ኮሮናና የማስኩ ገበያ!

0
733

ኮቪድ-19 የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመቀነስ፣ ሰዎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ አካሄድ እንዲቀይሩ ተገደዋል። አንደኛውም አካላዊ ወይም ማኅበራዊ ፈቀቅታ ሲሆን፣ ለዚህም የሚያግዙ ሳኒታይዘር፣ የእጅ ጓንትና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎች ተጠቃሽ ናቸው። ይልቁንም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክን በሚመለከት መገናኛ ብዙኀን የተለያዩ ባለሞያዎችን የተለያየ ዓይነት ሐሳብ የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ማስኮቹ በየመንገዱ እየተቸበቸቡ ነው። ግዛቸው አበበ ይህ ግራ መጋባት ጥርት ብሎ መገለጥ፣ የማስኮች ጥራትና ተፈላጊነትም ላይ ለሕዝብ ትክክለኛ መረጃ መድረስ አለበት ሲሉ ያሳስባሉ።

ጥቂት ችላ ባይ መንግሥታት ያሉባቸውን አገራት ጨምሮ ኮቪድ-19 የኮሮና ቫይረስ እስከ አሁን በአፍሪካ ምድር ይህን ያህል የተጋነነ ስርጭት የለውም። ድሃዋ አፍሪካ በየዕለቱ ይፋ የምታደርገው የበሽታው ተጠቂዎችና የሰለባወች ቁጥር አነስተኛ መሆኑም አነጋጋሪ ሆኗል። በአንድ በኩል በአፍሪካ ብዛት ያለው ምርመራ ማድረግ አለመቻሉ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት እንዲመስል አድርጓል ባዮች ሲኖሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካ አየር ንብረት ሞቅ ያለ መሆኑ ለቫይረሱ ስርጭት ስላልተስማማ ችግሩ ጎልቶ አልተከሰተ ይሆናል የሚሉም ወገኖች አሉ።

ነገር ግን ብዛት ያለው ምርመራ ስለማይደረግ ትክክለኛ የታማሚዎች ቁጥር አልታወቀም የሚሉት፣ በሽታው የሚገድላቸውን ሰዎች ሲጠባበቁ ሰንብተው ያሰቡትን ያህል ሆኖ ስላልተገኘ ዝምታን እንዲመርጡ ተገድደዋል። የአፍሪካ ሞቃታማ የአየር ንብረት ለቫይረሱ ላይስማማ ይችላል ባዮቹም መካከለኛው ምሥራቅን በመሰለ ሞቃታማ ስፍራም ሆነ ቅዝቃዜው ከባድ በሆነባቸው ቦታዎች ቫይረሱ አልበገር ብሎ መሰራጨቱን በማየታቸው፣ እንደቀደሙት ዝምታን መርጠዋል።

የአፍሪካ ጉዳይ ግራ ማጋባቱ እንዳለ ሆኖ ነገሩን በስጋት የሚያዩ ወገኖችም አሉ። በአፍሪካ ኮቪድ-19 እንደ አንዳች ፍንዳታ በአንዴ ድብልቅልቁን የሚያወጣ ችግር ያስከትል ይሆናል የሚሉ ወገኖች አሉ። የተባበሩት መንግሥታትና የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ የፈተና ጊዜ ገና መሆኑን በመናገር ላይ ናቸው። መዘናጋት፣ ጥንቃቄ አለማድረግና አለመዘጋጃት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል በመናገር እያስጠነቀቁ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ በአፍሪካ የበሽታው ግዳዮች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ አስጠንቅዋል። ጉቴሬዝ የጠቀሱት ቁጥር በሽታው የሚይዛቸው ሰዎችን የሚመለከት አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል። እርሳቸው የተናገሩት ስለ ሟቾች ብዛት ነው።
ጉቴረዝ ይህን ማስጠንቀቀያ የሰነዘሩት ባለጸጋ አገራት አፍሪካንና ሌሎችን አዳጊ አገራት ለመርዳት እንዲዘጋጁ ጥሪ ባደረጉበት ንግግራቸው ላይ (መጋቢት 22/2012) ሲሆን፣ እስከዚያ ዕለት በአፍሪካ የኮቪድ-19 ተጠቂዎች ቁጥር 3 ሺሕ 924፣ በበሽታው የሞቱት አፍሪካውያን ብዛትም 117፣ በሽታው የታየባቸው የአፍሪካ አገራት ቁጥርም 47 ደርሶ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቀጣዮቹ ኹለትና ሦስት ሳምንታት ለኢትዮጵያ ፈታኝ ሊሆኑ እንደሚችሉ የተናገሩት ከዚህ አኳያ ሊሆን ይችላል።

