በአማራ ክልል 200 አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ሊገነቡ ነው

0
890

አማራ ክልል በ421 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 200 አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊጀመር መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ከ2010 ጀምሮ ከተያዙ 118 ነባር የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል 89ኙ እስከ ቀጣዩ መጋቢት 30 2012 ድረስ ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል። በዚህ ዓመትም 200 አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ክልሉ በዝግጅት ላይ ይገኛል ተብሏል።
በመጋቢት ወር ይጠናቀቃሉ ለተባሉ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያም ከ142 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡም የተጠቀሰ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡ 219 ሺሕ 274 ሄክታር የእርሻ መሬት ያለማሉ ተብሎም ይጠበቃል።
በግንባታ ሂደት ላይ ከሚገኙት ፕሮጀክቶች በተጨማሪ 421 ሚሊዮን ብር በጀት የተመደበላቸው የእነዚህ 200 ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚጀመርም የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል። ነባሮቹን እና አዳዲስ የሚጀመሩትን ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ቢሮው ማስታወቁን ከአማራ መገናኛ ብዙኀን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ ካሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል 29 የሚሆኑት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በ2012 በጀት ዓመት ከ 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ አራት የመስኖ ግድብ እና ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ መጀመሩ የሚታውስ ሲሆን፣ ከ 33 ሺሕ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሏል። ከአራቱ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በአማራ ክልል የሚገኝ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here