‘ብርሃንና ሰላም’ 203 ሚሊዮን ብር አተረፈ

0
738

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በ2010 የበጀት ዓመት 184 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ ቢያቅድም፥ ትርፉ ከ203 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን አስታወቀ።
የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ዳንኤል ኃይሌ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በውጭ ኦዲተሮች ተመርምሮ የተገኘው ትርፍ ከታክስ በፊት ሲሆን መጠኑም 203 ሚሊዮን 756 ሺሕ 416 ብር ነው። ይህም በዕቅድ ከተያዘው 184 ሚሊዮን ጋር ሲነፃፀር ከ19 ሚሊዮን በላይ ብልጫ አለው። ዕቅዱን በወቅቱ ከነበረው ገበያ አኳያ ቃኝቶ ማውጣቱን የገለጸው ድርጅቱ በሒደት የገበያው መስፋት ትርፉ ካሰበው በላይ እንዲሆንለት ማድረጉ ተነግሯል።
ድርጅቱ በ2009 በጀት ዓመት ካገኘው 597 ሚሊዮን ብር ገቢ ውስጥ 155 ሚሊዮን ትርፍ አግኝቶ እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ። በዚህ መሠረት በ2010 በጀት የተገኘው ትርፍ ካለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ48 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል። በዚህም የድርጅቱ ትርፍ በዓመት በ23 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ማለት ነው።
ትርፉ የተሰላው መንግሥት ከ2009 ጀምሮ እንዲተገበር ባዘዘውና አዲስ ነው በተባለው ዓለም ዐቀፉ የፋይናንስ ሪፖርት ስታንዳርድ /IFRS/ ነው ተብሏል።
ማተሚያ ድርጅቱ ከዕቅዱ በላይ ስላሳካበት ስልት የተናገሩት ዳንኤል የምሥጢራዊና የጋዜጦች ኅትመት መጨመር ዋነኞቹ መሆናቸውን አንስተዋል። ድርጅቱ አሁን ላይ 18 ጋዜጦችን ሲያትም የኅትመት ቅጅ ቁጥራቸውም ከፍ ያለ መሆኑም ተነግሯል።
አታሚ ድርጅቱ ከጋዜጦች በላይ በምሥጢራዊ ኅትመቶች ከፍ ያለ ትርፍ ማግኘቱን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በምሥጢራዊ ኅትመቶች በኩል ሁሉንም የአገር ውስጥ ባንኮች ቼክ ጨምሮ ሲፒኦ፣ ሊብሬ፣ የተለያዩ የሎተሪ ትኬቶች፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቦንዶች፣ የባቡርና የአውቶቡስ የጉዞ ትኬቶችን የሚያትም ሲሆን እነዚህም በማተሚያ ቤቱ የገቢ ምንጭ ትልቁን ድርሻ አበርክተውለታል።
በአንፃሩ በበጀት ዓመቱ በመጽሐፍት ኅትመት የታሰበው ገቢ አለመገኘቱ የተገለጸ ሲሆን ምክንያቱም ትምህርት ቢሮዎች የመማሪያ መጻሕፍት ኅትመት ጨረታ አለማውጣታቸው ነው ተብሏል። በመጽሔት ኅትመት በኩልም በተመሳሳይ የታሰበው ገቢ አለመገኘቱ ታውቋል።
በተያያዘ ዜና ማተሚያ ድርጅቱ በዓለም ገበያ የፐልፕና ወረቀት ዋጋ መጨመሩን በመጥቀስ የጋጤጣ ኅትመት ላይ ዋጋ ለመጨመር አስቦ ነበር። በጉዳዩ ላይ ለመምከርም ከአሳታሚ ደንበኞቹ ጋር ኅዳር 27/2011 ለመምከር የስብሰባ የጥሪ ደብዳቤን አሠራጭቶ የነበረ ቢሆንም፥ በድርጅቱ ውስጥ ባሉ አለመግባባቶች ስብሰባው መቅረቱን አዲስ ማለዳ በኅዳር 29 እትሟ መዘገቧ ይታወሳል። ድርጅቱ በኅትመት ጥራትና ፈጥኖ ማድረስ ላይ ከደንበኞቹ ቅሬታ ሲነሳበት ይሰማል። ድርጅቱም አልፎ አልፎ በሚከሰት የማተሚያ ማሽን ጊዜያዊ ብልሽት የኅትመት መዘግየት እንደሚገጥመው ለአሳታሚዎች መልስ ሲሰጥ ይስተዋላል።
ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት መስከረም 3፣ 1914 የተመሠረተና የአገሪቱን የኅትመት ሥራዎች ከፍተኛ ድርሻ ይዞ የሚገኝ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here