ሕዝብ ግራ በመጋባትና መፍትሔ የሚለውን ነገር በማፈላለግ ላይ ተጠምዷል። በአዲስ አበባ ትንሽም ብትሆን ገንዘብ አለኝ የሚለው ሕዝብ ተስፋ ባለመቁረጥ አልኮል፣ ሳኒታይዘር፣ ጓንት፣ ማስክ ወዘተ… ፍለጋ ሲባዝን ይስተዋላል። የማስኩ ነገር እናቆየውና፣ በአሁኑ ሰዓት ጓንት በየትኛውም የከነማ ፋርማሲ የሚገኝ ሲሆን አልኮልና ሳኒታይዘር ግን እንደ ዕድል የሚገኙ እየሆኑ ነው። የቫይረሱን በኢትዮጵያ መገኘት እንደተሰማ የእጅ ጓንት የተባለው ነገር ወደ ገበያ እየወጣ ሲሆን የማስኩ ገበያ ደግሞ አጠያያቂም አስጊም ሆኗል።

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል ይረዳሉ የተባሉ የተለያዩ ነገሮች በሥመ-ማስክ ይቸበቸባሉ። 10 ብር፣ 30 ብር፣ 50 ብር ድረስ ዋጋ ይጠራላቸዋል። ተገቢነታቸውና በሽታ አምጭ ተሕወሶችን መከላከሉ ላይ ያላቸው ውጤታማነት ያልተረጋገጠላቸው ማስኮችን ጨምሮ፣ ሰዎች ማስክ ተብሎ ገበያ የቀረቡ ነገሮችን ሁሉ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ገዝተው ሲሄዱ ይታያሉ።

ይህ ግብይት የአዲሰ አበባ ማዘጋጃ ቤትና ምኒልክ አደባባይ ዙሪያን ጨምሮ ብዙ ሕዝብ በሚርመሰመስባቸው አደባባዮችና ጎዳናዎች ዳር በጠራራ ፀሐይ የሚካሄድ ነው። ቢሆንም እነዚህ ማስክ የተባሉትን ቁሶች እያመረቱና እያስመረቱ የሚጠቀሙ ወይም ለደንበኞቻቸው የሚያቀርቡ ድርጅቶች የጋዜጠኞችና የሐኪሞችት ኩረት አግኝተው አያውቁም። ሕዝብን የሚያዘናጋና ለአደጋ የሚያጋልጥ ሊሆን ስለሚችል ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ቁጥጥር ማድረጉን ችላ ባይሉት ጥሩ ነው።
በኢትዮጵያ የሚታየው የአልኮል፣ የሳኒታይዘርና የሌሎች በሽታውን መከላከያና መዋጊያ ኬሚካሎችና ቁሶች እጥረት በቶሎ ሊቀረፍ ይገባዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ አፍንጫንና አፍን ለመሸፈን በሚያስችለው ማስክ ላይ ሳይንሳዊ ሥራ መሥራትንና ሃቀኝነትም የሚጠይቅ ችግር መኖሩን በማመን፣ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድን ቅድሚያ መስጠት ይገባል።

