የበረሃ አንበጣን ለመከላከል 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊደረግ ነው

0
611

በኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል ኹለት ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች አንድ ሚሊዮን 300 ሺሕ ዶላር ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሆነ የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።
የገንዘብ ድጋፉንም ለማድረግ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት /FAO/ እና ከአሜሪካ ዓለም ዐቀፍ የልማት ኤጀንሲ /USAID/ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ቃል መግባታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍም ለፀረ-ተባይ መከላከያ ትጥቅ እና ለመረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያዎች እንዲሁም ለመድኃኒት መርጫ መሣሪያዎች ግዢ ይውላል ተብሏል።
ከዚህ ባሻገር ድጋፉ ፀረ-አንበጣ መድኃኒት የሚረጩ የአውሮፕላኖችን ኪራይ ለመሸፈን፣ በዘርፉ ለሚሠሩ ባለሞያዎች ሥልጠና ለመስጠት እና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ያለመ እንደሆነም የተገለጸ ሲሆን፣ ከድርጅቶቹም ጋር የድጋፍ ስምምነት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።
የአንበጣ መንጋው በሶማሊያ ክልል፣ ምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ባሉ ዞኖች እንዲሁም በተወሰኑ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተከስቷል። አሁን ባለው ሁኔታም በዘመናዊና በባህላዊ መንገድ የአንበጣውን መንጋ ቁጥር ለመቀንስ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
የበረሃ አንበጣ ባለፉት ወራት በአፋር፣ ሰሜን ምሥራቅ አማራ፣ ደቡብ ትግራይ፣ ምሥራቃዊ ሶማሌ እና ኦሮሚያ፣ ምዕራብ እና ምሥራቅ ሀረርጌን ጨምሮ እስከ ድሬዳዋ ድረሰ ጉዳት አድርሷል። ግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ለኹለተኛ ጊዜ እየተስፋፋ የሚገኘውን የበረሃ አንበጣ መቆጣጠር ካልተቻለ በቀጣይ ወራት ቋሚ እና የመስኖ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል መግልፁም የሚታወስ ነው።
ከአጎራባች አገሮች በተለይም ከኬንያና ከሶማሊያ አገራት እንደገባ የሚነገረው የአንበጣ መንጋ፣ በወቅቱ ቁጥሩን መቀነስ ካልተቻለ ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ አቅም እንዳለውም ከወዲሁ እየተነገረ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here