ሠላም የራቃት “ሠላም አስከባሪ”

0
922

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የእርስ በርስ ጦርነት ከከፋባቸው ሶሪያ፣ አፍጋኒስታንና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የበለጠ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ያለባት መሆኗን በስደተኞች ላይ የሚሰሩት የተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ ኤጀንሲዎች መረጃ ያመለክታል። አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን አትዮጵያዊያን በግጭትና ተያዥ ምክንያች በአገር ውስጥ ተፈናቅለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያን በዓለም ዐቀፍ መድረክ ከአውሮፓዊኑ 1951 የኮሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ጀምሮ ሠላም አስከባሪ ወታደሮችን በማሰማራት ለሠላም ዘብ የቆመች አገር ይላታል። እስካሁን ከ80 ሺህ በላይ ሠላም አስከባሪዎችን ማሰመራቷንም ያመለክታል፡፡
የአፍሪካ ቀንድ በዓለም ግጭት ከሚበዛባቸው ቀጣናዎች መካከል መሆኑን ይታወቃል። የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሙሃቤ መኮንን ‹‹The root cause of conflict in the Horn of Africa›› በሚል ርዕስ በ‹አሜሪካን ጆርናል ኦፍ አፕላይድ ሳይኮሎጂ› ገፅ ላይ ያወጡት ጽሑፍ ቀጣናው ቋንቋን መሠረት ባደረገ የብሔር ግጭት፣ የሃይማኖት አክራሪነት እና አሜሪካን ጨምሮ ስልታዊ ፍላጎትን የማስፈጸም እንቅስቃሴ ያልተለየው መሆኑን ያመለክታል፤ ኢትዮጵያም ከእነዚህ ፈተናዎች አላመለጠችም።
ኢሕአዴግ መር መንግሥቱ ሲያጋጥሙት ለነበሩት አለመረጋጋቶች የተለመዱ ውጫዊ ምክንያቶችን ከመደርደር አልፎ ወደ ውስጥ መመልከት በጀመረበትና ሕዝባዊ ተቃውሞ በበረታበት ሁኔታ የአመራር ለውጥ ለማድረግ ተገድዶ ዐቢይ አህመድን (ዶ/ር) የድርጅቱ ሊቀ መንበርና ጠቅላይ ሚንስትር አድርጓል። መንግሥት ከሚፈጠሩ ግጭቶች ጀርባ ‹‹በለውጡ ጥቅማቸው የተነካባቸው ኃይሎች›› አሉ ከሚል አዲስ ትርክት አምጥቷል። በቅርቡም ከሰብኣዊ መብቶች ጥሰትና ሙስና ወንጀል ጋር ተያያዘ ተጠርጣዎችን መያዝ መጀመሩን ይዝለቅለት አስብሏል።
የፌደራሊዝም አወቃቀርና ግጭት
አንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ማኅበራት መግለጫዎችና የፖለቲካ ተንታኞች አስተያየት ቋንቋን መሠረት አድርጎ የተዋቀረው የብሔር ፖለቲካና የክልሎች አደረጃጀት ሊቀየር እንደሚገባው የሚያሳሳቡ ናቸው። ኢሕአዴግ በበኩሉ የፌደራሊዝም ሥርዓቱ በራሱ የግጭት ምንጭ ሳይሆን ከአፈፃፀም ጉድለት የመነጨ መሆኑን ይገልጻል። በጀርመኗ ፍራንክፈርት ውይይት ያካሄዱት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ‹‹የክልል አደረጃጃት ቀርቶ ለምን ክፍለ ሀገር አይሆንም›› በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ከውሳኔ በፊት ጥልቅ ጥናትና ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ መናገራቸው መናገራቸው ይታወሳል።
በዚህ ሐሳብ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ መኮንን ፍስሃ ይስማሉ። ፌደራሊዝሙ በራሱ የችግር ምንጭ አይደለም። ‹‹ብሔር ወይም ሞት›› በሚባልበት አገር አከላለሉን ወደ መልከዓ ምድራዊ አቀማማጥ ይቀየር ቢባል የሚሰማ የለም፤ የመገንጠል መብትን መነሻ በማድረግ የራሴን አገር ልመስርት እስከሚል ንትርክ ያደርሳልም የሚል ሥጋታቸውን ይገልጻሉ። አንድ ቋንቋና ሃይማኖት ባላት ሶማሊያም መረጋጋት እንደሌለ በመጥቀስ ችግሩ የሚመጣው ልዩነትን ከማስተዳዳር አቅም ጋር ተያይዞ እንደሆነም ያምናሉ።
