ከ184 ሺሕ ሊትር በላይ ነዳጅ በኮንትባንድ ሊወጣ ሲል ተያዘ

0
561

በሕገ ወጥ መንገድ ናፍጣ ጭነው ከአገር ለመውጣት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አራት ተሸከርካሪዎች ከነተሳቢያቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባሳለፍነው ማክሰኞና ረቡዕ በሱማሌ ክልል በኩል ከሕግ አግባብ ውጭ ናፍጣ ጭነው ወደ ሌላ አገር ለማሳለፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አራት ተሽርካሪዎች ከነተሳቢያቸው በሚኒስቴሩ የጅግጅጋ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ በኩል መያዛቸው ነው የተነገረው፡፡
አንድ ተሽከርካሪ ከነተሳቢው (ቦቴ) ከ45 እስከ 48 ሺህ ሊትር እንደሚዝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 46 ሺህ ሊትር በአማካይ ተደርጎ ቢወሰድ፤ ከአገር ሊወጡ በነበሩት አራት ተሸከርካሪዎች ውስጥ 184 ሺህ በላይ ሊትር ነዳጅ ነበር ማለት ነው፡፡ አሁን ባለው የገበያ ዋጋ በአማካይ አንድ ሊትር በ17 ብር የሚሸጥ ሲሆን በኮንትሮባንድ ሊወጣ የነበረው ነዳጅ ከሦስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ አለው ማለት ነው፡፡
አዲስ ማለዳ ከሚኒስቴሩ ባጣራችው መረጃ ኢትዮጵያ ነዳጅን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ እያስገባች ቢሆንም ለተገቢው አገልግሎት ሳይውል በኮንትሮባንድ መልሶ ከአገር ሲወጣ እየተያዘ ነው፡፡
ሚኒስቴሩ ጥርጣሬ ባደረብኝ የጉሙሩክ ፈተሻ ኬላዎች ሁሉ በጥንቃቄ መፈተሼን አጠናክሬያለሁም ብሏል፡፡
በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች የናፍጣና ቤንዚን እጥረት መከሰቱ የሚታወስ ሲሆን ምክንያቱም ሕገ ወጥ የቤንዚን ንግድና ኮንትሮባድ ነው መባሉ ይታወሳል፡፡ ቤንዚን በኮንትባድ ወደ ጎረቤት አገሮች ሳይቀር እየተጓጓዘ ስለመሆኑም ይነገራል፡፡
አዲስ ማለዳ በቀደመ እትሟ ከቤንዚን እጥረትና ኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ በሰራችው ዘገባ ያነጋገረቻው የነዳጅ ማደያ ሰራተኞች ከዚህ ቀደም ይቀርብላቸው የነበረው ነዳጅ መጠን አሁን ላይ መቀነሱን መናገራቸው ይታወሳል። ምክንያት ያሉትም ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ነዳጅ ተመልሶ በኮንትሮባድ ወደ ሌሎች አገሮች መሸሽና እዚሁ አገር ውስጥም በሕገወጥ መንገድና ቦታዎች በከፍተኛ ዋጋ መሸጥን ነው።
በማደያዎች ቤንዚን ለማግኘት እንደተቸገሩ የገለጹ አሽከርካሪዎች በበኩላቸው በሕገወጥ መንገድ ከሚሸጡ አካላት በተጋነነ ዋጋ ለመግዛት መገደዳቸውን ስለመናገራቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here