እውቀትን ፍለጋ

0
825

ሕይወት አንድም ሰዎች ባከበሩት ፍላጎታቸው መሠረት የሚሄዱት ጉዞ ነው፤ ከሕልማቸው ለመድረስ። የኑሮ ሁኔታ ግድ ብሎ ባልፈለጉት መስክ ቢሰማሩ እንኳ፣ የሚፈልጉትን በማሰብ ውስጥ ጉዞው መኖሩ አይቀርም። አንዳንዶች ደግሞ በራሳቸው ባይሆንም በሌሎች ሕይወት ውስጥ ጉዞውን በማየት የሐሳብ ሸክማቸውን ያቀላሉ። እንዲህ ያለ የሕይወት አጥር መካከል ይገኛሉ፣ በሰሜን ሸዋ ውጫሌ ወረዳ አዲስ ማለዳ ያገኘቻቸው እናት፤ ወሰኔ አበበ።

ወሰኔ አበበ የአራት ልጆች እናት ናቸው። እናትነት ደረጃ ላይ ሳይደርሱ በፊት እርሳቸውም በእናታቸውና በአባታቸው ቤት ሳሉ የነበራቸውን ልጅነት ያስታውሳሉ። ከምንም በላይ ደግሞ ለትምህርት የነበራቸውን ፍቅር አይዘነጉም። ሆኖም በእርሳቸው የሕይወት ጉዞ ትምህርት ቢታገሉለት፣ አብዝተው ቢፈልጉትና ቢመኙትም ብዙ ያሻገራቸው መንገድ አልነበረም። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ወይም እስከ ስምንተኛ ክፍል እንደጨረሱ የሚሸጋገሩበት ትምህርት ቤት በአቅራቢያቸው አልነበረም።

ከአምስት እና ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአንጻሩ ትምህርት በሚገኝባት መልካ ጡሪ በምትባል አካባቢ እንዳይማሩ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ሊልኳቸው አልፈቀዱም። ነገሩስ የፈቃድ ጉዳይ ብቻም ሳይሆን የአቅምም ነገር ምክንያት ነበር። የቤት ኪራይ ከፍለውና ቀለብ ችለው ልጃቸውን በርቀት ማስተማር የሚችል የገንዘብ አቅም አልነበራቸውም።
ፈቃድ ለመከልከላቸውም ቤተሰቦቻቸው በቂ ምክንያት ነበራቸው። ልጃቸው መንገድ አቋርጣ ስትሄድ ጥቃት ይደርስባታል ብለው ስለሚሰጉም ነበር።

‹‹ቤተሰቦቼ ስላልቻሉ ትምህርቱን ትቼ ወደ ግብርና ገባሁ። የትምህርትን ጥቅም ስለማውቅ ወደ ግብርና ብገባም ኹለት ልጆቼን አስተምሬአለሁ›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።
በፊት በአካባቢያቸው ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አልነበረም። በአምስት ኪሎ ሜትርና ከዛ በላይ ርቀት ላይ የሚገኘው ትምህርት ቤት እየተመላለሱ ለመማር የትራንስፖርት ወጪ፣ በዛው ቆይቶ ቤት ተከራይቶ ለመኖርም በተመሳሳይ የቤት ኪራይን ጨምሮ የቀለብ ወጪ በኑሮው ላይ ሌላ ሸክም ነው። ‹‹እኔ ያልተማርኩት ለዛ ነው። አሁን በአካባቢያችን ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለተሠራልን ግን ልጆቼ ሳይርቁኝ ለማስተማር እችላለሁ›› ሲሉም አክለዋል።

ወሰኔን ያገኘናቸው ከሳምንት ቀደም ብሎ በሰሜን ሸዋ ዞን ውጫሌ ወረዳ ጃቲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቀዳማዊት አመቤት ጽሕፈት ቤት ተገንብቶ ለትምህርት ክፍት የሆነውን ኢፋ ሰላሌ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተመረቀበት ወቅት ነው። ወሰኔ በሆነውና በተደረገው ደስታቸው የላቀ ነበር። በተለይ አሁን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚማሩ ልጆቻቸው ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቅርበት ማግኘታቸው ደስታቸውን አልቆታል።

