በዓልና ቤተሰብ

0
911

የቻለ ቤቱ ሆኖ፣ ያልሆነለትና የሥራ ሁኔታ የማይፈቅድለት ሩጫውን እንደቀጠለ ፋሲካ በዓል ደርሷል። ቀድሞ የነበረው የቤት ውስጥ ጉድጉድ እንደወትሮው ላይኖር ይችላል። ለምን ቢሉ፣ እንደ ቀድሞው ሰው ዘመዱ ቤት እንዳይሄድ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከልክሏል። በትክክል ለቤተሰቡ፣ በእድሜ ለገፉ ወላጆችና ዘመዶቹ የሚያስብና የሚወዳቸው ደግሞ ይህን ይተገብራል።

እናም ይህ መሆኑ ጠላ ጠምቆ፣ የተለያየ ዓይነት ምግብ አዘጋጅቶ እንግዳን መቀበል እንዳይኖር አድርጓል። ለእናቶች፣ ለሚስቶች፣ ለእህቶች ይህ የበዓል ሥራቸውን ሊቀንስ ቢችልም ጭር ማለቱ ሳያስከፋቸው አይ ቀርም። ቢሆንም ባለው አቅምና ባለው ሰው ቤትን አድምቆ፣ ጤናንም ጠብቆ ማሳለፍ ይቻላል።

ሴቷ በቤቷ አገልጋይና እመቤት ትሁን አልያም ውጪ ወጥታ ለቤተሰቡ ገቢ የምታስገኝም፣ አሳቢነቷ የሚቀር አይደለም። እናት ልጇ ከቤት ሲወጣ፣ ለሚስት ቧላ ወደ ሥራ ሲሄድ፣ ‹‹ቀስ እያልክ! መንገድህን እያየህ! እየተጠነቀቅህ› ማለቷ አይቀርም። ‹ኑሩልኝ!› ስትል ነው። እና አሁንም ይህን የመሰለ ጥንቃቄ ልጆቿ፣ ባሏ ወይም ወንድሞቿ እንዲያደርጉ የማድረግ አቅም አላት። ታሳስባለች፣ ታስታውሳለች።

በዓልንም ታድያ ይህ ክፉ ጊዜ እስኪያልፍ ሴቶች በቤት ውስጥ መቀመጥን እንደምንም ሊቀበሉት ይገባል። ዘመድ ጥየቃን የሚያዘወትሩ ብዙውን ጊዜ ሴቶች መሆናቸው ይታወቃልና ነው። በትዳር ውስጥ ከሆነም የባልም ሆኑ የሚስት እናት ልጆቻቸው ወደ ቤት እንዲመጡና በዓልን አብረው እንዲያሳልፉ ከመጠየቅ መቆጠብ አለባቸው። አንድም የእነርሱ ቅር መሰኘት ነውና ‹የመጣው ይምጣ እንጂ በዓልንማ እዛ ነው የምናሳልፈው› እንዲሉ የሚያደርገው፣ እናቶች ይህን እንዳይዘነጉ አደራ ይድረሳቸው።
ጤነኛ ለሆነና ዛሬን አልፎ የነገን ብርሃን ለማየት የሚበቃ ሰው፣ ሁሌም በዓሉ ነው። እርግጥ ነው በሃይማኖትና በእምነት ውስጥ ከበዓላት ሁሉ የሚልቁ በዓላት አሉ። ፋሲካ ደግሞ የትንሣኤ እለት ብቻ ሳይሆን ከዛም በኋላ ባሉት 50 ቀናትም ሲታሰብና ሲከበር የሚቆይ በዓል ነውና ጊዜ አለ። ዛሬን ተርፎ ለነገ መኖር ይሻላል።
በእርግጥ ጸጸቱንስ ማን ይችለዋል? አያቶቻችን፣ እናትና አባቶቻችን፣ በእድሜ የገፉ ዘመድ ወይም ጎረቤታችን፣ የምንወዳቸው ሰዎች ላይ ቫይረሱን ብናስተላልፍ፣ ወጣት ስለሆንን እኛ ተሻግረነው እነርሱ አቅም አጥተው ቢቀሩ፣ ‹‹ያቺን ቀን ቤቴ በተቀመጥኩኝ ኖሮ!› ማለታችን ይቀራል? ‹‹ምነው በቀረብኝ ኖሮ!› የሚል ጸጸት ሳይነካን ያልፋል?

አይመስለኝም። እናም ከሌላው ማኅበራዊ ጉዳያችን፣ ከሌላው አሳሳቢና አስጨናቂ ኹነቶቻችን ጎን ለጎን፣ ይህንንም እናስብ። ልጆችሽ ከትምህርት ቤት የቀሩት ከቤት እንዳይወጡ ነውና ጠብቂያቸው፣ ባለቤትሽና አንቺ ከሥራ እረፍት የወሰዳችሁት እናንተም አገርም ደኅና እንድትሆን ነውና ቢቻል አትውጡ። የምትወጡበት ግድ የሚል ሥራ ካለ፣ የቀን ገቢችሁ ከሆነ ኑሮአችሁን የሚደግፈው፣ በቤታችሁ ብቻ ዘግታችሁ የምትጠቀሙበት ተቀማጭ ገንዘብና እህል የሌላችሁ ከሆነ፣ ብቻ በቸልታና ‹ኧረ አይደርስብኝም!› በሚል መታበይ ካልሆነና በቂ ምክንያት ካለ፣ ስትወጡ ተጠንቀቁ።

በፊት ስንል ነበር፣ መጀመሪያ የአገር ሰላም ይቀድማል። መጀመሪያ አገር ሰላም እንድትሆን ሁላችን እንረባረብ እያልን ነበር። አሁን ግን የአገር ሰላም በፖለቲከኞችና ባለሥልጣናት፣ በአክቲቪስቶችና እውቅናን በሚሹ ሰዎች እጅ አይደለችም። አሁን ሰላም በየሁላችን ፈቃድ ላይ ናት። በጥንቃቄያችን ውስጥ ትገኛለች። በአካል በመራራቅ፣ ለአረጋውያንና በእድሜ ለገፉ፣ የተለያየ ሕመም ላለባቸውና አዲሱን በሽታ መቋቋም ለማይችሉ በመራራት ውስጥ ትገኛለች። በጥንቃቄና በማስተዋል እንቆይ።
መልካም በዓል ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here