ማረሚያ ቤቶች ካስገኙልን መጻሕፍት አንዱ

0
751

አበራ ጀምበሬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የሕግ እና ፍትሕ ስርዓት ላይ ተጠቃሽ የሆነ “የኢትዮጵያ ሕግና የፍትሕ አፈፃፀም ታሪክ” የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል። ብርሃኑ ሰሙ መጽሐፋቸውን አንብበው ይዘታቸውን በቅምሻ መልኩ ያቋድሱናል።

ማረሚያ ቤቶች ጽሑፍ ሊሆኑ ለሚችሉ አያሌ ሐሳቦች እንዲወጠኑና ለበርካታ መጻሕፍት መጻፍ ምክንያት የሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ደራሲ ሲሳይ ንጉሡ በዩኒቨርስቲ ቆይታው በአራት ዓመታት ከገበየው ዕውቀት ይልቅ ለአንድ ዓመት በእስር ባሳለፈው ጊዜ ያገኘው ትምህርት ከፍ እንደሚል ከዓመታት በፊት በአንድ መድረክ ላይ ሲናገር መስማቴን አስታውሳለሁ። ደራሲና ጋዜጠኛ አብርሃም ረታ ዓለሙ (አፈሩ ይቅለለው) “የሕይወትና የነጻነትን ትርጉም ለመረዳት ከማረሚያ ቤት የተሻለ ማሳያ የትም አይገኝም” ይል ነበር።
ለዚህ እውነታ አበራ ጀምበሬ (ዶ/ር) ተሰናድቶ፣ ለአንባቢያን የቀረበው “የኢትዮጵያ ሕግና የፍትሕ አፈፃፀም ታሪክ” የተሰኘ መጽሐፍ አንዱ ማሳያ ነው።
ደራሲው በ1960ዎቹ የኢትዮጵያን ሕግና ፍትሕ አፈፃፀም ታሪክ አጥንተው፣ በመጽሐፍ ሰንዶ የማቅረብ የቆየ ዕቅድ ነበራቸው። በሥራ ጫና፣ በሕይወት ውክቢያና የዕለት ግርግር ምክንያት ያሰቡትን እውን ማድረግ ሳይችሉ ዓመታት ተቆጠሩ። ደርግን ወደ ሥልጣን ያበጣው፣ የ1967ቱ አብዮት አበራ ጀምበሬ ተጠምደውበት ከነበረው “ከፍተኛ ኃላፊነት” ተገልለው፣ በፖለቲካ እስረኛነት ማረሚያ ቤት እንዲገቡ ምክንያት ሆነ። ይህ ደግሞ ደራሲው ምኞታቸውን እውን እንዲያደርጉ አስተዋጽኦ እደረገ።
ለስምንት ዓመታት በታሰሩበት ሆነው፣ ዕቅዳቸውን እውን ማድረግ ስለሚችሉበት ሁኔታ ማጥናት ጀመሩ። “በአዲስ አበባ ታላቁ ቤተ መንግሥት የዙፋን አዳራሽ ምድር ቤት /ደይን/ ውስጥ” አብረዋቸው ታስረው ከነበሩት ታሳሪዎች፣ “ለዕቅዴ” ይጠቅመኛል ያሉትን መረጃ በማጠያየቅ ጥናታቸውን ጀመሩ። ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተለያዩ መጻሕፍትና ጽሑፎችን በማፈላለግ በርካታ መረጃ አሰባሰቡ። እስር ቤት ውስጥ እያሉም የጥናታቸውን ግማሽ ያህል መረጃ ማደራጀት ቻሉ። “ተጨማሪ የዕውቀት ጥማቴን ለማርካት እበቃ ዘንድ እንደ ገና ከኅብረተሰቡ መካከል ለመቀላቀል እንዲያበቃኝ ሁሉን ማድረግ የማይሳነው ፈጣሪን በፀሎት ተማጸንኩ” ይላሉ።
ከእስር ከተፈቱ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ ፋካልቲ እያስተማሩ፣ በማረሚያ ቤት የጀመሩትን ጥናትና ምርምር ከግቡ ለማድረስ በሥራው ቀጠሉበት። በ2006 በሻማ ቡክስ አሳታሚነት፣ በ424 ገጾች ተጠርዞ ለአንባቢያን የቀረበው የአበራ ጀምበሬ “የኢትዮጵያ ሕግና የፍትሕ አፈፃፀም ታሪክ” መጽሐፍ ከ1426 እስከ 1966 ባለው ዘመን ተቀንብቦ የቀረበ ነው። ከዚህ ዘመን በፊትና በኋላ ያሉት የኢትዮጵያ የሕግና የፍትሕ ታሪክ በመጽሐፉ ለምን እንዳልተካተቱ በጥራዙ መግቢያ የሚከተለው መረጃ ሰፍሯል።
“የኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ በሦስት ተከፍሎ ሊጠና ይችላል። የመጀመሪያው ክፍል ከ1426 ከዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በፊት ያለውን ረጂም ዘመናት የሚያጠቃልል ሲሆን፣ ይህ የታሪክ ክፍለ ዘመን አጥጋቢ መረጃ በጽሑፍ የማይገኝለት በመሆኑ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ይዘቱ አልተካተተም። ሁለተኛው የታሪክ ክፍለ ዘመን በዚህ ጸሐፊ አስተሳሰብ ከዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ያለው ሲሆን፣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ትኩረት የተሰጠው ይኸው ክፍለ ዘመን ነው። የሦስተኛው የታሪክ ዘመን ከ1966 መጨረሻ እስካሁን ያለው ሲሆን፣ የዚህን ዘመን የሕግ ታሪክ በሌላ ጽሑፍ ለማቅረብ ሙከራ ይደረጋል። ይህም ዘመን ከሌሎቹ የታሪክ ዘመናት በጣም አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ ሥር ነቀል ለውጦች የተደረጉበት በመሆኑ፣ ለውጡ በሕግ ዕድገት ላይ ያስከተለውን ሁኔታ ከፊተኛው ዘመን ጋር ለማነፃፀር ሰፊ ምርምር ማድረግን ይጠይቃል።”
መጽሐፉ በጥናትና ምርምር ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀ በመሆኑ፣ ጥናቱ የተመራበት ቢጋር (ፕሮጀክት) ምን እንደነበር የጥራዙ አካል ሆኖ ቀርቧል። ዓላማው፣ ትኩረቱ፣ የአቀራረብ ዘዴው፣ የጥናቱ ርዕሰ ቃላት ትርጉም… ተብራርቷል። መጽሐፉ በስምንት ክፍሎቹ ሃያ አንድ ምዕራፎችን ያዟል። እያንዳንዱ ክፍል መግቢያ ወይም ጠቅላላ መግለጫ አለው። የኢትዮጵያ ታሪክ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ፣ የፖለቲካው፣ የባሕሉ፣ የሃይማኖቱ… ታሪክ አካል የሆነው ሕግና ፍትሕ በየዘፍፉ ምን እንደሚመስል አጠቃላይ መግለጫ እየተሰጠ ነው ወደ ዝርዝር ጉዳይ የሚገባው።
“የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምጥን ታሪክ” በሚል ርዕስ በምዕራፍ 2 በቀረበው ጹሑፍ “የኢትዮጵያ የክርስቲያን መንግሥት ለታሪካዊ መለያው አካል የሆነውን ነገሥታቱንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚያጠቃልል ሁኖ አመሠራረቱ ወደ ኋላ ከዘመነ አክሱም ይጀምራል።” ከዚህ አንስቶ እስከ ዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የዘለቀው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ታሪክ “የኃይለኛ ሰው ሥርዓት” የተፈራረቀበት እንደነበር አንዱ መሳያ “የሽኩቻ አሸናፊ” ሆነው በ1923 ዘውድ የደፉት ዐፄ ኃይለሥላሴ ናቸው።
