የአፋር ገዢ ፓርቲ 72 አባላቱን አሰናበተ

0
744

ጉባኤ ላይ ተቀምጦ የሰነበተው የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ሊቀ መንበርና የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሀጂ ሥዩም አወል እና ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 72 የድርጅቱን አባላት በክብር አሰናብቶ፥ አዳዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አመራሮችን መረጠ።
በአፋር ክልል የለውጥ እንቅስቃሴ አለመኖሩን በመጥቀስ የክልሉ መንግሥት የወጣቱን ጥያቄ እንዲያዳምጥና መልስም እንዲሰጠጥ የሚጠይቁ ሰለፎች በቅርቡ በአፋር ክልል የተለያዩ ከተሞች ሲደረጉ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህም ውጥረት ውስጥ የገባው የክልሉ መሪ ድርጅት በቅርቡ በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ስብሰባ ማድረጉ አይዘነጋም። በስብሰባው መጨረሻም አመራሮቹ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገው የአመራር ለውጥ ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸውም ነበር።
ይህን ተከትሎ በሰመራ 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን ሲያካሒድ የሰነበተው አብዴፓ 72 የድርጅቱን ከፍተኛ አመራርና አባላቱን በክልሉ በነበራቸው የሥራ ዘመን ላበረከቱት ሚና የምስጋና ሽልማት አበርክቶ አሰናብቷቸዋል።
በምትካቸውም ከተጠቆሙ 50 ዕጩ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት 45ቱን የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አድርጎ መርጧል።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here