የኮቪድ 19 ዳፋ – በኢትዮጵያ

0
587

ዓለም ዐቀፉ ወረርሽኝ ኮሮና ኮቪድ19 በተለያዩ የዓለም አገራት በተለይም ደግሞ በምጣኔ ሀብት ደርጅተዋል በተባሉ አገራት ላይ ቁጣ ሽመሉን አጠንክሮ ቀጥሏል። ይህንንም ተከትሎ ችግሩ በስፋት የተከሰተባቸው የዓለም አገራት በርካታ እንቅስቃሴዎቻቸውን እና የዕለት ተዕለት ክንውኖቻቸውን እንዲገቱ ተገደዋል።

በተለይ ደግሞ ታላላቅ አየር መንገዶች ከወረርሽኙ ጅማሬ ጀምሮ ወደ ቻይና የነበራቸውን በረራ በማቆም ቢጀምሩም ቀስ በቀስ ግን የበረራቸውን ዕገዳ ወደ ሌሎች ዓለም አገራት መዳረሻዎችም አዙረዋል። ለዚህ ደግሞ በርካታ አገራት ውስጥ ወረርሽኙ በመዛመቱ መሆኑ ግልጽ ምክንያት እንደሆነ ይፋ ሆኗል።

ወረርሽኙ ከጀመረበት ቻይና ወደ ሌሎች አገራት ቢዛመትም በሦስት አገራት ማለትም በአሜሪካ፣ ጣልያን እና ስፔን ግን በሟቾች እና በታማሚዎች ቁጥር የሚስተካከላቸው እየተገኘ አይደለም። ይህ ጽሑፍ እየተሰናዳ ባለበት ወቅት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ወረርሽኙ ወደ 900 ሺሕ ገደማ ሰዎችን በተረጋገጠ ሁኔታ ያጠቃ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ከ43 ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ ሆነዋል። ከ185 ሺሕ በላይ ደግሞ ከበሽታው አገግመው መነሳታቸውን የወረርሽኙን ወቅታዊ ሁኔታ በቀጥታ የሚዘግበው ወርልዶ ሜትር አስታውቋል።

ከላይ ከተጠቀሱት አሃዞች ውስጥ በአሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ስፔን እና ቻይና ትልቅ ቁጥር ከተመዘገበባቸው አገራት ዋነኞቹ ናቸው። በተረጋገጠ ወረርሽኝ አሜሪካ ከ188 ሺሕ በላይ የበሽታው ተጠቂዎችን ስታስመዘግብ አምስት ሺህ በላይ ዜጎቿንም በሞት ተነጥቃለች። ጣሊያን እና ስፔን በ106 ሺሕ እና በ103 ሺሕ ገደማ የተጠቂዎች ቁጥር በኹለተኛ እና በሦስተኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጡም፣ የሟቾች ቁጥር ግን ከ12 ሺሕ በላይ ሰዎችን በማስመዝገብ ዘግናኝ እልቂት በማጋጠም ጣሊያን ግንባር ቀደም መሆኗን የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል።

የጤና ድርጅቱ የወረርሽኙ መነሻ የሆነችው ቻይና በከፍተኛ ርብርብ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎችን ቁጥር ከ81 ሺሕ 500 ላይ እንዳይዘል እየታገለች ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ሦስት ሺሕ 300 ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።

ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ አገራት የየራሳቸውን እና ያዋጣናል ያሉትን የመከላከያ እርምጃዎችን እየወሰዱም ይገኛሉ። ከማኅበራዊ ፈቀቅታ እና ከንጽህና አጠባበቅ ባለፈ ለሳምንታት ምናልባትም ለወራት የሚዘልቅ፣ ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡና ቤታቸው እንዲቀመጡም አዝዘዋል። ያንንም ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ።

ይህን ተከትሎ በበርካቶች ጉዳዩ በአፍሪካ በተለይም ደግሞ እምብዛም የማያወላዳ የጤና ስርኣት ያላትን አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ወረርሽኙ አንድ ጊዜ ካፈተለከ መመለሻው እንደሚቸግር እና የብዙዎችን ሕይወትም ሊቀጠፍ እንደሚችል ያስቀምጣሉ። ይህንም ምክንያት በማድረግ እንደ ሌሎች አገራት መንግሥት በሕዝቡ ዘንድ መንቀሳቀስን ከእነ አካቴው በመከልከል ቤት ውስጥ እንዲቀመጥ ትዕዛዝ ማስተላለፍ ይኖርበታል፤ እንዲሁም ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ መገታት ይኖርበታል በሚልም ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ማንኛውንም አይነት ወደ ክልላቸው የሚደረጉትን የሰዎች እንቅስቃሴዎች እና የሕዝብ መጓጓዣዎችን በማገድ ጀምረዋል።

