በአንድ ሳምንት ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የኮንትሮባንድ ዕቃ ተይዘ

0
783

በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግምታዊ ዋጋቸው ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የኮንትሮባንድ ዕቃዎችም የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ ጎማ፣ ማዕድን፣ ሲጋራ፣ ጀኔሬተሮች፣ አልባሳት፣ ዘመናዊ መገናኛ ሬዲዮዎች፣ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች፣ አደንዛዥ ዕፅ፣ የጦር መሣሪያዎች፣ ተሸከርካሪዎች እንዲሁም ብዛት ያላቸው የተለያዩ ዓይነት ዕቃዎች መሆናቸው ተገልጿል።

እነዚህ ሕገ-ወጥ ዕቃዎች በጅግጅጋ፣ ሞያሌ፣ አዋሽ፣ ኮምቦልቻ፣ አዋሳ፣ ሞጆ፣ ጅማ፣ ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ እና በሌሎች የኬላ ጣብያዎች በጉምሩክ ሠራተኞች፣ የጸጥታ አካላት እና በአካባቢው ኅብረተሰብ ድጋፍ በተደረገ ከፍተኛ ቁጥጥርና ፍተሻ መያዛቸው ታውቋል።

የሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች እና የተለያዩ የውጭ አገራት ገንዘብ አስተላላፊዎች፣ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚያዘዋውሩ ሲሆን መንግሥትም ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የአገርቷን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያዳክምና ሕጋዊ ነጋዴዎችን ከንግድ ውድድር በማስወጣት ላይ ያለ ተግባር በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ መሰል ድርጊቶችን ሲመለከት ጥቆማ እንዲያቀርብ ተጠይቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here