መቼም ባለፉት ሦስት ወራት በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በመቅረብ ከቻይናው ዉሃን ከተማ የተነሳውንና መላው የሰው ዘርን እያስጨነቀ፣ እያሰቃየ እንዲሁም በሺሕዎች እየገደለ ስለሚገኘው ኮቪድ 19 ወረርሺኝ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑትን ዶ/ር ቴድሮስን ወይም የሥራ ባልደረቦቻቸውን ያክል ድምጹን ከፍ አድርጎ የተናገረ፣ የወተወተ አለ ተብሎ አይገመትም።
ይሁንና ይህ ጩኸታቸው በሁሉም ዘንድ አንድ ዓይነት ምላሽ አግኝቷል ለማለት አያስደፍርም። በሚፈለገውም ደረጃ መንግሥታት የሚጠበቅባቸውን በወቅቱ ሳያደርጉ ቸል ማለታቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ብዙዎች ጣታቸውን ጣሊያን እና አሜሪካ ላይ በመቀሰር አብነት አድርገዋቸዋል። እስከ አሁን በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የዓለማችን ሰዎች የተለከፉ ሲሆን፣ ከ18ሺሕ በላይ ጣሊያናውያን እንዲሁም ከ15ሺሕ በላይ አሜሪካውያን ሕይወታቸውን በተለይ በመንግሥቶቻቸው ቸልታና ዳተኝነት ምክንያት አጥተዋል፤ ያሳዝናል!
ከዘመኑ ወረርሺኝ ጋር በተያያዘ ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አመራር አገራትና ግለሰቦች የተለያየ አቋሞች እያራመዱ በመሆናቸው የዓለም ትልልቅ የሚባሉ የመገናኛ ብዙኀንን ትኩረት ስበዋል። የማኅበራዊ ትስስር ገጾችም የሞቀ መሟገቻ ርዕሰ ጉዳይም ከመሆን አላመለጡም።
የኃያሏ አሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ ሌሎችም የኮሮናን ወረርሺኝ በተመለከተ ዶ/ር ቴድሮስንም ሆኑ ድርጅታቸው የዓለም ጤና ሁኔታን በበቂ ሁኔታና መጠን መረጃ ለዓለም አላቀረቡም ሲሉ ይከሳሉ። ‹‹ሐኪም ሳይሆኑ የዓለም ጤና ድርጅትን የሚመሩት…›› ሲሉ ትራምፕ ዶ/ር ቴድሮስን በማጣጣል ከቻይና የተቀሰቀሰውን ወረርሺኝ ለዓለም ወዲያውኑ አላሳወቁም ብለዋል።
በሌላ በኩል የዶ/ር ቴድሮስም ሆኑ ድርጅታቸው የኮቪድ 19 ወረርሺኝ በተመለከተ የሚጠበቅባቸውን ማሳሰቢያዎችና መረጃዎች በተገቢው ፍጥነት እና መጠን አሰራጭተዋል በሚል የአመራር ብቃታቸውን በማወደስ ያለማወላወል ድጋፍ የሰጧቸው አገራት፣ መሪዎችና ግለሰቦችም አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ጊዜው የመካሰስ ሳይሆን በጋራ ወረርሽኙን ከድርጅቱና ከአመራሩ ጋር በመሆን የምንከላከልበት ጊዜ ነው ሲሉ የክሱን ወቅታዊ አለመሆኑን በማንሳት ነቅፈዋል።
በዚህኛው ወገን ሩዋንዳው ፕሬዘዳት ፖል ካጋሜ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማህመት የሚጠቀሱ ሲሆን ከአገር ውስጥ ደግሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው እና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል አጋርነታቸውን ከገለጹት መካከል ናቸው።
እሰጣ ገባው በዚህም ሳያበቃ በዶ/ር ቴዎድሮስ ሙያዊ ብቃት ላይም ሆነ አመራር ላይ እንዲሁም ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ያለሙትንና ያጠፉትን በማንሳት ኢትዮጵያውያን እርስበርስ በማኅበራዊ ገጾች ላይ የጦፈ ክርክር ሲያደርጉ ሰንብተዋል።
በመጨረሻም ቴድሮስ ለዓለም መገናኛ ብዙኀን ፀጥታቸውን በመስበር በእሳቸው ላይ በግል ላለፉት ሦስት ወራት እስከ ግድያ የሚደርስ ዛቻና ዘረኛ ስድቦች እየደረሰባቸው እንደሆነ አስታውቀዋል። በተለይ ሲሉ ደግሞ ታይዋንን ከሰዋል። ታይዋንም ከብርሃን የፈጠነ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል በሰጠችው ምላሽ የዶ/ሩ ክስ መሰረተ ቢስ ነው ስትል አጣጥላ ይቅርታ ይጠይቁኝ ስትል አስጠንቅቃለች።
በመግለጫው ታይዋን ቫይረሱን መቆጣጠር ከቻሉ ጥቂት አገራት የምትመደብ ናት። በበሽታው የተያዙባት ሰዎች ብዛት 379 ሲሆን ሟቾች 5 ብቻ ናቸው በማለት የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱን ለመከላከል የሰጠሁትን የጥንቃቄ መረጃ ቸል ብሎታል ስትልም ትከሳለች።
አሁን ላይ በተቃውሞ ጎራ ያሉት ወገኖች ዶ/ር ቴድሮስ ከሥልጣናቸው እንዲወረዱ እንዲሁም ድጋፍ ሰጪዎቹ ደግሞ ከጎኖት ነን ለማለት የፊርማ ማሰባሰብ ሩጫ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012


