የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ አስተዳዳሪነት አሁንም እያወዛገበ ነው

0
765

በሦስት ቢሊዮን ብር የተገነባው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ማን ያስተዳደረው የሚለው ላይ ገንቢው ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ እና የፕሮጀክቱ ባለቤት የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መስማማት አልቻሉም።
ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ በተለያየ ወቅት ማመነጫውን ለማስተዳደር ጥያቄ አቅርቤያለው ቢልም የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ድርጅታቸው ካምብሪጅ ድርጅቱ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ለሦስት ወራት ማመንጫውን ማንቀሳቀስ አለበት ቢሉም የካምብሪጅ ኃይል ማኔጅንግ ዳይሬክተር የሆኑት ሳሙኤል ዓለማየሁ እንዲህ ዓይነት ሥምምነት የለንም ብለዋል።
ነገር ግን አዲስ ማለዳ ማግኘት የቻለችው መረጃ እንደሚያሳየው ማመንጫው በመገንባት ላይ በነበረበት ወቅት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች ድርጅቱ ግንባታው ከሚጠናቀቀበት ቀን አንስቶ ለሦስት ወራት ካምብሪጅ ያለ ምንም ተጨማሪ ክፍያ እንዲያስተዳድር ጠይቀው ነበር።
ይሁን እንጂ ካምብሪጅ በምለሹ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ማመንጫውን ማን እንደሚያስተዳድረው የሚወሰነው ግንባታው ካለቀ በኋላ በሚደረግ ሥምምነት ነው ብለው ነበር።
በተመሳሳይ ውል፤ ካምብሪጅ ግንባታው ተጠናቆ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለአምስት ዓመታት ለማስተዳደር ጥያቄ ቢያቀርብም የኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች አልተቀበሉትም።
ሁለቱ ድርጅቶች ባላቸው ውል መሠረት፣ ማመንጫው መሥራት ከጀመረ ከዓመት በኋላ ብቃቱን በገለልተኛ ማረጋገጥ ቢኖርባቸውም፥ በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ይህንን ለማድረግ አለመቻሉን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም፣ ከአራት ወራት በፊት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በተገኙበት የተመረቀው ፕሮጀክቱ ቢጠናቀቅም የፕሮጅክቱ ንዑስ ተቋራጭም ሆነ ዋናው ተቋራጭ በውሉ መሠረት ኃይል ማመንጫውን ስላላስረከቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች አልቀበልም ብለዋል።
የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ባለፈው ሐሙስ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ዋና ተቋራጩ በውሉ የተቀመጠውን መሥራት ያለበትን ነገሮች በአግባቡ ሳይሠራ ድርጅታቸው እንደማይረከብ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው የፕሮጀክቱ ውል ሲፈረም ተቋራጩ 50 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ሁለት ተርባይን ያለው ኃይል ማመንጫ እንደሚገነባ ቃል ገብቶ ነበር።
ነገር ግን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከቆሻሻ ላይ የማመንጨት አቅሙ ወደ 25 ሜጋ ዋት ዝቅ ብሏል፤ የተገነባው ሌላው 25 ሜጋ ዋት ተርባይን ግን በነዳጅ ኃይል የሚሠራ እንዲሆን ተደርጓል።
ነገር ግን የካምብሪጅ ኃይል ማኔጅንግ ዳይሬክሬተር የሆኑት ሳሙኤል ዓለማየሁ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፥ በውሉ መሠረት ድርጅታቸው የሚጠበቅበትን 1000 ቶን በቀን ማስወገድና 1850 ጊጋ ዋት ሀወር ማመንጨት የሚችል ፕሮጅክት ሠርተው አስረክቧል።
ፕሮጀክቱ በተመረቀበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አዜብ አስናቀ (ኢንጂነር)፣ “ከውላችን ውጪ የተከናወነ ስለሆነ ጉዳዩን ወደ ሕግ እንወስዳለን” ብለው እንደነበር አይዘነጋም። የረጲ ደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በዋና ተቋራጭነት የእንግሊዝና የአይስላንድ ኩባንያ የሆነው ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ፣ በንዑስ ተቋራጭነት ደግሞ የቻይናው ሲኤንኤኢሲ (CNAEC) የተሳተፉ ሲሆን የዴንማርኩ ራምቦል የተባለው ድርጅትም በአማካሪነት ሠርተዋል።
ማመንጫው እ.አ.አ. ከሰኔ 24፣ 2018 እስከ መስከረም 10፣ 2018 ድረስ በሥራ ላይ እንደነበርና 48 ሺሕ ኪሎ ግራም ቆሻሻ በመጠቀም 9.75 ሚሊየን ኪሎ ዋት ሀወር ኤሌክትሪክ ማመንጨት ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ በባለፈው ሳምንት ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በወጣ ዘገባ ላይ ማመንጫው ቆሻሻ ከማቃጠል የዘለለ ሚና የለውም ሲሉ የሲቪል ኤንድ ኢንቫይሮሜንታል ኢንጂነሪንግ ባለሙያ የሆኑት ሰሃዳት ሑሴን (ዶ/ር) ገልጸው ነበር።
ባለሙያው እንደ ምክንያት ያቀረቡት በኢትዮጵያ የሚመነጨው አብዛኛው ቆሻሻ ተፈጥሯዊና ከፍተኛ እርጥበት ያዘለ መሆኑን ሲሆን፥ ቆሻሻውን ለማድረቅ ከሚያስፈልገው አኳያ ሲታይ “ፕሮጀክቱን ዋጋ ቢስ” ያሰኘዋል ብለውት ነበር። ይሁን እንጂ፣ ከማመንጫው የሚገኘውን ኤሌክትሪክ በ0.07 ዶላር በኪሎ ዋት ሀወር ማቅረብ ይቻላል ሲሉ አቶ ሳሙኤል የባለሙያውን አስተያየት አጣጥለዋል።
በኤሌክትሪክ ታሪፍ፣ ኢትዮጵያ ከዓለም ትንሹን የምታስከፍል ሲሆን በኪሎ ዋት ሀወር 0.06 ዶላር ኤሌክትሪክ ታቀርባለች። ይህ አገሪቷ አንድ ኪሎ ዋት ሀወር ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ከምታወጣው ወጪ በ0.03 ዶላር ያነሰ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here