ፍርድ ቤቶች ትርጉም ለሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልገሎት እየሰጡ አይደለም ተባለ

0
334

በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ተገልጋዮች በሚግባቡበት ቋንቋ ተርጉመው እያቀረቡ አለመሆኑ ተገለፀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትኅ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሦስቱ ፍርድ ቤቶች ላይ ባደረገው የመስክ ምልከታ፣ በየጊዜው ከኅብረተሰቡ የሚመጡ ቅሬታዎችን ለመፍታት ፍርድ ቤቶች ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የውሳኔ ግልባጭ እና መሰል መረጃዎችን ትርጉም ለሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየተሰጠ አለመሆኑን አስታውቋል።
ቋሚ ኮሚቴው ከተቋማቱ ሠራተኞች ጋር ባደረገው ውይይት ላይም በፍርድ ቤቶቹ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ግልባጭ ሊኖር እንደሚገባ ያሳሰበ ሲሆን፣ ተገልጋዮች አገልግሎቱን እንዲያገኙም ፍርድ ቤቶች እንዲያመቻቹ አሳስቧል።
በውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት መዓዛ አሸናፊም፣ በተቋማቱ ላይ አዳዲስ አሠራሮች እየተተገበሩ መሆናቸውን በመጠቆም፤ የሪፎርም ሥራዎች ላይ ዳኞችን አሳትፈናቸዋል የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸው ተገልጿል።
በፍርድ ቤቶች አከባቢ የሚዘገቡ ዘገባዎች በሚተላለፉበት ጊዜ ተከታትሎ የእርምት እርምጃ መውሰድ የዳኛው ኃላፊነት በመሆኑ ወሳኝ የሆኑ የማስተካከያ እርምጃዎች ሲወሰዱ ፍርድ ቤቶች ሊበረታቱ እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።
የሕግ፣ ፍትኅ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያደረገውን የመስክ ምልከታ ታሳቢ በማድረግ፣ በመንግሥት ከታች ላሉት መዋቅሮች እየተደረገ ያለው የድጋፍ እና ክትትል ሥራ ክፍተቶችን በመሙላት እና የተገልጋይ እርካታ ማወቅ የሚያስችሉ የአሰራር ስርአቶችን በመዘርጋት ተፈጻሚ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አሳስቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here