በነቀምቴ ከተማ በግማሽ ቢሊዮን ዶላር አዲስ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነባ ነው

0
498

ኢንተር ኮላር ኮንሰልቲንግ ከስፔን አገር ከመጡ አልሚዎች እና ከኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር በ500 ሚሊዮን ዶላር በምሥራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ አዲስ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊመሰረት ነው።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ የግብርና ምርቶችን በማምረት እና ዕሴት በመጨመር ለውጪ እና ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ሐሳብ እንዳለው ተገልጿል።

በ250 ሔክታር መሬት ላይ የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርኩ፣ ከውጪ አገራት የሚመጡ የግብርና ምርት ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ብሎም እንደ ፍራፍሬ ጭማቂ ያሉ ምርቶች በከፍተኛ ጥራት በማምረት ለውጪ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ እንዳለው የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አዛርያ እስጢፋኖስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የፓርኩን ግንባታ በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ ለማስጀመር ኦሮሚያ ክልል ፕሬዘደንት ጽሕፈት ቤት እና ከክልሉ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት የተፈፀመ ሲሆን፣ የፓርኩ ግንባታ በቀጣይ ኹለት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

ኮርፖሬሽኑ የመሥሪያ ቦታውን ከማቅረብ እና ፍቃድ ከመስጠት በተጨማሪ ፓርኩ ከተገነባ በኋላ የማስተዳደር እና ውሳኔ የመስጠት ሚና ሊኖረው ይችላል ያሉት አዛርያ፣ የስምምነቶቹን ዝርዝር ሁኔታ ከመግለፅ ተቆጥበዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከሚያርፍበት 250 ሔክታር ቦታ በተጨማሪ ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግንባታው እና ለሰፋፊ እርሻዎች ሰፊ ቦታ ያስፈልጋል። በዚህም ምክንያት በርካታ ሰዎች ከቦታቸው ላይ ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተብሏል።

የመሬቱን ካሳ የመክፍል ኃላፊነት የክልሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ በአካባቢው ያለውን ማኅበረሰብ የሚያውቀው ኮርፖሬሽኑ በመሆኑ ቦታውን የማዘጋጀት ሥራ እያከናወነ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ከእርሻ እና ከመኖሪያ አካባቢያቸው የሚፈናቀሉ ግለሰቦችን ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የሙያ ሥልጠናዎች በመስጠት እና በማብቃት፣ በፓርኩ ውስጥ የሥራ እድል እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል። ከወለጋ፣ አምቦ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ለተማሪዎች ሥልጠና እና የሥራ ዕድል የማመቻቸት ዕቅድ እንዳለ ተገልጿል።

ከመኖሪያ አካባቢያቸው የሚነሱ ሰዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ እንደሚኖር የጠቆሙት አዛርያ፣ በአካባቢው ያሉትን ነዋሪዎች ከቦታው ከተነሱ በኋላ የሚከፈላቸውን ገንዘብ አጥፍተው ለችግር እንዳይጋለጡ ፓርኩ የሙያ ሥልጠና ይሰጣል ብለዋል።

ፓርኩ ከአምስት ዓመታት በኋላ ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ሲገባ ለ15 ሺሕ ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል እንደሚፈጥር የተገለጸ ሲሆን፣ በእነዚህ ዓመታትም ከ15 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ፓርኩ ከውጪ አገራት የሚገቡ ምርቶችን በመቀነስ የወጪ ንግድን የማሳደግ ዕቅድ አለው ያሉት አዛርያ፣ ከኢንተር ኮላር ኮንሰልቲንግ ከክልሉ መንግሥት ጋር ያሉ ጉዳዮች እያስፈፀመ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከስፔን የሚመጡትን ድርጅቶች ለመግለፅ ግን ጊዜው አሁን አይደለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ፓርኩ የራሱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ከፀሐይ የሚያመነጭ ሲሆን፣ በክልሉ የግብርና ምርቶችን የሚያመርቱ የአገር ውስጥ እና የውጪ አገራት አምራቾችን የግብርና ምርት በመሰብሰብ ዕሴት በመጨመር ለአገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ ያቀርባል።

የፓርኩን ግንባታ ለማስጀመር እና አሁን ላለበት ደረጃ ለማድረሰ ከሦስት ዓመታት በላይ መውሰዱን የተናገሩት አዛርያ፣ የግንባታ ፈቃዶችን እና ቦታን ለማግኘት በርካታ የመንግሥት ቢሮዎችን የሚያሳትፍ በመሆኑ አድካሚ እንደነበር ጠቁመዋል።

በመንግሥት የኢንቨስትመንት ቢሮዎች መሻሻሎች ቢኖሩም፣ አሁንም የኢንቨስትመንት ጉዳይ የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አሰራሩ ለአልሚዎች አመቺ እና ግልፅ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባቸው ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here