እኚህ እናት የመጀመሪያ ኹለት ሴት ልጆቻቸውን በዚህ ትምህርት ቤት እንዳያስተምሩ ጊዜው ረፍዷል። ሴት ልጆቻቸው እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረው ወደ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመላክ በቅርብ መማሪያ ባለመኖሩ፣ ወደ ትዳር ገብተዋል። ኹለቱ የቀሩ ወንድ ልጆቻቸው ግን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመሆናቸው፣ ያንን ጨርሰው የት እንደሚገቡ ከወዲሁ በማወቃቸው ነው ደስታቸው የበረታው።

በግብርና እና ከብት በማርባት ኑሮአቸውን የሚገፉት ወሰኔ፣ በቀበሌያቸው ሴቶች ጉዳይ ላይ ያገለገሉበትን ጊዜ ያወሳሉ። ጸሐፊም በመሆን መሥራታቸውን በመጥቀስ ‹‹አሁን ወደ እርጅና ነው። ልጆቼን ተክቻለሁ›› አሉ፤ የማይደበቅ ጥንካሬና ብርታት ግን ከገጻቸው ላይ በጉልህ ይነበባል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት ጽሕፈት ቤት የትምህርት ባለሞያ በመሆን በማገልገል ላይ ያሉት ንጋቷ ታዬ፣ በሙያው ላለፉት 24 ዓመት አገልግለዋል። ታድያ በሥራቸው ልጆች ትምህርት ሲጀምሩና ምን ያህል ተስፋ የሚጣልባቸው ቢሆኑ በቤተሰብ አቅም ማጣት ሲያቋጡ፣ ሰፌድ እየሠፉና የተለያ ሥራ እየሠሩ ትምህርታቸውን ላለማቋረጥ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ካለበት ሄደው የሚማሩ ተማሪዎችን ያውቃሉ።

በሴቶች ያለውን ፈተና እና ችግር ሳይታዘቡ አልቀሩም። የአካባቢው እንዲሁም የዞኑ ማኅበረሰብ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ስንፍናም ሆነ ቸልታ እንደሌለበት ንጋቷ ይጠቅሳሉ። እድሜያቸው 7 ዓመት የደረሰ ልጆችም በቀጥታ ወደ ቀለም ትምህርት ይገባሉ ብለዋል። ሴቶችን በሚመለከት ግን ሲናገሩ ቀድሞ ነገር አቅምና ገንዘብ ያለው ብቻ ልጆቹን የማስተማር እድል እንዳለው ደግመው አንስተዋል። ለዚህም ከአካባቢው ነዋሪዎች ጥቂት የማይባሉት በኢኮኖሚ ወደኋላ የቀሩና መሬታቸውም በቂ ምርት የማይሰጥ ስለመሆኑ ያስረዳሉ። በዚህም ነው ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑትን እንደ ደብተር፣ መጽሐፍ፣ ልብስና ቦርሳ የመሳሰለ ቁሳቁስ የሚገዙት።

ታድያ ለሴት ልጅ ይህን ተሟሙተውና አቅማቸውን አሟጠው ቢያደርጉ እንኳ እንደ ወሰኔ ያሉ እናቶች እንዳለፉበትና የእነ ወሰኔ ሴት ልጆችም እያለፉበት እንዳለ፣ ስጋት አለ። ይህም በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ነው። ጥቃቱ አሁን ላይ እንደማይኖር ቢነገር እንኳ፣ በነዋሪዎች አእምሮ ያለው ስጋት እረፍት የሚነሳቸው ነው። እናም በተደራራቢ ምክንያት ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ እድላቸው ይጠባል።

