዐቀፉ የወል (አሰባሳቢው) ማንነት – ኢትዮጵያዊነት – ሁሉን አካታች ሆኖ እንዲያድግ ማድረግ፣ አወቃቀሩን ከማጥናት እና ከመከለስ ጎን ለጎን ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው።
ለማጠቃለል ኮሚሽኑ በጥልቀትና በጥንቃቄ ሊመልሳቸው የሚገቡ ጥያቄዎች፡- ፌደራላዊ አወቃቀሩ ላይ የተገለገጹ ተግባራት በሥራ ላይ መዋል አለማዋላቸውን፣ የማንነት ጥያቄዎችን ለመመለስ መቻል አለመቻሉን፣ በክልሎች መካከል ያለውን መስተጋብር ጤናማነት፣ በሕዝቦች መካከል የነበሩ እና ያሉ ግጭቶችን መቅረፍ፣ አገር ዐቀፍ፣ አካታች የወል ማንነት ግንባታን በተሳካ ሁኔታ እንዴት ማከናወን፣ በሕዝቦች መካከል መተማመን መፍጠር እና ይህንንም ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌዎችን እና ዴሞክራሲያዊ መርሖዎችን ባሟላ መልኩ ማድረግ ናቸው።
በመጨረሻም የኮሚሽኑ ጥናት ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ትርፍ ማጋበሻነት እንዳይውል፣ ይልቁንም ከዘላቂ የአገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት አንዱ አካል ሆኖ መቀጠል ይገባዋል። ይህ እንዲሳካ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን በማዋጣት የዜግነት፣ ሙያዊ እና አገራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ስንል ጥሪ እናስተላልፋለን። ለፌደራል ስርዓተ መንግሥቱ አወቃቀርና የክልሎች አከላለል እንከኖች አስተማማኝ መፍትሔ ለማግኘት በጥልቀትና በዝርዝር ሕዝብ አሳታፊ ጥናት ማድረግ አንዱን አሸናፊ ሌላኛውን ተሸናፊ የሚያደርግ ሳይሆን ሁሉንም ባለድል የሚያደርግ አገረ መንግሥታዊ ስርዓተ መዋቅር ለመፍጠር ያስችላል እና ጉዳዩ ትልቅ ትኩረት እንዲሰጠው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here