የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በደብረ ዘይት የምርምር ተቋሙ በተደረጉ ጥናቶች አዳዲስ እና የተሻሻሉ አዝእርቶችን ያስተዋወቀ ሲሆን፣ ከዚህም በሔክታር የ13 ኩንታል ብልጫ በማሳየት ወደ 30 ኩንታል የሚጨምር እና በመልኩም እስካሁን ካሉት ነጭ ጤፎች በጣም የነጣ ዝርያ ይፋ አደረገ።
አዲስ የተገኘው የጤፍ ዝርያ በቂ ዝናብ ለሚያገኙ አካባቢዎች ከፍተኛ ምርት እንደሚሰጥና እስካሁን ከነበሩት የጤፍ ዝርያዎች ከስድስት እስከ ዐስር በመቶ የምርት መሻሻል ያሳየው ምርቱ፣ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ኹለት ዝርያዎች በተደረገ የኬሚካል ማዳቀል የተገኘ ነው።
የጤፍ ምርምሩን የመሩት ወርቁ ከበደ ሲሆኑ በቡድኑ አጠቃላይ ስምንት አባላት አሉ። ከእነዚህም መካከል ክበበዉ አሰፋ (ዶ/ር)፣ ዘሪሁን ታደለ (ዶ/ር) እንዲሁም የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ጫንያለዉ (ዶ/ር) ይገኙበታል።
ምርምሩ ሦስት ዓመት ፈጅቷል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት ሰለሞን፣ የምርምር ሥራዉ ተጠናቆ ዝርያዉ በተለያዩ የሙከራ ዘዴዎች ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል። አዲሱ የጤፍ ዝርያ በሥራ ላይ ከነበሩት የጤፍ ዝርያዎች ላይ ይታይ የነበረውን የመጋሽብ እና ፍሬ የማፍራት ችግር በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ በተለይ የመጋሸብ መጠኑ መቀነሱ ውጤቱን አመርቂ አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል።
ዝርያው በግብርና ሚኒስቴር በሚመራዉ ምርምር ግኝቶች አፅዳቂ ኮሚቴ ተገምግሞ በቅርቡ ለአርሶ አደሩ እንደሚለቀቅ ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ ከጤፍ ባሻገርም ኹለት የሽምብራ ምርጥ ዘሮች ይፋ እንደሚሆኑ ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት ከነበሩ ነባር የሽምብራ ዝርያዎች የተሻለውን በመምረጥ እና ነባሮቹን በማዳቀል የተገኙት ዝርያዎች፣ አንደኛዉ በአርሶ አደሩ የሽንብራ ምርት ላይ ከፍተኛ ችግር እየሆነ የመጣውን ‹አስኮ ካታፕላይት› የተባለ በሽታን መቋቋም የሚችልና ዝናብ አጠር ለሆኑ ቦታዎች ተስማሚ መሆኑን ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሌላኛዉ እና ኹለተኛዉ ዝርያ ‹ዊልክ› የተባለን የሽንብራ በሽታን የሚቋቋም ሲሆን ሞቃታማ ለሆኑ አካባቢዎች ተስማሚ መሆኑ ተገልጿል። ምርምሩን የመሩት ንጉሤ ይልማ ሲሆኑ፣ አምስት የምርምር አባላትች ተሳትፈውበታል።
አዲሶቹ ዝርያዎች እስካሁን በአገር ደረጃ ከነበረው አማካኝ የሽንብራ ምርት ከ21 ኩንታል በዘጠኝ ኩንታል ከፍ በማለት በሔክታር 30 ኩንታል ምርት ይሰጣሉ።
ዝርያዎቹ ቀደም ብለው ከነበሩት የሽንብራ ዝርያዎች በተሻለ በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸው ሲሆን፣ በኮሚቴዉ ተገምግመው በያዝነው ዓመት ከግንቦት ወር በኋላ ለአርሶ አደሩና ዝርያዉን ለሚያራቡ ባለሀብቶች ይሰራጫል። ዝርያዎቹ በኮሚቴዉ ከተረጋገጡ በኋላም ሥያሜ እንደሚሰጣቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በተለያዩ ቦታ እና በተለያዩ የግብርና ምርምር ባለሙያዎች ለሦስት ዓመታት ተሞክረዉ ውጤታማነታቸዉ ተረጋግጧል። ዝርያዎቹ የአርሶ አደሩን ምርት ከበሽታ ጥቃት እንደሚታደጉና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣውን የአርሶ አደሩን ምርታማነት እንደሚጨምር፣ በምርምር መረጋገጡንም ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እስካሁን በተለያዩ በሽታዎችና ተባዮች ምክንያት የሽንብራ ዝርያዎች በከፍተኛ ደረጃ በበሽታዎች ሲጠቁ እንደነበር ዳይሬክተሩ ገልፀው፣ አዲሶቹ ዝርያዎች እስካሁን በኅብረተሰቡ ዘንድ የነበረውን በበሽታዎች መማረር ለማስቀረት ታሰቦ የተደረገ ምርምር ነው ብለዋል። ሰለሞን አክለውም ሽንብራ ከኢትዮጵያ ባሻገር ወደ ውጪ የሚላክ ምርት መሆኑን ገልፀው፣ የምርት መጠኑን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ምርታማነትና ገቢ ለማሳደግ አዲሶቹ የሽንብራ ዝርያዎች ትልቅ አስተዋጽፆ እንደሚኖራቸዉ ጠቁመዋል።
በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከዚህ በፊት በምርመር ላይ መሆኑ የተነገረለትና የኒኩለር ጨረርን ተጠቅሞ ምርምር እያደረገበት ያለው የጤፍ ዝርያ፣ የመጨረሻ ሙከራ ላይ መሆኑንም ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በጤፍ ምርት የሚለማ ሲሆን፣ በየዓመቱ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶ አደሮች በጤፍ ምርት ይሰማራሉ።
ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012