ንጉሡ ሥልጣን እንደጨበጡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን በማቋቋም፣ የተወካዮች ምክር ቤትን በማደራጀት፣ የመጀመሪያውን የተጻፈ ሕገ መንግሥት በማውጣት… “ዘመናዊ ፕሮግራም ማካሔድ ጀምረው” ሕዝብና አገሪቱን በተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን ለውጥ ከማድረግ ይልቅ “ኃይለኛነታቸውን” የሚያስጠብቅላቸውን መንገድ በመከተላው፣ በውጤቱ “በሥልጣን ላይ ለመቆየት ከዲሞክራሲያዊ ሒደት ይልቅ በፖለቲካ ጨዋታና በወታደራዊ ኃይል ላይ በበለጠ በመተማመናቸው በ1966 ከሕዝባዊ አመፅ በኋላ ወደ ሥልጣን በመጣው ወታደራዊ ጁንታ ሥልጣናቸውን ተነጠቁ።”
የዕውቀቶች ሁሉ የበላይ የሆነው ፍልስፍና (የጥበብ ፍቅር)፤ በሕግና ፍትሕ አፈጣጠር፣ አረዳድ፣ አተገባበርና ትርጉም… ላይ ያለው ሚና ምን እንደሚመስል፤ በኢትዮጵያ የሕግ ፍልስፍና የዳበረው በምን መሠረት እንደሆነና መነሻውን በምሳሌያዊ አነጋገሮች ውስጥ ማግኘት እንደሚቻል፣ ሕዝባዊ ብሒሎች በአገራችን ለሕግና ለፍትሕ መከበር ጠንካራ ፍላጎት እንዳለ አንዱ ማሳያ ስለመሆናቸው በመጽሐፉ ገጽ 31 ሕጋዊ ይትበሃልና ትርጉሙ ቀርቧል።
“‹በፍርድ ከሔደች በቅሎዬ፣ ያለፍርድ የተበላች ዶሮዬ ወይም ጭብጦዬ› የሚለው አነጋገር፣ ሰው በፍርድ ከሚያጣው ከፍተኛ ሀብት ይልቅ አነስተኛ ሀብት ያለፍርድ፣ ያለአግባብ ሲሔድበት፣ በሕግ የተጠበቀ መብቱ ስለተነካበት ብቻ ያለመጠን እንደሚቆጭና ለሀብትነቱ ብቻ ሳይሆን ለመብቱ ማስከበርም ሲል፣ ከበታች ፍርድ ቤት እስከ መጨረሻው የፍርድ ባለሥልጣን ድረስ ሕጋዊ ክርክሩን በማቅረብ እንደሚሟገት ያዘክራል።” ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአበራ ጀምበሬ መጽሐፍ፣ ከገጽ 393 እስከ 417 በ36 ንዑስ ርዕሶች የተከፋፈሉ፣ 259 የሕግ ይትበሃላት /Legal Maxims/ አቅርቧል።
‹የኢትዮጵያ ሕግና የፍትሕ አፈፃፀም› ምን እንደሚመስል፣ በጥልቅ ምርምር ላይ ተመሥርቶ የተሠራውና ምድቡም ከታሪክ መጻሕፍት አካል የሆነው የአበራ ጀምበሬ መጽሐፍ፤ በማመሳከሪያ ሰነድነቱ፣ ለዘርፉ ባለሙያዎችና ለመምህራን ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ለጥናትና ምርምር አድራጊዎች፣ ለጠቅላላ ዕውቀት አንባቢያን ያለው ጠቀሜታም ቀላል የሚባል አይደለም። ተደራሲያን መሥመር በመሥመር ወይም ቃል በቃል (ከሀ እስከ ፐ) ማንበብ ሳያስፈልጋቸው፣ በንዑስ ርዕስ ከቀረቡት ጽሑፎች፣ የሚፈልጉትን በየገጹ መርጦ በማንበብም፣ ብዙ መረጃና ዕውቀት መቃረም የሚያስችላቸው ጥራዝ ነው።
አይሁድ፣ ክርስትና፣ እስልምና… የመሳሰሉት ሃይማኖቶች፣ ሕግን ለመቀመር ስላበረከቱት አስተጽዖ፤ በልማዳዊ ወግና በልማዳዊ ሕግ መሐል ስላለው አንድነትና ልዩነት፤ እነዚህ ወግና ልማዶች በተለያዩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ አተገባበራቸው ምን እንደሚመስል፤ ነገሥታት ስለሰጧቸው አስገራሚ ፍርዶች፤ ፍትሐ ነገሥት በኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ ውስጥ ያለው ሥፍራ ምን እንደሆነ፤ ስለመሬት ሥሪት ሕግና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዴት ሲሠራበት እንደነበር፤ ዐበይት ሕግጋት አወጣጣቸው ምን እንደሚመስልና ስለዓላማና ዝግጅታቸው፤ ጥንታዊ የወንጀል መከተተያ ዘዴዎች ከነበሩት መሐል ስለ ሌባ ሻይ፣ አፈርሳታ (አውጫጭኝ)፣ የአራዳ የምሥጢር ዘበኛ… እና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች በስፋትና በጥልቀት በርካታ መረጃ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥንት ዘመን ለሕግና ፍትሕ ያለው አስተያየትና ፍልስፍና ምን እንደነበር፤ የጥንቱ የኢትዮጵያ ሕግ ጉራማይሌነት የሚታይበት የአገሪቱንና የባዕድ ሕጎችን በመቀላቀሉ ምክንያት እንደሆነ፤ በጥንቱ ዘመን የሕግ አወጣጥና ስርጭት ከዘመናዊው ጊዜ ለየት ያለ መልክ ያለው ስለመሆኑ፤ የፍርድ ቤቶች አቋምና ሥልጣን ከ1928 በፊትና ከ1933 እስከ 1966 ያለው ስለመለያየቱ፤ ከ1928 በፊት የነበረው የሙግት ሥነ ስርዓት “የተጠየቅ ሥርዓት” እንደነበረና ከ1934 በኋላ በዘመናዊ የፍርድ ቤት ደንብ ስለመተካቱ፤ በጥንቱ ዘመን ከመሠረታዊው ሕግ /substantive Law/ ይልቅ የሙግት ስርዓት /procedural Law/ ዳብሮ እንደነበር፤ በጥንቱ ጊዜ የቀደመ ፍርድ /precedence/ በወደፊቱ ላይ ያለው አግባብ፣ የበታች ፍርድ ቤቶች ይከተሉት ዘንድ ሲያስገድድ፣ በአዲሱ ዘመን ግን ታዋቂነት /recognition/ ያለው እንጂ፣ የአስገዳጅነት ባሕሪ ያለው አለመምሰሉ፤ “ፍትሕ” እና “ርትዕ” የሚባሉት ሁለት ቃላት የተለያዩ ስለመሆናቸው፤ ከውጭ የተወረሱ ሕጎች በየጊዜው ተቀባይነት እያገኙ ከልማዳዊው ሕግና ሥሪት ጎን ለጎን ሲሠራባቸው ስለመቆየቱ፤ የውጭ አገር ተወላጅ የሆኑ አማካሪዎችና የሕግ ባለሙያዎች ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ስለማበርከታቸው፤ ከጥንታዊው የኢትዮጵያ የሕግ አስተሳሰብ ወደዘመናዊው የአገሪቱ ሕግ ስለመሸጋገሩት አሠራሮች፤ ሕግና ሕዝባዊ ብሒሎች ስላላቸው ግንኙነት… በመጽሐፋቸው ውስጥ በቂ ምላሽ ማኖራቸውን የገለጹት አበራ ጀምበሬ “የጥናቱ ማጠቃለያ” ባሉት ክፍል ስምንት የሚከተለውን ጽፈዋል።
“ኢትዮጵያ ዘመናዊ ዐበይት ሕጎችን (Codes) በሥራ ላይ ማዋል ከጀመረችበት ከ1950 በፊት በነበረው በረጅሙ ዘመን የተሠራባቸውን ሕጎች ሁሉ እንደዚህ ባለው አጭር ጥናት ውስጥ በበቂ ሁኔታ ተንትኖ ማስረዳት አለመቻሉ የታመነ ነው። ስለዚህም የዚህ (መጽሐፍ) ጸሐፊ በዚህ ሥራው የተሟላ የኢትዮጵያ ሕግ ጥናት እንዳቀረበ አያስብም” የሚል ትሁት ሐሳብ ያኖሩት አበራ ጀምበሬ (ዶ/ር) በስቶክሆልም (ስዊድን) ሕክምና በመከታተል ላይ ሳሉ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው በመጽሐፉ የጀርባ ገጽ በሰፈረ የሕይወትና የሥራ ታሪካቸው ተመልክቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here