በተመሳሳይም በመዲናችን አዲስ አበባ የመንግሥት ሠራተኞች ቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ መንግሥት ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከግማሽ በመቶ በላይ ሠራተኞቻቸውን ቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይም መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችና የኤምባሲ ቆንጽላ ጽሕፈት ቤቶችም ሠራተኞቻቸውን በቤታቸው አሳርፈዋል። ይህ የሰዎች እንቅስቃሴ መገታት እና መታገድ በሌላ በኩል በአገር ላይ የሚያደርሰውን ጫና ደግሞ ባለሙያዎች ከአዲስ ማለዳ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገው የሚከተለውን ሙያዊ ትንታኔ ሰጥተዋል።

በማኅበራዊ ቀውስ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማኅበረሰብ ጥናት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት የራስወርቅ አድማሱ (ዶ/ር)፣ በተለያዩ ስፍራዎች እና ጊዜያት ወደ ሕዝቡ ብቅ እያሉ መንግሥት ኹሉንም እንቅስቃሴዎችን እንዲዘጋ የሚወተውቱ ሰዎች ለምን ይህን መንገድ እንደፈለጉ አይገባኝም ሲሉ ይጀምራሉ። ራስወርቅ አያይዘውም በሽታውን በሚመለከት በአገሪቱ ነባራዊ እና ተጨባጭ ሁኔታ መከላከል እንደሚበጅ እና በሌላው አገር የተደረገው ሁሉ በኢትዮጵያም በኩል መደረግ ይኖርበታል የሚለው አካሄድ እንደ አገር ያለንበትን ሁኔታ ያላገናዘበ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

በሽታውን መቆጣጠር ቢኖርብንም ከሌሎቸ አገራት ተሞክሮ መውሰድ ካለብን እኛን ከሚመስሉ እና በርካታ ቁጥር ያለው ሥራ አጥ ባለባቸው አገራት የተወሰደውን እርምጃ ጠንቅቆ ማየት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ህንድን ለአብነት ያነሱት የራስወርቅ፤ በህንድ በመንግሥት በኩል የተወሰደው እርምጃ ለቀውስ እንደዳረጋቸው ሁሉ ነገም የእኛ እጣ ፋንታ እንደዛው ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

‹‹የመንግሥትን እርምጃ ለዘብተኛ እና አክራሪ ብለን በኹለት ከፍለን ማየት ይኖርብናል›› ይላሉ የራስወርቅ። አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት እየወሰደ ያለውን ነገር በለዘብተኛው ጎራ እንደሚመድቡት ይናገራሉ። በዚህም መሰረት በሥራ ላይ ያለው የመንግሥት እርምጃ ጠቃሚ እንዳልሆነ እና በሽታውን ከመቆጣጠር አኳያ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት እንዳለው በጥናት ከተረጋገጠ ወደ አክራሪው መሔድ እንደሚቻል ገልጸዋል።

‹‹እንደ እኔ ግን በሽታው በዋናነት ከውጪ እንደሚገባ እየተመለከትን የገጠር ከተሞችን እንቅስቃሴ መግታት ጭራሽ በሽታውን ለመቆጣጠር አስተዋጽኦው ጥቂት ነው። በዛ ፋንታ ግን በድንበሮች ላይ፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎች እና በባቡር ጣቢያዎች ላይ ከባድ የሆነ ፍተሻ ቢደረግ፣ የታማሚዎች ቁጥር ከዚህም ያነሰ ይሆን ነበር።›› ሲሉ አክለዋል።

ነገር ግን ወደ አክራሪው እርምጃ መንግሥት ከገባ እና ጠቅላላ እንቅስቃሴዎችን የሚያግድ ከሆነ ከባድ ማኅበራዊ ቀውሶች ይከተላሉ። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ቀድሞ ሊዘጋጅ ይገባዋል ባይ ናቸው። ነገር ግን ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ሌሎች አገራት እንዳደረጉት ሙሉ በሙሉ መዝጋት ከደኅንነት አንጻር ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል ያስረግጣሉ።

‹‹አንድን የሚበላው የሌለውን እና የቀን ሥራ ሠርቶ የሚተዳደረውን ጎረምሳ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴውን አግደህ ሂድ ብትለው፣ ትልቅ ችግር ነው። እንደ አገር የሚፈጠረው ይህ ሁሉ ታሳቢ መደረግ ይኖርበታል›› ይላሉ።