‹‹ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት በአካቢው ስለሌለ ርቀው ሄደው ነበር የሚማሩት። ለዛውም ያለው [ገንዘብ ያለው] ነው የሚያስተምረው። ምክንያቱም ቤት ኪራይ አለ።›› ሲሉ ያለውን ሁኔታ ያስረዳሉ። ኢፋ ሰላሌ የተባለው ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመሠራቱ ታድያ በሙያው ለዞኑና ለአካባቢው ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት ላገለገሉት ንጋቷ በጣም ደስ ያሰኘ ሁኔታ ነው።
‹‹ኹለተኛ ደረጃ ከመሆኑ ደረጃውን የጠበቀም ነው። ትምህርት ቤቱ እስከ አሁን በዞኑ ካለው ትምህርት ቤት ሁሉ ደረጃውን የጠበቀና ሁሉም ነገር የተሟላት ነው። ቤተ ሙከራና ቤተ መጻሕፍትም አለው።›› ሲሉ ቀድሞ ይጎድሉ የነበሩና አሁን ላይ ስላሉ ደስ ያሰኟቸውንም ሁኔታዎች ጠቃቅሰዋል።

ትምህርት ቤቱ ታድያ ለዞኑና ለአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ዳር ለሚገኙ ልዩ ዞኖችም ትልቅ ጥቅም እንደሚኖረው ንጋቷ እምነታቸውን ገልጸዋል። ‹‹ብዙ ችገር እንደሚቀርፍ በማሰብ ሁሉም ሰው ነው ደስ የተሰኘበት።›› ሲሉ የደስታውን ነገር ገልጸዋል።

ታድያ ላለው ይጨመርለታል እንዲሉ፣ ተጨማሪ መጠየቅ የሚመጣው ለመጠየቅ አንዳች መሠረት ሲኖር ነው። አሁንም ንጋቷ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ልዩና ጥሩ ሆኖ፣ አሁን ደግሞ እንደ ዞን አዳሪ ትምህርት ቤት ብናገኝ ሲሉ ተመኝተዋል። ክፍሎቹንም ቃኝተው በቂ እንደሆኑና የሚጨመሩት መኝታ ቤቶች ብቻ እንደሚሆኑ አስልተዋል። ‹‹ያ ቢሆንልን ደግሞ የበለጠ ደስ ይለናል። ጎበዝ ተማሪዎቸ በየትምህርት ቤቱ ያሉ ተመርጠው ቢማሩ አድማሱ ይሰፋል። እንደ ዞን ያሉ ጎበዝ ተማሪዎችም ውጤታማ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ።›› ሲሉም የምኞታቸውን ግብ አስረድተዋል።

የኹለተኛ ደረጃ ትምህርትን ዘንድሮ ማለትም በ2012 ነው የጀመረችው። ሐኪም የመሆን ምኞቷን ለማሳካት እንደሚረዳት የምታምንበትን ትምህርቷን አብልጣ ትወዳለች። ኢፋ ሰላሌ ቤተሰቦቿ ጋር ከሚኖሩበት አካባቢ በቅርበት መከፈቱ ደግሞ ሐሳቧን ቀንሶላታል። ‹ከቤተሰብ ርቄ ልሄድ ነው? ትምህርቴን አቋርጥ ይሆን? እየተመላለስኩ ብማር ይሻላል ወይስ በዛው ቤት መከራየት?› የሚሉ ጉዳዮች ያሳስቧት የነበረው ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ሳታጠናቅቅ፣ ወደ ኹለተኛ ደረጃ ዋዜማ ላይ ሆና ነው።

ፍርሃቷን ምንም የሚያደርገው ትምህርት ቤት ግን በድንገት በቅርበት ተከፈተ። በኢፋ ሰላሌ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ፍሬሕይወት ክፍሌ፣ መለስ ብላ ከዓመት በፊት የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች። ‹‹ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያለው መልካ ጡሪ የሚባል አካባቢ ነው። ከምንኖርበት ርቀት ያለው በመሆኑ እዛው ተከራይቼ ልቀመጥ ነበር።›› ፍሬሕይወት ለአዲስ ማለዳ ከተናገረችው ነው።

