መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ሕክምና ግብዓቶችን እያሰራጨ መሆኑን ገለጸ

0
541

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ የሕክምና ግብዓቶችን እያሰራጨ መሆኑን የኤጀንሲው የክምችትና ስርጭት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተስፋለም አድራሮ ገልጸዋል።
ኤጀንሲው የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚያስችሉ ከ200 ሺሕ በላይ የፊት መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ)፣ ከ3.2 ሚሊዮን በላይ ሰርጅካል የፊት መሸፈኛ ጭምብል፣ አንድ ሚሊዮን የፊት መከላከያ ፕላስቲክ፣ 21 ሚሊዮን ጓንት፣ አልጋ፣ የሙቀት መጠን መለኪያ ቴርሞ ሜትር፣ ለጤና ባለሞያዎች የሚሆኑ ልብሶችና ሌሎች መከላከያዎች በአጠቃላይ 13 የሚሆኑ የፊትና የሰውነት መከላከያ ግብዓቶች መሰራጨታቸውን ተስፋለም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሕክምናውን ለመስጠት የሚያስችሉ ኦክስጂን ኮንሴንትሬተር፣ ኦክስጅን ሲሊንደር፣ ሜካኒካል ቬንትሌተር እና ሌሎች የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶችም መሰራጨታቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
ስርጭቱ የተካሄደው ለለይቶ ማቆያ እና ሕክምናውን ለሚሰጡ በፌዴራልና በክልል ለተለዩ ሆስፒታሎችና ተቋማት ሲሆን፣ ይህም በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስርጭት ክፍፍል መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ኢንስቲትዩት በአስቸኳይ እንዲገዙ የተጠየቁ 700 ሺሕ ሊትር ሳኒታይዘር ለሁሉም ክልሎች እየተሰራጨ ሲሆን፣ 200 ሺሕ ሊትር አልኮል፣ ከ100 ሺሕ በላይ ፌስ ማስክ፣ 14 ሚሊዮን ሰርጂካል ፌስ ማስክ እና ሌሎች የግዥ ሂደታቸው ተጠናቆ በቅርቡ የሚገቡ መሆኑ ተነግሯል።
ኤጀንሲው ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ግምታዊ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ሊኖራቸው የሚችሉ የፊት መሸፈኛ ጭንብሎችን ጨምሮ ሌሎች የመከላከያ ግብዓቶች፣ የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶች ከውጭ እና ከአገር ውስጥ አቅራቢዎች ገዝቶ ለማቅረብ የግዥ ሂደታቸው መጀመሩንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አውስተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here