በክልል መንግሥታት የተላለፈውን የሕዝብ እንቅስቃሴ እገዳ በሚመለከትም ለዘብተኛ እርምጃ ልንለው እንችላለን። ግን ኅብረተሰቡን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አይደለም ይላሉ። ነገር ግን የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዲንቀሳቀሱ መፍቀዳቸው ለዘብተኛ ልንለው እንችላለን ሲሉ ይናገራሉ። ነገር ግን ሰዎች መጓጓዣ በመከልከሉ ምክንያት ለሚደርስባቸው እንግልት ቀድሞ የታሰበ አይመስልም ሲሉም ቅሬታቸውን ይናገራሉ።

እንደ መደምደሚያም መንግሥት አሁን ባለው ሁኔታ እስከ መጨረሻው ድረስ መታገል እንዳለበትና ኢትዮጵያ ያለችበት የማኅበራዊ መዋቅር ሙሉ በሙሉ ዘግቶ ለማስቀመጥ የማይቻል እንደሆነም ያወሳሉ።

በምጣኔ ኃብት
በአንድ ጅምር ፎቅ ቤት በረንዳ ተከራይታ ጀበና ቡና በመሸጥ የምትተዳደረው ትዕግስት ዓለሙ ሥራዋ ከሰሞኑ መቀዛቀዙን ትናገራለች። በተለይም ደግሞ በምትሠራበት ሲኤምሲ አካባቢ የጉምሩክ ኮሚሽን ሠራተኞች መኖራቸው ነበር በዋናነት የጀበና ቡናዋን ያለ እረፍት እንድትሸጥ ይረዳት የነበረው። ይሁን እንጂ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራተኞቹን ቤት ሆነው እንዲሠሩ ከማድረጉ የተነሳ ገበያዋ ቀዝቅዟል።

‹‹በዋናነት ጉምሩክ የሚሠሩ ሰዎች በቋሚነት ደንበኞቼ ሆኑ እንጂ ብዙ ሰው አልፎ የሚሄደውም ተጠቃሚ ነበር። ነገር ግን እንቅስቃሴ ሲቀንስ ገበያውም አብሮ ሞተ›› ስትል ትዕግስት ትናገራለች። አዲስ ማለዳ በስፍራው በተገኘችበት ወቅት ከሦስት ሰዎች በላይ ጀበና ቡናውን ሲጠቀሙ አልታዩም። ለወትሮው እስከ ኹለት መቶ ሲኒ ቡና እሸጥ ነበር የምትለው ትዕግስት፣ ይሄ የእንቅስቃሴ መቀነስ ካጋጠመ ጀምሮ ግን ግማሹን ለመሙላትም በጭንቅ እንደሆነ ትናገራለች።

ትዕግስትን እንደ ማሳያ አነሳን እንጂ፣ ጫማ ጠርገው (ሊስትሮዎች) ከሚያድሩ እስከ ጎዳና ላይ ነጋዴዎች ድረስ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች መገታታቸው በምጣኔ ኃብቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በተለይም በታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የምጣኔ ኃብት ሙሑሩ አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሲሰጡ በየደረጃው ያሉት ግለሰቦች ከሰዎች እንቅስቃሴ መገታት ጋር ተያይዞ ሊጎዱ እንደሚችሉ በመናገር ይጀምራሉ። ነገር ግን አሁን እንደ አገር ኹለት መመረጥ የሌለባቸው ግን ከመምረጥ ውጪ ሌላ አማራጭ የሌለበት ጊዜ ላይ በመደረሱ እንቅስቃሴዎችን በመግታት የቫይረሱን ወረርሽኝ እድሜ በማሳጠር ሊያደርስ የሚችለውን ችግር ማስቆም እንደሚቻል ይጠቁማሉ።