ያም ሆኖ ትምህርቷን የመቀጠሏና ርቃ የመሄዷ ነገር ቤተሰቦቿን ያሳስብ እንደነበር አልደበቀችም። ‹‹እዛ እንደምማር አስበው ቤተሰቦቼ ይጨነቁ ነበር።›› ብላለች። የአካባቢው ነዋሪ ስጋት ለሴቶቹ ጥቃት ይሁን እንጂ ‹‹ከተማ ያበላሻል›› የሚል እሳቤም አለበት። ፍሬሕይወት ይህን ስታነሳ፣ ‹‹ከቀድሞ ጓደኞቹ ትምህርታቸውን የቀጠሉ አሉ፣ ያቋረጡም አሉ። ከተማ ስትሄዱ ባለጌ ትሆናላችሁ እንባልም ነበር›› ስትል ያለውን አመለካከት ገልጣለች።

‹‹ኢፋ ሰላሌ በቅርበት መከፈቱ ከቤተሰቦቼ እንዳልለይና በቅርብ እንድማር አድርጎኛልና ደስተኛ ነኝ›› ስትል ደስታዋን ገልጻለች። መኖሪያ አካባቢዋ የከተማ መልክ ይዛ ማየት ላደገችበት ስፍራ የምትመኘው መሆኑን ያነሳችው ፍሬሕይወት፣ በትምህርት ውስጥ ለታይታ ያልተቀመጠ፣ ከሌሎች ተቀድቶ እንደሚደገም ልማድ ያልሆነ ተስፋ አላት። አሁንም በትምህርት ቤቱ ያለው ቤተመጻሕፍት እንዲሟላ፣ ቤተ ሙከራውም ቁሳቁስ ሁሉ በደንብ እንዲገባና እንዲሟላለት ጥያቄዋን አቅርባለች።
ለእኩያዎቿም ለተማሪዎች ምንም ያህል ውጣ ውረድ ቢደርስባቸውም ትምህርታቸው ላይ እንዲጎብዙ የሚል ነው።

ተመርቆ ሥራ መፍታትን እያነሱ ትምህርትን የሚረግሙ፣ የትምህርት ስርዓቱን የሚወቅሱ፣ መማር ዋጋ እንደሌለው አረጋግጠናል ያሉ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የውጊያና የጸብ አውድማ ያደረጉ ወዘተ በኢትዮጵያ ጥቂት ሰዎች አይደሉም። እንዲህ ለማለትም የሚያቀርቡት ምክንያት ይኖራል። ያም ሆኖ እንደ ፍሬሕይወት ላሉ፣ ለማማረር እንኳ እንዳይችሉ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ርቋው ለቆዩ፣ ትምህርት የሚያውቁትና ተስፋ የሚያደርጉት ዓለም ነው።

እንደ ወሰኔ ከቤተሰቦቻው በተሻለ ‹በልጄ ላይ ጉዳት ይደርስ ይሆናል› የሚል ስጋት የሚቀንስላቸው ቤተሰቦች ያሉ ሲሆን፣ አሁንም እንደ እርሳቸው፣ ከራሳቸው በተሻለ ደግሞ ለልጆቻቸው የትምህርት እድል ለመፍጠር እድሉን ያገኙ አሉ። ይህ ሁሉ እውቀትን፣ ትምህርትን፣ የተሻለ ሰው መሆንን ፍለጋ ነው።

እድለኛነት ወሰኔ በምትኖርበት አካባቢ ለራስ ፈልገው ያላገኙትን ለልጅ መስጠት መቻል ነው፣ በንጋቷ ሙያና አገልግሎትም ይህን እድል የተጠቀሙ ስኬታማዎችን መመልከት ነው። እንደ ፍሬሕይወት ላሉ ዓለማቸው በትምህርት ቤት ጊቢ ውስጥ ለሚገኝ ደግሞ፣ ስኬት ይህን እውቀትና ትምህርት ካበት አድኖ ማግኘት ነው። እንዲህ ሲመጣ ደግሞ መቀበል።

