በአዲስ አበባ ሰው ሠራሽ የምግብ ዘይት እጥረት ተከሰተ

0
594

የምርት ወይም የአቅርቦት እጥረት ባልተከሰተበት ሁኔታ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ወረርሽኝ ተከትሎ የምግብ ዘይት ዋጋ ይጨምራል በሚል በነጋዴዎች ዘንድ ያለአግባብ ዘይት በመደበቅ ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ የምግብ ዘይት እጥረት መፈጠሩን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ጨምሮ እንደገለጸው፣ የምግብ ዘይት እጥረት ሳይኖር ነገር ግን የአቅርቦት እጥረት ሊመጣ ይችላል በማለት እና ከዛም ከወጣለት ዋጋ በላይ ጭማሪ አድርጎ ለመሸጥ በማሰብ በመጋዘን ሲያከማቹ የነበሩ ነጋዴዎች አሉ። ሚኒስቴሩም ባደረገው ክትትል እነዚህን ነጋዴዎች መለየታቸውንና እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።

በዚህም ረገድ ሚኒስቴሩ ከኅብረተሰቡ ጋር በጋራ በመሆን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሕገ ወጥ ነጋዴዎች አሉ ሲሉ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወንድሙ ፍላቴ ገልጸዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ እስከ አሁን በተሠራው ሥራ፣ በተገቢው መንገድ ተሰራጭቶ ነገር ግን ካለአግባብ ዘይትን ጨምሮ የምግብ ሸቀጦችን ያከማቹ 15 ሺሕ 58 ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደተወሰደ የተናገሩት ሕዝብ ግንኙነቱ፣ ከእነዚህም መካከል 424 ነጋዴዎች የእስር እርምጃ እንደተወሰደባቸው ኃላፊው ተናግረዋል።

የምግብ ዘይት በመንግሥት የዋጋ ድጎማ ተደርጎበት የሚገባ እንደመሆኑ፣ በየወሩ 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት እንደሚገባና እጥረት እንደሌለ ተግልጾ ነበር። በመጋቢት ወርም የሰውን ፍጆታ ለማሟላት የሚበቃ ዘይት መግባቱንም ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪ በግለሰብ ነጋዴዎች ከውጭ የሚገባና የሚሸጥ አራት ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ ዘይት ያለ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ዘይት ፋብሪካዎች ተመርቶ በየወሩ የሚቀርብ በተመሳሳይ አራት ሚሊዮን ሊትር ዘይት እንዳለ ወንድሙ አስታውሰዋል። አሁንም የአቅርቦት ችግር ሳይሆን የነጋዴዎች ከተገቢው በላይ የማከማቸትና የማስቀመጥ እና ገዢዎችም ደግሞ በፊት ይወስዱ ከነበረው በላይ የመግዛት እና የማከማቸት ሁኔታ ይህን ችግር እንዳመጣው ተናግረዋል።

‹‹አሁን ላይ የሚስተዋለው በአገር ውስጥ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በማድረግ፣ ያለአግባብ በምግብ ሸቀጦች ላይ ዋጋ የሚጨምሩ እና የአቅርቦት እጥረት ባጋጠመ ሰዓት ዋጋ ሊጨምር ይችላል በማለት የሚያከማቹ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰድን ነው።›› በማለት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዚህም ላይ የክትትል ሥራውን ለማከናወን፣ አዲስ አበባ ዙርያ ያሉትን ኦሮሚያ ንግድ እና ኢንዱስትሪ እንዲሁም የአዲስ አበባ አስተዳደርን ጨምሮ የሚከታተል ግብረ ኃይል መቋቋሙን አንስተዋል። ይህን ግብረ ኃይል በበላይነት የሚመራውም የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ የቁጥጥር ሥራውን የሚያከናውን ግብረ ኃይል መቋቋሙን የሕዝብ ግንኙነት ኃለፊው አስታውቀዋል።

የቁጥጥር ሥራውን የሚያከናውነው ግብረ ኃይል በምርቶች ላይ ዋጋ የሚጨምሩ እና ያለአግባብ የሚያከማቹ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ሲኖሩ፤ ተከታትሎ በሳምንት በሳምንት ለአገራዊ የገበያ ዋጋ ማረጋጊያ ግብረ ኃይል ሪፖርት የሚያቀርብ ይሆናልም ተብሏል።

‹‹መንግሥት ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ይውሰድ እንጂ፣ የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ያለአግባብ ወደ ፊት ሊጠፋ እና ሊወደድ ይችላል በማለት ገዝተው ማከማቸታቸውም ለእጥረቱ ምክንያት እንዲሆን እና ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን እንዲባባሱ አድርጓል።›› ሲሉ ወንድሙ አስረድተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here