የሕዳሴ ግድብ ተጨማሪ 18 ቢሊየን ብር አስወጣ

0
736

. ኢትዮጵያን በዓመት ወደ 800 ሚሊየን ዶላር አሳጥቷል ተብሏል

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላለፉት ዓመታት በነበረው ግንባታ የውጭ ምንዛሬ ማስተካከያ በመደረጉና በነበሩ ክፍተቶች የተነሳ ከተያዘለት 80 ቢሊየን ተጨማሪ 18 ቢሊየን ብር ማስወጣቱን ማወቅ ተችሏል። ግንባታውን ለማጠናቀቅም ቢያንስ ተጨማሪ 40 ቢሊየን ብር ሊያስወጣ ይችላል ተብሎ ተገምቷል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ውይይት በተደረገበት ወቅት የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክፍሉ ሆራ ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4 በሰጡት መግለጫ፥ ግድቡ በግንባታ ላይ በነበረበት ወቅት በነበሩ ክፍተቶችና በመዘግየቱ የተነሳ ኢትዮጵያ በዓመት ማግኘት የሚገባትን ወደ 800 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ እንድታጣ አድርጓታል ሲሉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የግድቡ የሲቪል ምህንድስና ሥራው 82 በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው ግን 25 በመቶ ላይ ይገኛል። ዋና ሥራ አስኪያጁ ‹‹በአጠቃላይ የግድብ ግንባታ 65 በመቶ መጠናቀቁን›› ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱን የኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታዎች ሲያከናውን ከነበረው የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የነበረው ውል ተቋርጦ በዘርፉ ልምድ ካላቸው የውጭ አገራት ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ ወደ ሥራ መገባቱን የፓናል ውይይቱ ላይ ተገልጿል።
ግድቡ በቀጣይ አራት ዓመታት ይጠናቀቃል ሲሉ የተናገሩት ክፍሌ ሆራ ግድቡ ከሁለት ዓመት በኋላ በሚኖሩት ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ተናግረዋል። ‹‹ፕሮጀክቱ እንደቆመ የሚናፈሰው ወሬ እውነት አለመሆኑና ግንባታው ለደቂቃም ሳይቋረጥ በመካሄድ ላይ እንደሆነም›› ጨምረው ገልፀዋል። በተጨማሪም ላለፉት ዓመታት ግድቡን በተመለከተ ያለውን ድብቅነት በማስቀረት የውሸት ሪፖርት ማቅረብ ተቋማቸው እንደሚያቆም ቃል ገብተዋል። የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ጥልቅ ጥናትና ምርምር ሥራ ሳይከናወንለት የግድቡ ግንባታ መጀመሩ ለግንባታ ጊዜው መጓተት ትልቁ ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል።
የግድቡ የመሠረት ድንጋይ መጋቢት 24/ 2003 በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የተጣለ ሲሆን የግድቡ ሥፍራ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ይገኛል።
ግድቡ በ2010 መጠናቀቅ ቢኖርበትም በግንባታ ወቅት ባጋጠሙ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሊዘገይ ችሏል።
ግድቡ በግንባታ ወቅት ከጥራት፣ ከጊዜ እና ከወጪ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮች እንደነበሩበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አብረሃም በላይ ተናግረዋል።
የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን ሲያከናውን በነበረው ሥራ ተቋራጭ የዕውቀት እና የክህሎት ማነስ እንዲሁም በግንባታው ወቅት ጥልቅ የሆነ ዋሻ ማጋጠሙ በሥራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ በግድቡ ዙሪያ ተጨማሪ ሳይንሳዊ ጥናቶች ለማካሄድ ተስማምተዋል ተብሏል።
ከአፍሪካ ትልቁ ከዓለም ደግሞ በስፋቱ ስምንተኛ የተባለውና 6450 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችለው የሕዳሴ ግድብ ከግብፅ በኩል ከጅማሬው አንስቶ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።
ከሱዳን ድንበር 20 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው ግድቡ፤ የውሃ ሙሌት ሥራው ባለፈው ዓመት ሊጀመር ይችላል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም ከግንባታው መዘገየት ጋር ተያይዞ ሊሳካ አልቻለም።
ይሁንና ሙሌቱ መቼ ይጀመር የሚለው ላይ በሦስቱ አገራት ስምምነት እንደሚሆን የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here