በሞጆ ደረቅ ወደብ ከ60 ቀናት በላይ ተከማችተው የሚገኙ ከሁለት ሺሕ በላይ ኮንቴነሮችን ሊወርሳቸው እንደሚችል የጉሙሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚኒሽኑ ከፍተኛ ባለሞያ አብዱልከሪም አደም እንደገለጹት ሊወረሱ የሚችሉት 2 ሺሕ 781 ኮንቴነሮች አስመጪዎቻቸው እንዲነሱ በተደጋሚ ቢጠየቁም፥ ባለቤቶቻቸው ኮንቴነሮቹን ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም። በመሆኑም በጉሙሩክ ሕግ መሠረት ሊወረሱ ይችላሉ ተብሏል። ይሁንና መንግሥት በጊዜው ያልተነሱ ኮንቴነሮችን እወርሳለሁ ከማለት ባሻገር በተግባር እርምጃ ሲወስድ አይታይም፤ ጊዜውን በተደጋጋሚም ያራዝማል በሚል ይተቻል። ስለዚህ ጉዳይ አብዱልከሪም ሲያብራሩ መንግሥት ወርሶ የሚያገኘው ገቢ አነስተኛ ሲሆን የማስወገጃ ወጪው በአንጻሩ ከፍተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል።
የሞጆ ደረቅ ወደብ ሲመሠረት በአገሪቱ ላይ ያለውን የወጪ እና ገቢ ንግድ እንዲያቀላጥፍ ታስቦ ሲሆን፣ በወደቡ የሚስተናገዱ ኮንቴነሮች ከ40 እስከ 50 ባሉት ቀናት የጉምሩክ ስርዓታቸውን ጨርሰው ከወደቡ እንዲወጡ ይጠበቃል። ይሁንና አሁን ላይ በርከት ያሉ ኮንቴነሮች በወደቡ መቆየት ካለባቸው ግዜ በላይ እየቆዩ ለጉሙሩክ አሠራር እና ቅልጥፍና ፈተና ሆነዋል ተብሏል።
ወደቡ አጠቃላይ ኮንቴነር የመያዝ አቅሙ 14 ሺሕ ቢሆንም ባሳለፍነው ኅዳር መግቢያ ላይ በወደቡ 17 ሺሕ ኮንቴነሮች ተከማችተው መገኘታቸው መጨናነቅ ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል። መጨናቁን ለማስወገድ በተከናወነ ተግባር ደረቅ ወደቡ በአሁኑ ወቅት ወደ 9 ሺሕ 900 የሚጠጉ ኮንቴነሮችን አከማችቶ ይገኛል ተብሏል። ከእነዚህ ኮንቴነሮችም ከሦስት ሺሕ በላይ የሚሆኑት የተለያዩ የዘይት ምርቶችን የያዙ መሆናቸው ታውቋል። የመማሪያ መጻሕፍትን የያዙ ኮንቴነሮችም በደረቅ ወደቡ ተከማችተው እንደሚገኙ ተሰምቷል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት ማጋጠሙ እየተገለጸ ይገኛል።
ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከ800 እስከ አንድ ሺሕ የሚሆኑ ኮንቴነሮች በቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተወርሰው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ አገሪቱ ባጋጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት በርካታ አስመጪዎች ኮንቴነሮቹን በወቅቱ ለማንሳት ተቸግረዋል።
ኢትዮጵያ ካሏት ሰባት ደረቅ ወደቦች መካከል አንዱ የሆነው የሞጆ የደረቅ ወደብ ከ78 እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የወጪ እና ገቢ ዕቃዎች በማስተናገድ ላይ የሚገኝ ትልቁ ወደብ ነው። ወደቡ በ2001 በመልቲ ሞዳል አገልግሎት የሎጀስቲክስ ሥራውን መጀመሩ ይታወሳል።
ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011