በባህር ዳር የወባ መድኃኒቶች ለኮቪድ 19 መከላከያ በሚል በከፍተኛ መጠን እየተገዙ ይገኛል

0
785

በአማራ ክልል መዲና ባህር ዳር እና አካባቢው ህብረተሰቡ የወባ በሽታ መድኃኒትን ለኮረና ቫይረስ መድኃኒትነት ያገለግላል በሚል ያልተረጋገጠ መረጃ እየገዛ እንደሆነ በአካባቢዉ የሚኖሩ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በአካባቢዉ የሚኖሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንደገለጹት ከወባ መድኃኒቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን ክሎሮኪን የተባለውን መድኃኒት ህብረተሰቡ በከፍተኛ ወጪ እየገዛ ነው፡፡ ምንጫችን እንደገለፁትም ህብረተሰቡ ይህንን መደኃኒት እንደ መጠባበቂያ በማሰብ በስፋት እየገዛ ነው፡፡

ከዚህ በፊት በመድኃኒት መደብሮች 150 ብር ሲሸጥ የነበረ በውስጡ አንድ መቶ ኪኒኖችን የያዘ አንድ ካርቶን የወባ መድኃኒት እስከ 900 ብር እየተሸጠ ሲሆን አንዳንድ መድኃኒት ቤቶች የህብረተሰቡን ፍላጎት መጨመር በመመርኮዝ ወደ ፊት ሊጨምር ይችላል በሚል አከማችተው እስከ ማስቀመጥ መድረሳቸው ታውቋል፡፡
የአዲስ ማለዳ ምንጮች በአካባቢው በአሁኑ ጊዜ የወባ በሽታ የሚቀሰቀስበት ጊዜ አለመሆኑ እና ከዚህ በፊት የወባ በሽታ የሚቀሰቀሰው በተለይ ግንቦት ወር ላይ እንደሆነ ገልጸዉ ለኮሮና መድኃኒት ይሆናል በሚል በገፍ መግዛቱ ከፍተኛ የሆነ ዕጥረት እንዲከሰት አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽ/ፈት ቤት ኃላፊ ሙሉጌታ ቆየ በአካባቢው ችግሩ እንዳለ በማህበራዊ ሚዲያና በወሬ ደረጃ ጥቆማዎች መኖራቸውን ገልጸው አስከ አሁን ግን የወባ መድኃኒት ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ ያገለግላል ተብሎ ሲሸጥ አልተገኘም በማለት ጉዳዩን አስተባብለዋል፡፡

እስከ አሁን በተጨባጭ አለመገኘቱን የገለጹት ሙሉጌታ በግላቸው መድኃኒቱ ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ያገለግላል ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደሚያውቅም ጠቁመዉ ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ ወደ ፊት በሚደረግ ማጣራት በባለሙያዎችና በግለሰቦች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል፡፡

ኃላፊዉ አክለዉም ህብረተሰቡ አሜሪካ የወባ መድኃኒት ለኮሮና ቫይረስ በሽታ መድኃኒትነት እንደሚያገለግል መግለጿን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጩ መረጃዎች አንዳንድ ግለሰቦች እና ከሙያ ስነ ምግባር ውጭ የሆኑ ባለሙያዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ወሬውን ሰምቶ ብቻ እንዳይጠቀም አሳስበዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም በባህር ዳርና አካባቢዋ እንቅስቃሴ ስለቆመ ጉዳዩን በትኩረት ለመከታተል አስቸጋሪ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ማንኛዉም አይነት መድኃኒት በብሔራዊ አማካሪ ኮሚቴ ታይቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ካልተፈቀደ በምንም መልኩ መጠቀም የተከለከለ መሆኑን ሙሉጌታ አብራርተዋል፡፡

በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ጥበበ ጊዎን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና ክፍል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብርሃም አማረ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በባህር ዳር ከተማ ህብረተሰቡ የወባ መድኃኒት የሆነውን ክሎሮኪንን በስፋት እየገዛ እንደሆነ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዶክተር አብርሃም ሰሞኑን በከተማዋ 10 ብር ይሸጥ የነበረው ክሎሮኪን 100 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

የወባ በሽታ መድኃኒቱን የሚጠቀሙ ሰዎች በተለይም ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸዉ ለሌላ ተጨማሪ የጤና ዕክል ሊገጥማቸው ስለሚችል ከመጠቀም መቆጠብ እንዳለባቸው ሙያዊ ምክራቸውን ሰጥተዋል፡፡

ህብረተሰቡ መድኃኒቱን ገዝቶ ቢያስቀምጥም እንኳን ቫይረሱን የመግደል አቅም ስለሌለዉ ከጤና ባለሙያ ትዕዛዝ ውጪ እንዲሁም እንደ ቅድመ መከላከያ መጠቀም እንደሌለበት ዶክተር አብርሃም አሳስበዋል፡፡

እንደ ዶክተር አብርሃም ገለጻ በአካባቢዉ በአሁኑ ጊዜ የወባ በሽታ ባልተከሰተበት ወቅት አስቀድሞ መድኃኒቱ ማለቁ ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን የወባ በሽታ ለማከም እና ለመከላከል እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡ ዶክተር አብርኃም አክለዉም ሌሎች አገሮች ክሎሮኪንን ለኮረና ቫይረስ መድኃኒትነት እንዲያገለግል ቢፈቅዱም በጤና ባለሙያዎች ያልታዘዘለት ሰው መውሰድ እንደማይችል ገልጸዉ ማህበረሰቡ በራሱ መንገድ መድኃኒቶች ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here