የፌዴራል ኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከመጋቢት 10 ቀን 2012 ጀምሮ አዲስ ፓስፖርት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መስጠት ሊጀምር መሆኑን ገለጸ።
ከዚህ ቀደም አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት እስከ 90 ቀናት የሚደርስ ጊዜ ሲወስድ የቆየ ሲሆን፣ አሰራሩን በማዘመን አዲስ ፓስፖርት የሚፈልጉ ተገልጋዮች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማግኘት እንዲችሉ እንሚያደረግ ተገልጿል።
ካለፈው ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ በፓስፖርት ወረቀት እጥረት ምክንያት የአዲስ ፓስፖርት መስጫ ጊዜ ከአንድ ወር ወደ ኹለት ወር ከ15 ቀን መራዘሙ ይታወሳል። በአዲሱ አሰራር መሰረት አስቸኳይ ፓስፖርት የሚያወጡ ሰዎች በ5 ቀናት ውስጥ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት ኤጀንሲው ከ270 ሺሕ እስከ 300 ሺሕ ፓስፖርት እንዳለው የተገለፀ ሲሆን፣ በቀጣይ 500 ሺሕ ፓስፖርት ለማስገባት ስምምነት መደረሱ ተጠቁሟል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ተመዝግበው ከኹለት እስከ ሦስት ወር የሆናቸው 90 ሺሕ ተገልጋዮች እየተጠባበቁ እንደሚገኙም ታውቋል።
አስቸኳይ ፓስፖርት ሲያወጡ የነበሩ ሰዎች የገንዘብ ጭማሪ ተደርጎብናል በሚል ሲያቀርቡት የነበረው ቅሬታ በወረቀት እጥረት ምክንያት የተከሰተ ጭማሪ መሆኑን የገለፀው ኤጀንሲው፣ የፓስፖርቱ የገጽ መጠን በእጥፍ መጨመሩን ጠቅሶ በአዲስ መልክ በሚጀመረው የፓስፖርት አሰጣጥ ስርዓት ችግሩን እንደሚቀረፍ አስታውቋል።
በአስቸኳይ ፓስፖርት ለማውጣት የሚጠየቁ መስፈርቶችን ያላሟሉ እና መደበኛውን ፓስፖርት ያለአግባብ ሲሰጡ የነበሩ ሠራተኞች እንደነበሩም ተጠቅሷል። መስፈርቱን ላላሟሉ እና ለውጭ ዜጎች ፓስፖርት የሰጡ 10 ሠራተኞችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በተደረገው የማጣራት ሥራ ሠራተኞቹ ከውጭ ዜጎቹ ከ5 ሺሕ ዶላር በላይ ተቀብለዋል። 77 የሚሆኑ ፓስፖርቶችም በሕገ ወጥ መልኩ ተሠርተው ተገኝተዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ፓስፖርቶቹ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለኢንተርፖል ማሳወቅ እና ሰዎቹን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ኤጀንሲው ገልጿል።
ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012