‹‹ይሁን እንጂ እንቅስቃሴ ሲገታ የንግድ እንቅስቃሴው ስለሚጎዳ እንዲሁም በቀን ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚሠሩ የዕለት ጉርሳቸውን የሚጠብቁ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዱ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ታዲያ መንግሥት፣ ዕርዳታ የሚሰጡ አካላት እስከ ቀበሌ መዋቅር ድረስ በመውረድ በቤታቸው ሆነው ለሚቸገሩት እንዲደርሱ መደረግ ይኖርበታል። ለዚህም ደግሞ ዕድር እንዲሁም ሸማቾችን እና የመሳሰሉትን መጠቀም ያስፈልጋል›› ሲሉ ይጠቁማሉ። ወደ ውጪ የወጡትን ሰዎች እና በልመና የሚተዳደሩትን ሰው ስለሚያያቸው ቢጎዱም በቀን ሥራ ተሰማርተው እንዳሉት ሰዎች ላይሆን ይችላል የሚሉት አጥላው፣ በየመንደሩ ለሚገኙ እና ቀን ጉርስ ለሚሠሩ ሰዎች ግን ተገቢው ድጋፍ መሰጠት ይኖርበታል ሲሉ አጽንኦት ይሰጣሉ።

ከእንቅስቃሴ መገታት ጋር ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባም የተላለፈው ገደብ በኀብረተሰቡ ላይ ረሃብን እንዳይቀሳቅስ ዋና ዋና እና መሰረታዊ የሆኑ ማምረቻዎች፣ የምርቶች ማጓጓዣዎች እንዲሁም አገልግሎት ሰጪዎች መገታት አይደለም እንዲያውም ከመቼውም ባለፈ መበርታት እና አቅማቸውን ጨምረው መሥራት ይኖርባቸዋል ሲሉ ይናገራሉ።

በጤናው ዘርፍ
በኢትዮጵያ ኹሉም የሕክምና ባለሙያዎች የሚስማሙበት አንድ ጉዳይ ቢኖር ጤናው ስርዓት እምብዛም የሚያወላዳ እንዳልሆነ እና ዓለም ዐቀፍ ወረርሽኙ ደግሞ ወደ ባሰ ችግር ሊከተው እንደሚችል ነው። ዶክተር ብሩክ ዓለማየሁ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያታቸውን ሲሰጡ፣ በኢትዮጵያ እንዲሁም እንደ አኅጉር በአፍሪካ የጤና መስኩ የደከመ ነው ሲሉ ይጀምራሉ።

ይህ ግን ያለንን ሁሉ እንድናወጣ ሊያደርገን ይችላል። እንደምንም እየተንገዳገደ የነበረውን የጤና ዘርፍ ቀውስ ውስጥ እንዳይከተው ያስፈራል። ስጋቱ ሲጨምር ይህ ማለት ሰዎች መታከም ሳይችሉ በየመንገዱ ይሞታሉ የሚልም ፍራቻ አላቸው። የተወሰነ ተስፋ ማድረጉ ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ ትብብርና የምንሠራበት ፍጥነት፣ የማስተላለፍና መረጃ መለዋወጥ ላይ በጣም ይቀረናል። አስተያየት መቀበል ነገር ላይ ክፍተት አለ፣ የሌላ ሰው ሐሳብ መስማት የማይፈልጉም አሉ ሲሉም ያክላሉ።

በአሁኑ ሰዓት ወረርሽኙን ለመግታት እየተደረገ ያለውን ጉዳይ ብሩክ ሲናገሩ የተለያዩ ጎኖች መኖራቸውን በመጥቀስ ይጀምራሉ። በኢትዮጵያ ደረጃ በመንግሥት የሕክምና ተቋማትና በግል ተቋማት መካከል መግባባትና መተባበር ተፈጥሯል። ይህ የሁሉንም ድርሻና ትብብር የሚፈልግ ስለሆነ፣ ከሌላ ጊዜ በተሻለ ትብብር በተወሰነ መልኩ ይታያል።

ግን በጣም ተስፋ የሚሰጥ ነገር አይታይም። የካቲትና ጥቁር አንበሳ ለቫይረሱ ዝግጅት ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል ሲሆኑ፣ በእነዚህ ሆስፒታሎች በር ላይ እጅ ማስታጠብና ለእጅ ማጽጃ አልኮል መስጠት እንዲሁም ትኩሳት መለየት ይታያል። ይህ ግን የጤና ዘርፉ መሻሻል ማሳያ አይደለም የሚሉት ብሩክ፣ ‹‹ዋናው መዋቅሩ ላይ ነው። መዋቅሩ ላይ ጠንካራ ሥራ ከተሠራ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።›› ብለዋል። አሁን ላይ የሕክምና ባለሞያዎቸ በተነሳሽነት እያገለገሉ ቢሆንም፣ ያንን በስርዓት ወስጥ አስገብቶ መቀጠል ላይ ምን አለን የሚለው መታየት አለበት ብለዋል። ‹‹ትብብር ሲቀጥል ለውጥ ሊመጣ ይችላል›› ሲሉም ሐሳባቸውን ይደመድማሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here