ኢፋ ሰላሌ
ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በነበረው ሳምንት ማክሰኞ እለት ነበር ከአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፍት ቤት የተነሳው ተሽከርካሪ የጋዜጠኞችን ቡድን ይዞ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ያቀናው። የጉዞው ዓላማ በዞኑ በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባውን ኢፋ ሰላሌ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመመረቅ ነው።

በውጫሌ ወረዳ ቦሶቄ ጃቴ ቀበሌ ግንባታው ተጠናቆ መስከረም 2012 አገልግሎት መስጠት የጀመረውን ትምህርት ቤት ያስገነቡት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ሊመርቁ እንደሚመጡ የአካባቢው ነዋሪ በመረዳቱ፣ ቀድሞ ነበር ጊቢውን ሞልቶ የጠበቀው። የሰላሌ ፈረሰኞችም ፈረሶቻቸውን አስጊጠው እንግዳቸውን መጠበቅ የጀመሩት ቀድመው ነው። ምንም እንኳ እንደ ዜጋ ትምህርት የማግኘት መብት ቢኖራቸውና ያንንም ማሟላት የመንግሥት ግዴታ ቢሆንም፣ በበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት አሠርቶልናል ብለው እንደተዋለላቸው ውለታ እልል ብለው የሠሩላቸውን ያመሰግኑ ነበር።

‹‹ኢፋ ሰላሌ›› ትርጉሙ የሰላሌ ብርሃን ነው። ይሄ የሰላሌ ብርሃን የተባለ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 16 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ቤተ መጻሕፍት እና የሠራተኞች ቢሮን ያካተተ ነው። ትምህርት ቤቱን ለማገንባትና ለመጨረስ ከ13 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገም በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ተነግሯል። በዚህም እንደ ፍሬሕይወት ያሉ 800 ትምህርት ፈላጊዎችን የመቀበል አቅም እንደሚኖረው ተደርጎ እንደተሠራም ከመድረክ ሲገለጽ ነበር።

ትምህርት ቤቱን የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ብቻውን ያስገነባው ሳይሆን ጉዲና ኩምሳ የተባለ ፋውንዴሽንም ጉልህ አስተዋፅኦ ያደረገበት ነበር። ይህንንም ቀዳማዊት እመቤቷ በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት አጭር ንግግር የጠቀሱት ነው።

ሚያዝያ ወር 2011 ላይ የመሠረት ድንጋዩ የተጣለው ትምህርት ቤቱ፣ በሰኔ ወር የተጀመረ ግንባታው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለ2012 የኹለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መድረስ ችሏል። በዚህም አሁን ላይ 158 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ እንደተገለጸው፣ በመላ አገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች 20 የሚሆኑ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት እቅድ ይዟል። ይህንንም እውን ለማድረግ እንቅስቃሴው በጉልህ እየታየ ነው። ታድያ አሁን ላይ ከዚህ እቅድ ውስጥ የተሳኩት ሲቆጠሩ፣ ኢፋ ሰላሌን ጨምሮ አምስት ደርሰዋል። ይህም ማለት ከተያዘው እቅድ ውስጥ ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአገሪቱ የተለያዩ ከተማዎች የሚገኙ ናቸው።

ትምህርት ቤቱ ሲመረቅ ታድያ አጠር ያለ ንግግር ያደረጉት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ፣ በስፍራው ትምህርት ቤቱን ለመመረቅ ለተገኙ የአካባቢው ነዋሪዎችና ተማሪዎች መልእከት አስተላልፈዋል፣ ለሥራውሥኬት እጃቸውን ለሰጡና ላገዙ የምስጋና እና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል። እርሳቸውም ከዞኑ የምስጋና ጋቢ ደርበዋል። በንግግራቸውም ‹‹እንደራሳችሁ ንብረት እንድትይዙት አደራ እላለሁ።›› ሲሉ የሰላሌ ብርሃን ሥራቸውን ጨርሰው ደግሞ ለሌሎች ተመሳሳይ ብርሃን የሚሆን ሥራን አስተባብሮ ለመሥራት አቅንተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here