የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማእከላት ሊገነቡ ነው

0
774

በ91 ሚሊዮን ብር 10 የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማእከላትን መገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከ8 የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ከኹለት ሥራ ፈጣሪ ኤጀንሲዎች ጋር ተፈፅሟል። ስምምነቱም የግብርናውን ዘርፍ በዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎች የታገዘ ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

ማእከላቱ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ትግራይ ክልሎች የሚገነቡ ሲሆን፥ የማእከላቱ ግንባታ 70 በመቶ ወጪ በኤጀንሲው የሚሸፈን ይሆናል ተብሏል። ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ በኅብረት ሥራ ማኅበራቱ የሚሸፈን ይሆናል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካሊድ ቦምባ፥ የግብርና ሜካናይዜሽን ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈም የአነስተኛ ማሳ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻል እንደሚረዳም ጠቁመዋል።

ማእከላቱ ከመሬት ማለስለስ እስከ ምርት መሰብሰብና ማጓጓዝ ድረስ ባለው ሂደት ለአርሶ አደሮች እገዛ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳሉ።
አገልግሎቱ የግብርና ሚኒስቴር በዴንማርክ እና ኔዘርላንድስ መንግሥት ድጋፍ ለሦስት ዓመታት የሚተገበረው የሙከራ ፕሮጀክት መሆኑም በፊርማ ስነ ስርአቱ ወቅት ተገልጿል። የማእከላቱ ውጤታማነት እየታየም ፕሮጀክቱ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በቀጣይነት እንደሚተገበር ኤጀንሲው አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here