ለሴፍቲ ኔት ፕሮግራም 75 ሺሕ ቶን ስንዴ ሊገዛ ነው

0
685

በግብርና ሚኒስቴር ስር ለሚከናወነው ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል 75 ሺሕ ቶን ስንዴ ግዢ ለማከናወን ‹ፕሮሚሲንግ› ከተሰኘ ድርጅት ጋር ከስምምነት ላይ መድረሱን የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አስታወቀ።
ግዢው የዓለም ባንክ ለግብርና ሚኒስቴር የሴፍትኔት ፕሮግራም ባደረገው 24 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚፈፀም ነው። አቅራቢዎቹን የመለየት ሥራ በመንግሥት ግዢ እና ንብረት ማስወገድ በኩል እንደተከናወነም ለማወቅ ተችሏል።
አቅራቢ ድረጅቶችንም ለመለየት በተደረገው ጨረታ ላይ ሀካን፣ ፕሮሚሲንግ እና ጀም ክሮፕ የተሰኙ ሦስት ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል። ፕሮሚሲንግ እስከ ድሬደዋ መጋዘን አንድ ቶን ስንዴ ገዝቶ ለማድረስ 310.05 ዶላር ያቀረበ ሲሆን፣ በአጠቃላይም 75 ሺሕ ቶኑን ስንዴ ወደ ሦስቱ መጋዘን ለማድረስ 23.8 ሚሊዮን ዶላር በማቅረቡ ጨረታውን ማሸነፉን የአገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መልካሙ ደፋሊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሀካን የተባለ አቅራቢ 25.4 ሚሊዮን ዶላር ያቀረበ ሲሆን፣ ጀምክሮፕ ደግሞ 26.4 ሚሊዮን ዶላር አቅርቧል። ጨረታዉን ፕሮሚሲንግ 23.8 ሚሊዮን ዶላር ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረቡ ጥር 14/2012 አሸናፊ ሆኗል ብለዋል። ድርጅቱ አንድ ቶን ስንዴ እስከ አዳማ ለማጓጓዝ 324.05 ዶላር የቀረበ ሲሆን፣ እስከ ኮምቦልቻ መጋዘን ድረስ ደግሞ በ320 ዶላር ለማቅረብ ባቀረበው ዝቅተኛ ዋጋ ተመርጧል።
የግብርና ሚኒሰቴርም በጨረታው ውጤት ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ በ45 ቀን ውስጥ ዉል እንደሚፈፀም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዉ ገልፀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here