ይልቁንም መንግሥት ‹‹የኢትዮጵያ ችግር ምንድነው?›› የሚለውን መለየት ያስፈልገዋል የሚሉት መኮንን መንግሥት ችግሮችን ሁሉ ውጫዊ አድርጎ ከመመልከት ይልቅ ወደ ውስጡ ማየት እንዳለበት ይሞግታሉ። የሚያዋጣው ያለፈውን ችግር ለይቶ የጋራ አገር መገንባት እንደሆነ በመጠቆም ‹‹የኢትዮጵያ መሪዎች ችግራቸው ወደፊት ሳይሆን ወደኃላ ስለሚያዩ ነው›› ሲሉም ያክላሉ።
በሌላ በኩል ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች ናቸው›› የሚለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ስምንት እንዲሁም የመሬት ባለቤትነት የሚያትተው አንቀጽ 40ን ጨምሮ በተለያዩ የሕገ መንግሥቱ ክፍሎች ላይ ከግለሰብ ይልቅ ለቡድን የጎላ ሥፍራ መስጠቱ እያጋጠሙ ላሉ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃትና ግጭቶች መነሻ ነው የሚሉ ወገኖች ግጭቶቹና የሠላም እጦቱ የመጣው ኢትዮጵያዊነት እንዲከስምና የብሔር ማንነት እንዲጎላ ሲሰራ በመቆየቱ ነው ሲሉ ይደመጣል።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በቅርቡ ለአንድ የአገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደገለጹት በሥልጣን ዘመናቸው ሳይሰሩት በመቅረታቸው የሚቆጫቸው ኢትዮጵያዊነትን እያኮሰሰ የብሔር ማንነትን አገንግኗል የሚባለውን የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች በዓል አለማስቀረታቸው ወይም አለማስተካከላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶች መነሻ ኢትዮጵያ ለውጥና ሽግግር ላይ በመሆኗ ነው ይላሉ። ሆኖም በለውጥ ሂደት ሥልጣንና ጥቅምን ያጡ ወገኖች በአንድ በኩል፤ ለረጅም ዘመናት ተረግጦ የነበረ ሕዝብ ከጠብመንጃ ተላቆ ወደ አዲስ ለውጥ መግባቱ በሌላ በኩል የግጭቶች መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው።
ይሁንና የብሔር ፌደራሊዝሙም ለሚነሱ ግጭቶች የራሱ ድርሻ እንዳለው የሚያነሱት የሺዋስ ‹‹የሕወሓት ፕሮግራም ወደ ኢሕአዴግ ፕሮግራም ከፍ ማለቱና ሕገ መንግሥቱም ቢሆን አገር ለማፍረስ የተሰራ በመሆኑ፣ የክልሎች ሕገ መንግሥትም ክልሉ የዚህ ብሔረሰብ ነው፤ ሌሎቹ መኖር ይችላሉ የሚሉ በመሆናቸው እንዲያውም ከተተበተበው አንጻር ያጋጠመው ችግር ቀላል ነው›› ይላሉ።
የአመራር ለውጡና የሕግ የበላይነት
የአመራር ለውጡ ከተደረገ መጋቢት 24/2010 ወዲህም ቢሆን በሚፈጠሩ ግጭቶች ሰዎች ሞተዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትም ከመኖሪያ ተፈናቅለዋል። አንዳንዶች በኢትዮጵያ ከጥቂት ወራት ወዲህ ግጭቶችና የሠላም እጦት ተበራክተዋል ይላሉ። ይሁንና ከስምንት ወር በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያ ከዛሬዋ ጋር ማነጻጸር ተገቢ አይደለም የሚሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የአገር ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን በማስታወስ ግጭቶቹ በቅርቡ በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉ ተስፋቸውንም ይገልጻሉ።