ኢትዮጵያችን ውስጥ በመገናኛ ብዙኀን ላይ ጭምር የማስክን ጥቅም የሚያጣጥሉና ማስኩን ሁሉም ሰው ሊያደርገው አይገባም የሚሉ መረጃዎች እየተሰራጩ ቢሆንም፣ አንዳንድ አገራት ደግሞ ዜጎቻቸው ሁሉ ማስክን የመጠቀም ግዴታ እንዳስቀመጡ ይሰማል። በውጭ አገራት ከበሽታው ጋር በተያያዘ የሚሠሩ ዜናዎች ሲቀርቡ፣ በቴሌቪዥን መስኮቱ ላይ የሚታዩት ሰዎች ማስኮችን አድርገው ስለሚታዩ ኢትዮጵያችን ውስጥም ሕዝቡ ማስክን መጠቀም እንደሚገባው ያመነ ይመስላል። እናም የማስክ ገበያው ደርቷል።

በማስክ ሥም ገበያ ላይ ከሚገኙት መሸፈኛዎች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓርማ ያለበት ከጨርቅ የተሠራ ነገር ነው። ስለዚህ ቁስ እናውቃለን የሚሉ ሰዎች ነገርየው ‹በበረራ ወቅት እንቅልፍ የመጣባቸው ተሳፋሪዎች ዐይናቸውን የሚሸፍኑበት ነው› ይሉታል። በእርግጥም ይህ የአየር መንገዱ ሎጎ ያረፈበት መሸፈኛ ቅርጹና መጠኑ ለዐይን እንጅ አፍንና አፍንጫን በአንዴ ለመሸፈን የሚመችም የሚበቃም አይደለም።

ይህን መሸፈኛ አየር መንገድ ለገበያ አቀረበው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር ባይሆንም፣ የአየር መንገድ ንብረት ስለሆነ ብቻ ጥራቱና ውጤታማነቱ አስተማማኝ መሆኑ እየተነገረለት ነው። ሰውም በዐስር እና በኻያ ብር በገፍ እየገዛው ይታያል።

ሌላው በሽታ አምጭውን ሕዋስ ይከላከላል ተብሎ ገበያ ላይ ከሠላሳ እስከ ሃምሳ ብር የሚቸበቸብ ነገር በእርግጥም አፍንና አፍንጫን ለመሸፈን የተሠራ ማስክ ይሁን እንጂ፣ አገልግሎቱ ብናኝን ለመከላከል ብቻ የሆነ ማስክ ነው። ይህ ማስክ ከነ ማሸጊያው ከተገኘም በላዩ ላይ ‘Dust Mask’ የሚል ጽሑፍ ማንበብ ይቻላል።
በመንገድ ዳርና በአደባባዮች ዙሪያ ለገበያ ቀርበው ባይታዩም፣ አንድንድ ሰዎች ውድ የሆኑ ነገር ግን ለወቅቱ ችግር ተገቢ መከላከያዎች መሆናቸው ያልተረጋገጡ ሌሎች የማስክ ዓይነቶችን ሲጠቀሙ ይስተዋላሉ። እነዚህ ማስኮች በግብርና ቦታዎችና አንዳንዴም በቤት ውስጥ ጸረ-ተባይ መድኃኒቶችን (በዱቄትና በፈሳሽ መልክ የተሠሩ) የሚረጩ ሰዎች እንዲጠቀሙባቸው ተብለው የተዘጋጁ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስኮች ናቸው።

ግለሰቦች በየቤታቸው አምርተው ወደ ገበያ የሚያወጧቸው ማስኮችም አሉ። ማስኮቹ የተሠሩበት የጨርቅ ዓይነት፣ አሰፋፉ ወዘተ… በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት እንዳለው በግልጽ የተነገረ ነገር የለም። እነዚህ ማስኮች ከ20 እስከ 30 ብር የሚቸበቸቡ ሲሆን፣ በአንዳንድ ሚዲያዎችና በማኅበራዊ ገጾች ላይ እነዚህን ማስኮችን እየሠሩ በነጸ የሚያድሉ የተባሉ ሰዎች እንደ በጎ አድራጊዎች ተደርገው ሲወደሱና ሲመሰገኑ ይሰማል። ሐኪሞችስ ምን ይላሉ?
ከየት እንደመጡና ለምን ዓላማ እንደተሠሩ የማይታወቁም ሆነ የሚታወቁ፣ ነገር ግን ኮቪድ-19ኝን እንደሚከላከሉ ማረጋገጫ ያልተሰጠባቸው ማስኮችን በየሰው ፊት ላይ ማየትም በብዛት የሚያጋጥም ነገር ነው።

