በኢትዮጵያ የመቀንጨር መጠን ከ60 በመቶ ወደ 37 በመቶ ቀነሰ

0
519

በስርዓተ ምግብ ዙሪያ በተሠሩ ሥራዎች አገር አቀፍ የመቀንጨር መጠን ከ60 በመቶ ወደ 37 በመቶ መቀነሱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከአማራ ክልል ለደሃና፣ ዝቋላና ጋዞ ከትግራይ ክልል ደግሞ አፍላና ቆላ ተንቤን በሽታውን ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት በማድረጋቸው እውቅና ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም ለሌሎች አምስት ወረዳዎች ዕውቅና መሰጠቱንም ከጤና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ሕፃናት ዳይሬክተር መሠረት ዘላለም (ዶር) በስርዓተ ምግብ ዙሪያ በተሠሩ ሥራዎች አገር ዐቀፍ የመቀንጨር መጠን የቀነሰ ቢሆንም፣ የሚቀረው ሥራ የበለጠ በመሆኑ ብዙ መሥራት ይገባል ሲሉ የመንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤቶችንና የአጋር ድርጅቶችን የስድስት ወር አፈፃፀም የተመለከተ ምክክር በተደረገበት ወቅት ተናግረዋል።

መቀንጨር የሕፃናት ዕድሜ እና ቁመት ሳይመጣጠን ሲቀር የሚከሰት የጤና ችግር ሲሆን፤ ከአካል መቀጨጭና ከቁመት ማጠር ባሻገር በአዕምሮ ላይ ጉዳትን ያስከትላል። በዚህም ምክንያት አገሪቱ መከላከል በሚቻል በሽታ በዓመት 58 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እያጣች መሆኑንም ይገለጻል።

በሽታው ባልተመጣጠነ የሥነ ምግብ ስርዓት ምክንያት የሚከሰት መሆኑን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ የምግብ እና ስርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት እንደሆነ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መናገራቸው ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here