በቀድሞው የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር የግጭት ቅደመ ማስጠንቀቂያና ዘላቂ መፍትሔ ዳይሬክተር ጀነራሉ (አሁን በሠላም ሚኒስቴር የሕግ ዘርፍ ውስጥ የተካተቱት) ንጋቱ አብዲሳ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ሰው በኢትዮጵያዊነቱ በፈለገው ቦታ መሥራት ከቻለ ብቻ ሠላም እንደሚመጣ ያምናሉ። አሁን እየተስተዋለ ያለው ‹‹ያንተ አይደለም ከዚህ ውጣ›› የሚል ነገር ካልቀረ አስቸጋሪ እንደሚሆንም ያነሳሉ። እንደ ንጋቱ አንድ ቦታ ያጠፋ ወንጀለኛ ተገቢው ፍርድ ቢወሰንበት ሌላ አካባቢ ግጭት ሊቀሰቅስ ያሰበ ሰው ይፈራ ነበር፤ ይህ ባለመሆኑ ግን አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት ነው ይላሉ።
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በበኩላቸው ‹‹እኛ ከምንሠራው አንዱ ግጭት እንዳይከሰት መከላከልና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው። ይህ ሲባል ግጭት ጠንሳሹ፣ አነሳሹና ፈፃሚው በሕግ መጠየቅ አለባቸው›› ይላሉ። እንደኮሚሽነር ምትኩ እምነት የሕግ የበላይነት እስካልተረጋገጠ ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ለሚፈናቀሉ ሰዎች ጭምር አስቸኳይ ድጋፍ ለማድረግ ፈተና ሆኖ ይቀጥላል።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው መኮንን በኢትዮጵያ ግጭት አዲስ አለመሆኑን በመጠቆም ዋናው ችግር በብዙዎች ዘንድ ‹‹የተገኘውን ዕድል ለግል የመጠቀም ፍላጎት ስላለ ነው›› ባይ ናቸው። የትጥቅ ትግልን የመረጡ ፓርቲዎችን ጨምሮ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውንና በርካታ የመገናኛ ብዙኃንም መከፈታቸውን የሚያስታውሱት መምህሩ ‹‹በዚህ ሁሉ ሒደት ግን ሁሉን የሚግባባ ሕግና ሥርዓት አልተበጀም›› ይላሉ። የመንግሥት ሁሉን ነገር ክፍት ማድረግም ዋጋ እንደሚያስከፍል ያነሳሉ። ችግሩ ውስጣዊ ቢሆንም ውጫዊ ምክንያቶች እንዳሉም ያነሳሉ። ጎረቤትና ሌሎች አገራት በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ፍላጎት በየዋህነት ማየቱም እንደማያዋጣ ያሰምሩበታል።
መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማስከበር ተስኖታል፤ አሁንም ግጭቶች አሉ የሚሉ ጥያቄዎች የተነሳባቸው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ችግሮች መኖራቸውን አምነው በጋራ በመቆም መሻገር እንደሚቻልና ኢትዮጵያ የተሻለች አገር እንደምትሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በኅዳር 13/2011 የተወካዮች ምክር ቤት ውሏቸውም ‹‹ሁሉንም ወንጀለኛ እንያዝ ከተባለ እስር ቤት ሳይሆን ከተማ ነው መገንባት ያለብን›› ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከትንሽ እስከ ትልቅ ወንጀል ያልተነካካ ሰው እንደሌለ በመጠቆም ሁሉንም አስሮ የሚሰራ ኃይል ከማጣት ዋና ዋና ችግሮች ላይ ማተኮሩ እንደሚበጅ መክረዋል፡፡
ክልሎችና የፌደራል መንግሥት ተሰሚነት