እነዚህን ሁሉ ነገሮች እየተከታተሉ ማስተማር የሐኪሞች ሥራ ቢሆንም፣ ከእነዚህ ወደ ገበያ ከወረዱ ማስኮች ጋር ትውውቅ ያላቸው አየር መንገድን የመሳሰሉ ድርጅቶችም ወደ ሚዲያዎች ቀርበው ተገቢውን መረጃ መስጠት፣ ማስኮቹ ተገቢ ባልሆነ ጉዳይ ላይ ጥቅም ላይ እየዋሉና ሰው ለችግር እንዲጋለጥ እየተደረገ ከሆነም፣ ከሚመለከታቸው ሕግ አስከባሪ መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይገባቸዋል።

ጋዜጠኞችም፣ ሐኪሞችንና የንብረቶቹን ባለቤቶች በማነጋገርና በማማከር ትምህርት ሊሰጡባቸው ይገባል። በእርግጥ አንዳንዶቹ አዘናጊና ለአደጋ አጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉና ስህተቱ ቀላልና ችላ ሊባል የሚገባው ወይም ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ አይደለም።

ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ስለ ማስክ ጠቃሚነትና እነማን ሊጠቀሙበት ይገባል በሚለው ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ጨምሮ በመገናኛ ብዙኀን ላይ ሲስተጋቡ የሚደመጡ ግራ አጋቢ ነገሮች አሉ። ከእነዚህ አባባሎች ውስጥ የአንዳንዶቹ አንደምታ ማስኩን ለሕክምና ባለሙያዎች እንተውላቸው የሚል ይመስላል። ከሆነም በግልጽ ሊነገር ይገባል። ወይም ጤና ሚኒስቴር ከማስክ አምራቾችና ከአቅራቢዎች ጋር ሊነጋገርበት ይገባል።

ነገር ግን ማስክን ያለ ሐኪም ትእዛዝ ወይም ፈቃድ መጠቀም ዋጋ እንደሌለው፣ ማስክ መጠቀም አደጋ ሊኖረው እንደሚችል፣ ማስክን መጠቀም ትርፉ ኪሳራ ብቻ እንደሆነ ወዘተ… ተደርጎ መነገሩ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ትክክለኛው አካሄድ ማስክን ያለ ሐኪም ፈቃድ ጥቅም ላይ እንዳይውል መከልከል ነው ወይስ ጥራት ያለው ማስክን በብዛት ተመርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ የሚለው ሐሳብ በጥንቃቄ ሊጤን ይገባዋል።

የሕክምና ባለሙያዎች ከሐኪም ቤት ውጭ በተለይም በሕዝብ መጓጓዣዎች ሲጠቀሙ ማስክ አድርገው የሚታዩባቸው አጋጣሚወች ስላሉ፣ ማስክን የታመመ ሰው ወይም ወደ ታመመ ሰው የሚቀርቡ አስታማሚወችና ሐኪሞች ‹ብቻ› ሊደርጉት ይገባል የሚለውን አባባል ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነው። ለዚህም ይመስላል፣ የአሜሪካ ድምጽ ራድዮ (ቪኦኤ) የአማርኛው ክፍል በማስኩ ዙሪያ ብቻ የሚያጠነጥን አንድ ፕሮግራም አዘጋጅቶና ባለሙያ ጋብዞ ሰፊ ውይይትን ያስተናገደው።
ግዛቸው አበበ በኢ-ሜይል አድራሻቸው
gizachewabe@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here