በሕገ-ወጥ መንገድ ጥራቱን ያልጠበቀ የቆርቆሮ ምርት ወደ አገር ውስጥ በስፋት በመግባቱ እና በመላው የኢትዮጵያ በመሰራጨቱ በአገር ውስጥ የሚገኙ የቆርቆሮ አምራች ፋብሪካዎችን ከገበያ ማስወጣቱ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ መሰረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ማኅበር ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው፤ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እየገባ የሚገኘው የቆርቆሮ ምርት ጥራቱን የጠበቀ አይደለም። ከዛም ባሻገር የአገር ውስጥ አምራቾችን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እያዳከመው እንደሚገኝ ጠቅሷል።
የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን ሙሉጌታ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን የሚደርስ የማምረት አቅም ተፈጥሮ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ቀድሞ ከተመዘገበው ውስጥ 10 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ማምረት እንደተቻለ ጠቁመዋል። ይህ ማለት በምርት ላይ ያለው ከ100 ሺሕ ቶን በታች ነው ማለት ነው ሲሉ አክለዋል።
መነሻውን ከተለያዩ ዓለም አገራት በማድረግ በጅቡቲ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ድሬዳዋ ከተማ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የሚከፋፈለው ቆርቆሮ፣ በሕገ -ወጥ መንገድ ገበያ ላይ መግባቱን ተከትሎ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች ገበያውን በመቆጣጠራቸው ተገቢ ላልሆነ የንግድ ውድድር እየዳረጋቸው እንደሆነም ታውቋል። ሰለሞን ጨምረውም ይህን ምክንያት አድርጎ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች አቅማቸው በማነሱ ምክንያት እየተዘጉ ነው። በዛም ምክንያት ብዛት ሥራ አጦች እየተበራከቱ ነው ሲሉ ገልፀዋል። ‹‹የሚፈለገውን ያህል ትኩረት ያልተሰጠው ዘርፍ ነው›› ሲሉም አክለዋል።
የማኅበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ ጨምረው እንደገለፁት፣ ገበያ ላይ ያሉት ምርቶች ከአገር ውስጥ አምራቾች የቀረቡ ተደርጎ ስለሚታሰብ፣ በአገር ውስጥ ምርት ላይ እምነት እያጡ ነው ብለዋል። በዚህ ምክንያት ከአምራቾች ብዙ ወቀሳ እየቀረበብን ነው ሲሉ አንስተዋል።
ይህ ደግሞ አገር ቤት ያሉ አምራቾች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ከማድረግ ባሻገር ለአገር ውስጥ አምራቾች የወጣላቸው ደረጃ መመዘኛ አለ። በዛ መሰርት እንዲያመርቱ ሲገደዱ፣ ነገር ግን ከውጭ በሕገ ወጥ መንገድ የሚያስገቡት የደረጃ ምዘና ካለመደረጉ ባሻገር ወደ ገበያው በመቀላቀል ከዋጋው ቀንሶ በማቅረብ በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩትን ከገበያ የማስወጣት ሥራ ይሠራል ብለዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ከሆነ፣ የንግድ ውድድሩንም ከመቀነሱ ባሻገር፣ የኢኮኖሚ ቀውሱ በረጅም ጊዜ የማይጠገን ነው። ምክንያቱም ምርቱ ከሚገባበት አገር ተነስቶ ወደተለያዩ የኢትዮጰያ ከፍሎች እስከሚከፋፈል ድረስ ያለውን ሂደት ለማለፍ የሚወጡ የሙስና ገንዘቦች በርካታ ናቸው። ከዛ፣ አልፎ እንደ አገር ኢትዮጵያ ከዘርፉ ልታገኘው የሚገባውን ግብር እንድታጣ ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል።
ከእነዚህ ችግሮች ባሻገር አምራቾች ደግሞ ለሚያወጡት ዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ አገልግሎት ወይም የምርት ጥራት አያገኙም። ይሄ እንደ አገር ትልቅ ኪሳራን ያስከትላልም ብለዋል።
በዚህ ዙርያ የተለያየ የገበያ ጥናቶች ተደርገው ነበር ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ነገር ግን በየጊዜው የሕገወጥ ንግዱ ቅርፁን እየቀያየረ ወደ አገር ቤት እየገባ መሆኑ ከባድ እንዳደረገባቸው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ነገር ግን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ከሠራበት እና ቁጥጥሩ ላይ ትኩረት ከተደረገ፣ በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚቻል እና ፍትኃዊ የሆነ የገበያ ውድድር ይኖራል በማለት ሰለሞን ሐሳበቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012