አቶ ንጋቱ ‹‹ክልሎች ላይ ተጠያቂነት ቢኖር ኖሮ አንድም ሰው አይሞትም ነበር፤ እራሳቸውን እንደመንግሥት ቆጥሮ ያለመታዘዝ ተግባር አለ›› ይላሉ። ክልሎች የቅድመ አደጋ አመላካች መረጃን ያለመስጠት ዳተኝነት እንዳለባቸው የሚያነሱት የሥራ ኃላፊው የችግሩ ምልክት እየተስተዋለና ግጭት ለመቀስቀስ ውስጥ ውስጡን እየተሰራበት እንደሆነ እየታወቀ እንኳን ክልሎች ለፌደራሉ መንግሥት ‹ሠላም ነው› የሚል መረጃን በመስጠት የመሸፋፈን ሥራ እንደሚሰሩ ያክላሉ። ለዚህም ማሳያው ምንም ችግር የለም በተባለ ማግስት ግጭት ተፈጥሮ ሰዎች ሲሞቱና ከቀያቸው ሲፈናቀሉ መስተዋሉን ያለነሳሉ። በዚህ ሂደት የፀጥታ ኃይሉም ትዕዛዝ አልተሰጠኝም በሚል ዳተኝነት እንዲሁም በመንግሥት በኩል ግጭትን በእንጭጩ ያለመፍታት ችግር መኖሩንም ያነሳሉ። መኮንን በበኩላቸው መንግስት ግጭቶችን የመተንበይና የመከላከል፣ ከሥሩ የመፍታትም ችግባር አለበት፤ እየሠራ ያለውም ለታይታ ይመስላል የሚል እምነትም አላቸው።
የሺዋስም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ቀድሞውኑ የክልሎች አፈጣጠር አገር ለማፍረስ አልሞ የነበረ መሆኑንም ያነሳሉ። በኢትዮጵያ ሕግ በሃይማኖት ተደራጅቶ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት እንደማይቻለው በብሔር (ጎሳ) የተደራጀም ሆነ የሚደራጅ እየከሰመ የሚሄድበት በመጨረሻም በርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተ ፓርቲ የሚሆንበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልጋልም ይላሉ። በኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ሥርዓት ላይ የተደረጉ ጥናቶች ግን በብሔር መደራጀት የሙጥኝ የተባለበት ምክንያት ሥልጣንን ለመያዝ አቋራጭ መንገድ ሆኖ ማገልገሉ ይጠቅሳሉ።
መፍትሔውስ?
አቶ ንጋቱ፤ የሠላም ሚኒስቴርን ማቋቋም ጥሩ ሆኖ ሳለ ዋነኛ የግጭት መንስዔዎችን ከሥረ መሠረታቸው መፍታት እንደሚገባ ያሰምሩበታል።
መኮንን በበኩላቸው የኢትዮጵያ ችግር የ27 ዓመት ብቻ ሳይሆን የዘመናት ችግር በመሆኑ መንግሥታት መጀመሪያ ከአሸናፊነትና ተሸናፊነት ስሜት መውጣት፣ በማይግባቡበት ላይ ከመጨቃጨቅ በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራትን ማስቀደም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከክልል አጥር ወጥተው አገራዊ መሆን እንደሚገባቸው ይጠቅሳሉ። አሁን ያለው ፌደራሊዝም ነው ችግሩ ተብሎ በስሜት ይቀየር ወደሚል ውሳኔ መሄዱም የከፋ ዋጋ እንደሚያስከፍል በመግለጽ ጥልቅ ጥናትና ውይይት ያስፈልጋል በሚለው የጠቅላይ ሚንስትሩ ሐሳብ ይስማማሉ።
የሺዋስ መፍትሔው ለውጡን ተቋማዊ ማድረግ እንደሆነ ያምናሉ። ለውጥና ሽግግር ላይ ነን ከማለት ባለፈ እንዴትና እስከመቼ በለውጥ ሽግግር የሚለውን የሚመልስና ተቋማዊ ቅርጽ እንዲያዝ የሚያደርግ፤ መንግሥትና የማኅበረሰብ መሪዎችን ያካተተ ሁሉን ቀፍ ውይይት አድርጎ ‹‹የሽግግር ጉባኤ (ምክር ቤት)›› በመመስረት ስለሠላምና መረጋጋት አልፎም ስለምጣኔ ሀብት እድገት በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ። በተጨማሪም በሚፈጠሩ ግጭቶች ተጠያቂዎች ላይ አፋጣኝና አስተማሪ ሕጋዊ እርምጃ እየወሰዱ ለሕዝብም ግልጽ እያደረጉ መሄድ እንደሚገባ ይመክራሉ።
የእርቀ ሠላም ኮሚሽን እየተደራጀ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከራሱና ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዲታረቅ እያደረጉ መሄድን ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ይህ ካሆነ ግን መጠፋፋቱ ቀጣይ እንደሚሆን መክረዋል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here