የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎቼ እየታሰሩብኝ ነው አለ

0
620

በመመሥረት ላይ የሚገኘው የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ፓርቲ አባላቱ እና ደጋፊዎቹ እየታሰሩበት እና በምሥረታ እንቅስቃሴው ላይ በመንግሥት ጫና እየተደረገበት መሆኑን ገለፀ።
ፓርቲው በድሬዳዋ ሳተናው የወጣቶች ማኅበር በሚል ሲያደርግ ከነበረው እንቅስቃሴ የተወለደ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የመንግሥት አካላት የፓርቲውን አባላት እና ደጋፊዎች በማሰር እንዲሁም የመሰብሰቢያ ቦታ በመከልከል የፓርቲውን ምስረታ በማደናቀፍ ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።

ፓርቲውን ለመመስረትም ምርጫ ቦርድ በሰጣቸው ደብዳቤ መሰረት ቅዳሜ የካቲት 28/2012 ጉባኤውን ለማከናወን ከ500 በላይ ሰዎችን ቢሰባሰቡም፣ መንግሥት ሆቴሎችን በማስፈራራት አዳራሽ እንዳይፈቅዱ አድርጓል የሚሉት የፓርቲው ሊቀመንበር ሲሳይ አየለ ናቸው። የምስረታ ጉባኤውንም በአካባቢው በሚገኝ ዛፍ ስር ለማድረግ መገደዳቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች በተደጋጋሚ ለእስር እየተጋለጡ እንደሆነ ገልጸው፣ የከተማው ነዋሪዎች እና ደጋፊዎች ከሥራ እየታገዱ፣ ቤት እየተቃጠለባቸውና ለመሰል ማስፈራሪያዎች እየተዳረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ለአዲሱ ፓርቲ ከፍተኛ ድጋፍ አለው ያሉት ሲሳይ፣ ኅብረተሰቡ በግልፅ ድጋፍ ለመስጠት እና ድጋፍ ለማድርግ ስጋት ወድቆበታል ብለዋል። በከተማው የመመስረቻ ፊርማ ለማሰባሰብ እየሞከርን ነው ያሉ ሲሆን፣ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ፊርማውን ለማኖር ፍራቻ እንዳለው እየገለጸ ይገኛል ብለዋል።

ሳተናው የተሰኘው የወጣቶች ማኅበር በድሬዳዋ እና ሀረር ከተሞች ላይ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን በመርዳት፣ ከሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው የሚመጡ ሰዎችን በመደገፍ ሥራ በስፋት ሲንቀሳቀስ የቆየ ነው። በመሆኑም በኅብረተሰቡ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ በርካታ ደጋፊዎች እንዳሉት ሊቀ መንበሩ ተናግረዋል።
አሁን ተዳፍኖ ያለው የሕዝቡ ድጋፍ በምርጫው ውጤት እንደሚገለፅ እናምናለን ያሉት ሲሳይ፣ ፓርቲው በድሬዳዋ፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የመመስረቻ ፊርማውን እያሰባሰብ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

አክለውም ድሬዳዋ የቀደመ ድምቀቷን አጥታ ሥራ አጥንት፣ ዘረኝነት እና የፍትኅ መጓደል ተንሰራፍቶባታል። ይህም በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞች ለመኖር አስጊ እንድትሆን አድርጓል ያሉ ሲሆን፣ የተማሩ እና መሥራት የሚችሉ ሰዎች እንዳይሠሩ ተደርገዋል። ፓርቲያችን እነዚህን ድርጊቶች ለመከላከል በስፋት ይንቀሳቀሳል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ፓርቲ የምስረታ ጥያቄውን ለምርጫ ቦርድ ጥር 22/2012 ያስገባ ሲሆን፣ የካቲት 16/2012 ጊዜያዊ ሰርተፍኬት አግኝቷል። ሰርተፍኬቱን ቋሚ ለማድረግ እና ለምርጫው ለመሳተፍ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ፓርቲው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ደብዳቤ እና ማሟላት የሚጠበቅባቸው ዝርዝር ሁኔታዎችን የሚያስረዱ ሰነዶች የደረሳቸው የፓለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ፣ እስከ መጋቢት 03 ቀን 2012 ድረስ እንዲያቀርቡ ማሳወቁ ይታወሳል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ፣ የተቀመጠውን ቀነ ገድብ ለማሟላት በርካታ ጥያቄዎችን እና ሰነዶችን ለቦርዱ እያቀረቡ በመሆኑ፣ ቦርዱ በሥራ ውጥረት ላይ ይገኛል። የአንድ ፓርቲን ጉዳይ ነጥሎ አስተያየት የሚሰጥበት ጊዜ የለም ብለዋል።

በምስረታ ላይ ያሉ ፓርቲዎችን በሚመለከት እና የፓርቲዎችን ጥያቄ ለመመለስ፣ ቀነ ገደቡ ይራዘም ወይስ በዚሁ ይቀጥል የሚለውን ቦርዱ በቀጣይ እንደሚወስንም ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ የድሬደዋ ከተማ ጸጥታ እና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም፣ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here